ታላቁ ታሪክ ዓድዋ

እነሆ የየካቲት ወር ታላቁ ታሪክ፣ የኢትዮጵያም ታላቁ ታሪክ ዓድዋ ትናንት ተከበረ። ዓድዋ፣ ትናንት ዛሬም፣ ነገም ነውና እነሆ በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ታላቁን የዓድዋ ታሪክ እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን እናስታውስ።

ከ18 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 18 ቀን 1998 ዓ.ም ስመ ጥሩ ባለቅኔ ፀጋዬ ገብረመድኅን አረፈ።

ከ11 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም አቡነ ማትያስ፤ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ሆነው ተመረጡ።

ከ12 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት 23 ቀን 2004 ዓ.ም ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ አረፈ።

ልክ ከዛሬ 40 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት በዛሬዋ ቀን የካቲት 24 ቀን 1976 ዓ.ም በዓሉ ግርማ ከቤቱ ወጥቶ ቀረ። እስከ አሁን ድረስ የት፣ እንዴት፣ እና በምን እንደሞተ ያልታወቀው (መሞቱ ራሱ ያልተረጋገጠው) ደራሲ እና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ከሥራዎቹ ያላነሰ አጠፋፉም አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል።

ከዛሬ 101 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ቀን የካቲት 24 ቀን 1915 ዓ.ም ዝነኛውና አንጋፋው ‹‹ታይም›› መጽሔት መታተም ጀመረ።

ወደ ዓድዋ ታሪካችን እንመለስ። ዓድዋን ስናስታውስ ከ28 ዓመታት በፊት በ1988 ዓ.ም 100ኛ ዓመቱ ነበር። 100ኛ ዓመቱ እንዴት እንደተከበረ ከ35 ዓመት በታች የሆነ ወጣት ብዙም አያስታውስም። በወቅቱ የመገናኛ ብዙኃን ተደራሽነቱ ጠባብ ስለነበር ከከተማ ነዋሪ ውጭ ያለው ማህበረሰብ ሁነቱን አያስተውልም ማለት ይቻላል።

ዕለታዊ ሁነቶችን እየዘገበ ታሪክ የሚሰንደው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የወቅቱን ሁነቶች ሰንዶ አስቀምጦልናል። የካቲት ወር ከገባ የመጀመሪያው ሳምንት ጀምሮ ሁነቶች የነበሩ ቢሆንም በዋዜማው ሰሞን የካቲት 21 ቀን 1988 ዓ.ም በታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ስለዓድዋ በዓል አከባበር የወጣውን ፕሮግራም ለአሁኑ አንባቢ እናስታውስ።

በዕለቱ (በ23 ማለት ነው) ከሌሊቱ 10፡00 የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ይከናወናል። ከማለዳው 12፡00 አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ደወል ያሰማሉ። በዚሁ ሰዓት መድፍ ይተኮሳል። ከማለዳው 1፡00 በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ሥነ ሥርዓቱ መካሄድ ይጀምራል።

በተመሳሳይ በዓድዋ ከተማ ከሌሊቱ 10፡00 የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ይካሄዳል፤ ከማለዳው 12፡00 በዓድዋ ከተማ የሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ደወል ያሰማሉ። ከማለዳው 4፡00 በዓድዋ ከተማ የአውሮፕላን ትርዒት ይካሄዳል።

እንዲህ እንዲህ እያለ የዓድዋ የድል በዓል ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ ሲዘከር ቆይቶ በዚህ ዓመት ደግሞ 100ኛ ዓመቱን በሚያስታውስ ሁኔታ አንድ አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል። ይሄውም የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ተገንብቶ ተመርቋል። 100ኛ ዓመቱ ሲከበር ጀምሮ የዓድዋ መታሰቢያ የመሠረት ድንጋይ እንደሚቀመጥ ሲወራ እንደቆየ በየዘመኑ የነበሩ ዘገባዎች ያሳያሉ። እነሆ ዘንድሮ እውን ሆኖ ተመርቋል። ይህ ክስተት በሚቀጥለው ትውልድ ሲታወስ ይኖራል።

ለዚህ ሁሉ መሠረት ወደሆነው የዓድዋ ታሪክ እንሂድ!

ከታዋቂው የታሪክ ጸሐፊ ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› መጽሐፍ፣ ከተክለጻድቅ መኩሪያ ‹‹አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት›› መጽሐፍ፣ ከተለያዩ ድረ ገጾች እና የመገናኛ ብዙኃን ባገኘናቸው መረጃዎች የዚህ ሳምንት ክስተት የሆነውን ዓድዋ እናስታውሳለን።

የዓድዋ ታሪክ የሚጀምረው ባለፈው ሳምንት (በየካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ እንደገለጽነው) ሴራው የጀመረው ከዓድዋ ጦርነት 12 ዓመታት በፊት በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር 1884 ነው። ይህም በታሪክ ‹‹የበርሊን ጉባዔ›› እየተባለ የሚጠራው ማለት ነው። የአውሮፓ ሀገሮች በርሊን ላይ ባደረጉት ስብሰባ አፍሪካን ለመቀራመት ሲወስኑ የጣሊያን ድርሻ ኢትዮጵያ ሆነች። በነገራችን ላይ ይህ መዘዝ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በነበረው የሃያላን ሀገራት ውይይት ላይ ለተሸናፊዋ ጣሊያን ከፍተኛ አደጋ እንደጋረጠባት፣ ለኢትዮጵያ ደግሞ የዲፕሎማሲ ኩራት ሆኖ እንደነበር የአምባሳደር ዘውዴ ረታ ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› መጽሐፍ በሰፊው ያብራራል። ዓድዋ እነ አክሊሉ ሃብተወል ከሃያላን ሀገራት ጋር ሲከራከሩ የታፈሩና የተከበሩ እንዲሆኑ ኩራት ሆኗል።

ኢትዮጵያ በቅድመ ዓድዋ ከወራሪዎችና ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር ተዋግታም ድል አድርጋለች። ከእነዚህም አንዱ በአጼ ዮሐንስ አራተኛ ዘመነ መንግሥት 1879 ዓ.ም ዶግዓሊ ላይ በራስ አሉላ አባነጋ አዝማችነት በጣሊያን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀዳጀችው ድል ነበር። በዚህም የጣሊያን ወታደሮች ለወሬ ነጋሪ ሳይተርፉ በአሉላ አባ ነጋ ዶግዓሊ ላይ ዶግ አመድ ሆነዋል። የኢትዮጵያ ነገር በርሊን ላይ እንደታሰበው ሊሆን አልቻለም።

በጦርነቱ እንደማይሳካላት ያወቀችው ጣሊያን እንደገና ደግሞ ውል ማጭበርበር አሰበች። በመሆኑም ለዓድዋ ጦርነት ምክንያት የሆነው የውጫሌው ውል፤ በአንቀጽ 17 በጣሊያንኛ ትርጉሙ ኢትዮጵያ የጣሊያን ጥብቅ ግዛት ነች። የውጭ ግንኙነቷም በጣሊያን በኩል ይሆናል የሚለው ሐረግ መዘዝ አመጣ። በዚች መዘዘኛ አንቀጽ ምክንያት ጦርነቱ የማይቀር መሆኑ ተረጋገጠና ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ለጦርነቱ የሀገራቸውን ሕዝብ ‹‹ክተት›› ጠሩ።

‹‹አሁንም ሀገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል ። በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው፣ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ፤ …›› የሚለውን አዋጅ ተናገሩ። እነሆ ይህ አዋጅ በብዙ ሰዎች ዘንድ በቃል ሁሉ ሳይቀር ይታወቃል።

ዳግማዊ አጼ ምኒልክ አዋጁን ሲናገሩ፤ ኢትዮጵያውያን የእርስ በእርስ ግጭታቸውን፣ ውስጣዊ ችግሮቻቸውንና አለመግባባታቸውን ወደጎን ትተው፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተጠራርተው እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነው የመሪያቸውን ጥሪ ተከትለው ወደ ጦር አውድማው ተመሙ።

በ1988 ዓ.ም የዓድዋ ድል 100ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲከበር፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታተመ የጥናት መድበል ላይ እንደተጻፈው፤ የጦርነቱ አዝማቾች፤ ዳግማዊ አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ፣ ንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ አባነጋ፣ ራስ መኰንን፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ ወሌ፣ ራስ ስብሐት፣ ደጃዝማች ሐጎስ ተፈሪ፣ ራስ አባተ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (ባልቻ አባ ነፍሶ) እና ዋግ ሹም ጓንጉል ናቸው።

እውቁ የታሪክ ጸሐፊው ተክለ ጻድቅ መኩሪያ እንደሚነግሩን፤ የኢትዮጵያ ተዋጊዎች የጣሊያንን ወታደር ከበው እየተፏከሩ በጥይትና በጎራዴ ሲደበድቡት የኢጣሊያ ጦር አራት ሰዓት ከተዋጋ በኋላ ሽሽት ጀመረ። በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን እየተከታተሉ ሲወጉት፣ ጦር አዝማቹ ጄኔራል አልቤርቶኒ ተቀምጦበት የነበረው በቅሎ ተመቶ ወደቀ። ወዲያው ተነሥቼ አመልጣለሁ ብሎ ለመነሣት ሲጥር ከቅምጡ ሳይነሳ እየተሽቀዳደሙ የሚሮጡት ኢትዮጵያውያን ደርሰው ጄኔራሉን ማረኩት። የአንደኛው ክፍለ ጦር አዛዡ ተማርኮ፣ ሠራዊቱ በጭራሽ ከጠፋ በኋላ ሁለተኛው ክፍል የጦር ሠራዊት ‹‹ራአዮ›› ከሚባለው ስፍራ ላይ ሆኖ፣ ካራት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ የሦስተኛውን ክፍል የጄኔራል ኤሌናን ጦር ጨምሮ ተዋግቶ በመጨረሻ የጦር አዛዡ ጄኔራል አሪሞንዲ እዚያው ጦርነቱ ላይ ሞቶ ተገኘ።

ከዚህም በኋላ፤ በመጨረሻ ያለው የጣሊያን ጦር በተለይ ማርያም ሸዊቶ ከሚባለው ስፍራ ላይ ተጋጥሞ ከቀድሞው የበለጠ ጦርነት ተደረገ። ይልቁንም የመጨረሻው ድል የሚፈጸምበት በመሆኑ የሁለቱም የጦር ሠራዊት ተደባልቆ በጨበጣ በሚዋጉበት ጊዜ፣ በጨበጣ በሚደረገው ዘመቻ ከኢጣሊያኖች ይልቅ ኢትዮጵያውያን በጎራዴ አነዛዘር ቀልጣፎች ነበሩ።

ይሁን እንጂ ጣሊያኖች ተስፋ በቆረጠ ኃይል እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ በጉብዝና ሲዋጉ በመጨረሻ አዛዣቸው ጄኔራል ዳቦርሚዳ በጥይት ደረቱን ተመቶ ሞተ።

የጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› መጽሐፍ በወቅቱ የነበረውን ክስተት እንዲህ ይተርከዋል።

‹‹የተተከለው ድንኳን ሲታይ ከብዛቱ የተነሳ አፍሪካ አውሮፓን ለመጠራረግ የተነሳች ይመስላል። የጦርነቱ ዕለት ኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው፣ ጠመንጃና ጦር ይዘው፣ ጎራዴ ታጥቀው፣ የነብርና የአንበሳ ቆዳ ለብሰው፣ አዝማሪዎቹ እየዘፈኑ ቄሶች፣ ልጆች፣ ሴቶች ሳይቀሩ ፀሐይዋ ፈንጠቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ጊዜ የጣሊያንን ጦር አሸበሩት››

በወቅቱ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበሩት ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም በዓድዋው የጦር ግንባር በመሰለፍ ያስተዋሉትን ‹‹ኦውቶ ባዮግራፊ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዲህ ጽፈውታል።

‹‹የሰው ብዛት እንደ ጎርፍ ሆነ። እግረኞችም በቅሎኞችም ተደባልቀን እንርመሰመሳለን። ፈረሰኞች በጎን እያለፉን ይቀድማሉ። ይሮጣሉ! እንደተቻለን እንሽቀዳደማለን።

ጠመንጃ ሲንጣጣ ሰማን፣ መድፍ ወዲያው ያጓራ ጀመር። ተኩሱ እያደር እየባሰበት ተቃረበን፣ አረሮቹ ማፏጨት ጀመሩ። የቆሰሉ ሰዎች ተቀምጠው አገኘን። አያ ታደግ እጁን ተመትቶ ከመንገዱ ዳር ከዛፍ ሥር ተቀምጧል። ገና በሩቁ አይቶን ተጣራ፣ ቁስሉን በመቀነቱ አሰርንለት። ጥለነው እንዳንሄድ ለመነን፣ ፈይሣ ጠመንጃ የለውም፤ የቁስለኛውን ጠመንጃ ተሸከመና እዚያው ቀረ። እኔ ዝም ብዬ ወደ ግምባር አለፍኩ። የማውቀውን ሰው አንድም አላጋጠመኝም። ተኩስ ስለበዛ መሮጥ የማይቻል ሆነ። የሰውም ብዛት እንደልብ አያስኬድም።

ደጃዝማች ማናዬ እና ልጅ አስፋው ሁለቱም ቆስለው ድንጋይ ተንተርሰው ተጋድመው አገኘኋቸው። ልጅ አስፋው (በኋላ ፊታውራሪ አስፋው) አወቀኝና ጠቀሰኝ። ዝም ብዬው እንዳላየ ሰው ወደ ግምባር ሮጥኩ። ጦራችን ተደባልቋል። ሰውና ሰው አይተዋወቅም። ሴቶች ገምቦ ውሃ እያዘሉ፣ በበቅሎዎቻቸው እንደተቀመጡ፣ ለቁስለኞች ውሃ ያቀርባሉ። ሲነጋገሩ ሰማኋቸው። «ኧረ በጣይቱ ሞት» ይላሉ። እቴጌ የላኳቸው ይሆናሉ እያልኩ አሰብኩ።

ነጋሪቱ ከግምባርም፣ ከጀርባም፣ ከቀኝም ከግራም ይጎሸማል። የተማረኩ ጣልያኖችን አየሁ። ወዲያው ምርኮኞቹ በዙ፣ አንዳንዶቹ ወታደሮች፣ ይበልጡን ጣልያኖችን እየነዱ መጡ። በኋላ የምርኮኞች ብዛት ለዓይን የሚያሰለች ሆነ፤ ድል ማድረጋችንን አወቅሁ። ጣልያኖች መዋጋታቸውን ትተው ማርኩን እያሉ ይለምናሉ። እንደዚህ የዓድዋ ጦርነት ዕለት አንድ ጥይት እንኳ ሳልተኩስ ጦርነቱ አለቀ።››

በዚህ ሁኔታ ነው እንግዲህ የዓድዋ ጦርነት የተጠናቀቀው፤ ክብር ለጀግኖቻችን እና ታሪክን ሰንደው ላቆዩልን ጸሐፊዎች!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን  የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You