አዳማ፡– ከተላላፊ በሽታዎች በላይ በአየር ብክለት ምክንያት የሚመጡ የጤና ችግሮች መበራከታቸውን የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ትናንት በአዳማ ከረዩ ሂል ሪዞልት የአካባቢ ቀን በተከበረበት ወቅት እንደገለፁት፤ በአገሪቱ የአየር ብክለት እየጨመረ መምጣት ተላላፊ በሽታዎች ከሚያስከትሉት ችግር በባሰ መልኩ ጤና ላይ ጉዳት እያመጣ ነው። በተለይም በብክለት ምክንያት እንደ ካንሰር፣ የልብ እና የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች የሰው ሕይወትን በከፍተኛ ደረጃ እየቀጠፉ ናቸው።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ በከተማ መስፋፋት፣ በመኪናዎች ጭስና የነዳጅ ጥራት ማነስ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአየር ብክለት እያደገ መጥቷል። በዚህም የጤና ችግሩም እንዲሰፋ ሆኗል።
ችግሩ እንዳይባባስና ባለበት እንዲቆም ለማድረግ ኅብረተሰቡ ዘመናዊ ማብሰያዎችን እንዲጠቀም፣ ጭስ አልባ ትራንስፖርትን እንዲያዘወትርና የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱን ማዘመን እንዳለበት አሳስበዋል።
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦና ያደሳ በበኩላቸው፤ በአየር ብክለቱ ምክንያት እያየለ የመጣውን የጤና ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ተፈጥሮን ጠብቆና ተንከባክቦ ወደ ነበረበት መመለስ ይገባል ብለዋል። በተለይም በአሁኑ ወቅት በአየር ብክለት ምክንያት በደኖች፣ ወንዞችና ለም አፈሮች ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ ፈጥኖ መድረስ እንደሚገባ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ቦና ማብራሪያ፤ አሁን የምንጠቀመው የተፈጥሮ ሀብት ዘላቂ ባለመሆኑ ተንከባክበን ለቀጣዩ ትውልድ ካላስረከብነው የጤና ችግሩም ሆነ የተፈጥሮ ሀብት ለጋስነት ይጠፋል። ስለሆነም ችግሩን በፍጥነት ለመቅረፍ በየጊዜው ችግኝ ተከላ ማካሄድና መንከባከብም እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአካባቢ፣የደንና ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአካባቢ ሕጎች ተከባሪነት ዳይሬክተር አቶ መሀሪ ወንድማገኝ በጥናታቸው እንዳመላከቱት፤ በአየር ብክለት ምክንያት በርካታ የጤና ችግሮች እየታዩ ናቸው። በተለይም በአሁኑ ወቅት ከተላላፊ በሽታዎች በላይ ግዝፈት ያለው ችግር እያስከተሉ ይገኛሉ። ስለሆነም በጤና መታወኩ ከዚህ የበለጠ እንዳይሆን ብክለቱን መከላከል ላይ መስራት ይገባል።
በአየር ብክለት ዙሪያ ከሞላ ጎደል የሕግ ክፍተት እንደሌለ የሚያነሱት አቶ መሃሪ፤ የወጡ ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት በመኖሩ በሰው ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር እየተፈጠረ ነው። ስለሆነም ብክለት እንዳይጨምር ማድረጉ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2011
ሞገስ ፀጋዬ