አዲስ አበባ፡- በወላይታ ዞን አስተዳደር በዲግሪና በዲፕሎማ ተመርቀው የሚገኙ 90 ሺ ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማሰማራት የተለያየ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደጋቶ ኩንቤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በዞኑ 90ሺ ወጣት በዲግሪና በዲፕሎማ ተመርቆና ሥራ ሳያገኝ መቆየቱ በዞኑም ሆነ በአገር ላይ ሊያመጣ የሚችለው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ስለሆነም ዞኑ ይህንን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል። በተለይም የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት በቀላሉ ሥራ የሚያገኙበትን ሁኔታ ከማመቻቸት አንጻር በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል።
በዞኑ የወላይታ ልማት አብዮት በማወጅ እየተሰራ እንደሆነ የገለጹት አቶ ደጋቶ፤ በልማቱ በዛ ያሉ የመካከለኛ ልማት ማዕከሎች ተከፍተዋል።
በተመሳሳይ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን በማሳተፍ የሥራ አማራጭ ጥናት መደረጉን ጠቅሰው፣ ይህም ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በማቅረብ ማን በምን ቢሰራ ውጤታማ እንደሚሆን መለየቱን ተናግረዋል። ጥሩ ልማት ሰርተዋል የሚባሉ አካባቢዎችንም በመጎብኘት የልምድ ቅመራ መደረጉንም አንስተዋል።
«ሥራ አጥ ተብለው የተለዩ ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ በርካታ ተቋማትን በመክፈት በልማት እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል» ያሉት አቶ ደጋቶ፤ ለመንግሥት፣ ለባለሀብትና ለማህበረሰቡ በማለት የሥራ ድርሻ መሰጠቱን ተናግረዋል። በተለይ ከመንግሥት በላይ ባለሀብቱ ብዙ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይታወቃልና ባለሀብቱ ወደ ወላይታ ሲመጣ ምን ላይ ቢሰማራ ውጤታማ ይሆናል የሚለውን ለማወቅ የአዋጭነት ጥናት መደረጉን ተናግረዋል።
በዞኑ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ የተለየ አማራጭ እያሰናዳን ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ወደ ወላይታ ዞን የሚመጡ ባለሀብቶች በተለይ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ በእርሻ ልማት፣ የተለያዩ ሞሎችን በመገንባት፣ ለቱሪስት መናኸሪያ የሆነችውን ከተማ መጥቀምና ራሳቸውንም ውጤታማ ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ባለሀብቱ በፈለገበት ዘርፍ የት ቦታ ላይ ማልማት እንደሚችል የሚያሳይ ሰነድ አዘጋጅተን እየጠበቅን ነው የሚሉት አቶ ደጋቶ፤ እስከዛሬ ባለሀብቱ ሲመጣ በመልካም አስተዳደር እጦት ብዛት የሚንገላታበት ነገር እንዲቀርም ብዙ ነገሮች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ደጋቶ ገለጻ፤ ኢንቨስተር ነጋዴ ነው። ነጋዴ ደግሞ ሰዓት ገንዘቡ ነው። እናም ቢሮ ላይ መጥቶ በቢሮክራሲው ረጅም ሰዓት የሚጠፋበት ከሆነ ሥራውን ሊያከናውን አይችልምና ይህንን ላለማድረግ እያንዳንዱ የመንግሥት አካል ኃላፊነቱን ወስዷል። ባለሀብቱ ለሚያቀርበው የኢንቨስትመንት ጥያቄ ፈጣን እና ቅን አገልግሎት ለመስጠት በራችን ክፍት ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው