በጣሊያን ወራሪ እብሪት ተሸናፊነትና በጀግኖች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ድል አድራጊነት የተጠናቀቀው የዓድዋ ድል ድፍን 128 ዓመታትን አስቆጠረ። የታሪክ ሰነዶችም ለትውልድ ‹‹የሰው ልጆችን እኩልነት የበየነ፤ የነጭና የጥቁር የበላይነት ግንብ ያፈረሰ ድል ከወደ ኢትዮጵያ የዓድዋ ተራሮች ተመዘገበ›› በማለት የዓድዋን ድል ከተቡ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ትውልድ ከታላቁ የዓድዋ ድል ብዙ ቁምነገሮችን ተምሯል። በየዘመኑ የነበሩ የማኅበረሰቡ መሪዎች፣ ተፅእኖ ፈጣሪዎች፣ መምህራን ዓድዋን የሰው ልጅ የስብእና መለኪያ፣ የፍትህ ሚዛን፣ የነፃነት ምሳሌ አድርገው ትውልድ እንዲማር መክረዋል። ዛሬም በተመሳሳይ ዓድዋን በመዘከር መጪው ትውልዱ አያሌ ቁምነገር እንዲጨብጥ፣ የአባቶቹን ታሪክ ጠንቅቆ እንዲያውቅ የሚሞክሩ በርካቶች ናቸው። ከእነዚህ መካከል የስነ ጥበብ ባለሙያዎች (ሰዓሊያ) ይገኙበታል።
ሕብር የሰዓሊያን ቡድን ይባላል። በ14 ወጣት ሰዓሊያን ከስድስት ዓመት በፊት የተመሰረተ ነው። የስዕል ስራዎቻቸውን በዓድዋ ድል ላይ በማድረግ ተተኪው ትውልድ የአባቶቹን ገድልና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በጥበብ እየተዝናና እንዲያውቅ የማድረግ ዓላማን አንግበው ተነስተዋል። በተጨማሪ የዓድዋ ድል በተለያዩ መስኮች ከሚተረከው በተጨማሪ በስዕል አማካኝነት ያልተዘመረላቸውን ኢትዮጵያዊ ጀግኖች በማወደስ፣ ታሪካቸው ቋሚ ቅርስ ሆኖ ለትውልድ እንዲተላለፍ ይሰራሉ።
የዓድዋን ታሪክ በስዕል አማካኝነት ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ ይሻሉ። ይህ ሁነት ቀጣይነት ኖሮት ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን ለትውልድ ለማሻገር፤ ሕብር የስነ ጥበብ ማዕከል በማቋቋምና ኢትዮጵያዊነት ሁሌም እንዲዘመርለት ቀለሙን፣ ማንነቱን፣ ባሕሉን ብሎም ወጉን ጠብቆ የትውልድ መኩሪያና መመኪያ እንዲሆን ለማስቻል፤ የዓድዋ ገድል ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ በመሆኑ በስዕል አማካኝነት ተተኪው ትውልድ ገድሉን በሚገባው እንዲረዳው፤ ታሪኩም በስዕል ለመጭው ትውልድ በቋሚ ቅርስነት እንዲተላለፍ በማሰብ እየሰሩ መሆኑን የቡድኑ አባላት ይናገራሉ።
ሰዓሊ አለምሰገድ በኃይሉ ይባላል። የሕብር የሰዓሊያን ቡድን አባል ነው። ባለፉት ስድስት ዓመታት በልዩ ልዩ ቦታዎች በተካሄደው የዝከረ አድዋ አውደ ርዕይ ላይ ተወዳጅ ስራዎችን አቅርቧል። አርቲስቱ በስዕል ስራዎቹ በተለየ በቅርፅ፣ ቀለማት፣ እንዲሁም በእይታ ላይ የኢትዮጵያን አሳሳል ዘይቤ ወደ ዘመናዊው ስልት ለማሻሻል በርከት ያሉ አስተዋፅዎችን ማበርከት ችሏል።
አለምሰገድ ከሙሉ ጊዜ የስቱዲዮ ሰዓሊነቱ ባሻገር የተለያዩ ሰብአዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው የሚሰሩ ድርጅቶች ጋርም ሰርቷል። የአማኑኤል የአእምሮ ሕክምና ተቋምን ማንሳት ይቻላል፡፡ በዚህ ተቋም ውስጥ ‹‹አርት ቴራፒ›› አሊያም በስዕል ሕሙማንን ማከም በሚል ፕሮጀክት ውስጥ ተሳታፊ መሆን ችሏል።
አርቲስት አለምሰገድ በርካታ የቡድን አውደ ርዕይ ዝግጅቶች ላይ ተካፍሎ ስራዎቹን ማቅረብ ችሏል። በተለይ የሕብር ሰዓሊያን ቡድን መስራችና አባል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የዘንድሮውን ጨምሮ በስድስቱም አውደ ርዕይ ላይ ተካፋይ እንደሆነ ይገልፃል። ከዚያ ባሻገር ሰዓሊው በብሄራዊ ሙዚየም፣ በዩኤን ዲፒ፣ በአፍሪካ ሕብረት፣ እንዲሁም ከሁለት መቶ በላይ አርቲስቶች በየዓመቱ የሚሳተፉበት ትልቅ አውደ ርዕይ ላይ ተሳታፊ በመሆን ተወዳጅነትን አትርፏል።
‹‹የሕብር የሰዓሊያን ቡድን አድዋን በስዕል ስራዎች ለመዘከር የተመሰረተው 2011 ዓ.ም ላይ ነው›› የሚለው ሰዓሊ ዓለምሰገድ፤ ዘንድሮም በሜትሮፖሊታንት ጋለሪ እስከ መጋቢት አንድ ድረስ የሚቆይ አውደ ርዕይ የካቲት 15 ቀን መክፈቱን ይናገራል። ይህ አውደ ርዕይም ለስድስተኛ ጊዜ መካሄዱን ይገልፃል። 27 ሰዓሊያን የተሳተፉበት አውደ ርዕይ ‹‹1888›› የሚል ርዕስ እንዳለው በመግለፅ፤ በዚህ ቁጥር መሰየም ያስፈለገው ጦርነቱ የተካሄደበትን ጊዜ ለማስታወስ በማሰብ መሆኑን ይናገራል።
ሰዓሊ ዓለም ሰገድ አድዋን በልዩ ሁኔታ የሚዘክረው የስዕል አውደ ርዕይ የቡድኑ አባላት ብቻ የሚሳተፉበት አለመሆኑን ይገልፃል። ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታትም የተለያዩ ሰዓሊዎችን (በሕይወት ያሉትም ሆነ የሌሉትን) አድዋን የሚገልፁ የስዕል ስራዎቻቸውን በመሰብሰብና በመጋበዝ በጋራ መደረጉን ይናገራል።
የአድዋን ድል ታሪኮች በስዕል ለተከታታይ ዓመት በመስራትና ለዕይታ በማብቃት ሕብር የሰዓሊያን ቡድን ስኬታማ ውጤት አስመዝግቧል የሚለው ሰዓሊ አለም ሰገድ፤ እስካሁን ድረስ ለትውልድ የሚሻገሩ፣ በቅርስ መልክ የሚቀመጡና የታሪክ ማስረጃ የሚሆኑ ከ150 በላይ ስዕሎች በቡድኑ አባላትና ተጋባዥ አቅራቢያም መሰራቱን ይገልፃል። ዋና ዓላማውም ለድሉና ለድሉ ባለቤት አርበኞች የሚገባቸውን ክብር መስጠትና ታሪክን በሚገባ መሰነድ መሆኑን አመላክቷል።
‹‹የሕብር ሰዓሊያን ቡድን የሚያዘጋጀው አውደ ርዕይ ላይ በርካታ ታዳሚዎች በየዓመቱ ይሳተፋሉ››የሚለው ሰዓሊ አለምሰገድ፤ ማኅበረሰቡ ከአውደ ርዕይም በላይ የአባቶቹን ታሪክ፣ ጀግንነት፣ በጊዜው የነበራቸውን ፅናትና ሌሎችም ሁነቶችን ለመዘከር ጭምር እንደሚገኝ ይገልፃል። ሰዓሊያኑም ያንን በማሰብ በየዓመቱ በአዳዲስ ስራዎች ተዘጋጅተው ስራዎቻቸውን ይዘው እንደሚመጡ ያስረዳል።
ሰዓሊ ዓለም ሰገድ ስዕል ታሪክን በሚመች መንገድ ለመግለፅና ለትውልዱ ለማስተማር ምቹ የጥበብ ዘርፍ መሆኑን ይናገራል። በስዕል ወደኋላ በመሄድ ሀሳብን ለመግለፅ የሚያስችል እድል ማግኘት እንደሚቻል በመናገርም ይህንን የጥበብ አቅም ተጠቅሞ የአድዋ ድል ከፍ ብሎ እንዲዘከርና ለትውልዱ እንዲተላለፍ የሕብር የሰዓሊያን ቡድን በተነሳሽነት እየሰሩ መሆኑን ያስረዳል።
በተለይ አሁን ያለው ትውልድ እድሜያቸው ገፋ ካለ አርበኞች አሊያም አዛውንቶች ታሪኩን መስማት ወይም መረዳት ቢችልም ቀጣይ ትውልድ ግን ይህንን እድል ላያገኝ ስለሚችል ስዕልና ሌሎች የጥበብ ስራዎችን ተጠቅሞ የአድዋን የድል ታሪክ ማሻገር እንደሚያስፈልግ ያስረዳል። በተለይ በጦርነቱ ወቅት በምስል ያልተቀረፁ አሊያም በፅሁፍ ብቻ የተቀመጡ ታሪኮችን በስዕል በሸራ ላይ ማስፈር ታሪኩን ለመረዳት እንዲሁም በምናብ ወደኋለ መለስ ብሎ ለመቃኘት እድል ይከፍታል የሚለው ሰዓሊ አለምሰገድ፤ ይህንን አጋጣሚ ለመፍጠር ሕብር የሰዓሊያን ቡድን በዓላማ ተነሳሽነት እየሰራ መሆኑን ያነሳል።
ሰዓሊ አለምሰገድ፤ እርሱን ጨምሮ የቡድን አባላቱ በዓድዋ ጦርነት ወቅት የነበሩ ክስተቶችን ቀለምና ሸራቸውን በማዋሃድ ሕያው አድርገው እንደሚሰሩ ይገልፃል። የጦር መሪዎችን፣ አርበኞችን፣ ጦርነቱ የተካሄደበት ዓድዋ ተራሮችን፣ በስድስት ሰዓቱ ውስጥ የተካሄዱ ገድሎችን፣ በልዩ ሁኔታ በታሪክ የሰፈሩ የአርበኞች ገድልን እንዲሁም ልዩ ልዩ የዓድዋ ድል ታሪካዊ ክስተቶችን የሰዓሊያን ቡድኑ በርዕስነት በመምረጥ በየራሳቸው የአሳሳል ዘዴ በሸራዎቻቸው ላይ ያሰፍሯቸዋል።
ለምሳሌ ያህል ሰዓሊ ዓለም ሰገድ በሜትሮ ፖሊታንት ጋለሪ እየተካሄደ ባለው አውደ ርዕይ ላይ እቴጌ ጣይቱን በዋና ርዕሰ ጉዳይነት ይዞ ቀርቧል። ንግስቲቷ በመቀሌ ከተማ የጣሊያን ሰራዊት ውሃ የሚያገኝበትን ስፍራ በማስቆም የወሰዱትን የጦር ስልት እና የአመራር ጥበብ የሚዘክር የስዕል ስራ ለታዳሚያን አቅርቧል።
‹‹1888››በሚል ስያሜን ያገኘው የዘንድሮው የሕብር ሰዓሊያን ቡድን አውደ ርዕይ በተጋባዥነት 16 ሰዓሊያንን አሳትፏል። ከአባላቱ ውስጥ ደግሞ 11 ሰዓሊያን አንድ ወይም ሁለትና ሶስት ስዕሎችን በማቅረብ ተሳታፊ ሆነዋል። ከዚህ ቀደም በነበሩ ዝግጅቶች ላይ ሕፃናት ሰዓሊያን እንዲሳተፉና ልምድ እንዲያገኙ መደረጉን የሚናገረው አለም ሰገድ፤ ዘንድሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይጋበዙ መቅረታቸውን ያነሳል። በቀጣይ ጊዜያት ግን አገር ተረካቢ የሆኑ ታዳጊዎች መሰል ልምድ እንዲኖራቸው እነሱን የሚያሳትፍ ዝግጅት እንደሚካሄድ ይናገራል።
ሰዓሊ አለም ሰገድ ሕብር የሰዓሊያን ቡድን አባላት ይህንን አውደ ርዕይ ከዚህም በተሻለ በማሳደግ ዓድዋን እና ጀግኖች አርበኞች ያስመዘገቡትን ድል ለመዘከር እንደሚሰሩ ይናገራል። ቡድኑ ከዓድዋ ድል ባሻገር ‹‹ውብ ኢትዮጵያ›› የሚል ስያሜ ያለው አውደ ርዕይ ለሁለት ጊዜያት ማዘጋጀታቸውን ገልፆ፤ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የሚያደርጉ፣ ታሪክን የሚዘክሩና ለትውልድ የሚያሻገሩ በርካታ አውደ ርዕይዎችን በጥራትም በብዛትም ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራል።
እንደ መውጫ
ታላቁ የጥቁር ሕዝብ ድል ዓድዋ የጀመረው ከጦርነቱ በፊት ሕዝቡ የንጉሰ ነገስቱን ጥሪ ሰምቶ ከጫፍ ጫፍ በተመመበት ዕለት ነው። አዋጁም ገና ከመነሻው ላይ የድል አድራጊነት መንፈስ እንደደረበበት የሚያመላክት የክተት አዋጅ የተላለፈበት ነው። ይህን ታላቅ ገድል እና ስነ ልቦና ለትውልድ ማጋባት ያስፈልጋል። ለዚህ ሁነኛ መንገድ ደግሞ የጥበብ ስራዎች ናቸው።
የካቲት ታላላቅ ገድሎች የተፈጸሙበትና አንፀባራቂ ድሎች የተመዘገቡበት ወር ነው። የካቲት ወር ለኢትዮጵያውያን፣ ለመላው አፍሪቃ ብሎም ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ድል በደማቁ የታተመበት የአድዋ ድል የተበሰረበት ወር ነው። በመሆኑም በተለያዩ ሙያ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በየሙያዎቻቸው የዓድዋን ድል በተለያዩ ክንውኖች በድምቀት ሲያከብሩት ይገባል። የዘንድሮው 128ኛው ዓመት የዓድዋ ድልም በዛሬዋ እለት በዚህ መንፈስ ሊከበር ይገባል፡፡
ሕብር ሰዓሊያን ቡድን ‹‹ የኛ የክተት አዋጅ አባቶች ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸው ከስክሰው ያቆዩንን ሀገር ፈጣሪ የቸረንን ጥበብ ተጠቅመን ታሪካቸውን ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ ጥሪ ነው›› በማለት በየዓመቱ ለተከታታይ ስድስት ጊዜያት ስራዎቻቸውን ለታዳሚያን አቅርበዋል። ዋና ዓላማቸውም የዓድዋ ገድል ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ በመሆኑ በስዕል አማካኝነት ተተኪው ትውልድ ገድሉን በሚገባው እንዲረዳው ታሪኩም በስዕል ለመጭው ትውልድ በቋሚ ቅርስነት እንዲተላለፍ በማሰብ መሆኑን ገልፀውልናል። የዝግጅት ክፍላችንም ‹‹1888›› የመሰሉ ዓድዋን ያከበሩ የስነ ጥበብ አውደ ርዕይ እንዲበዙ እየተመኘን በዚሁ አበቃን። ሰላም !!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም