ዓድዋን ያነበሩ እና ያደመቁ ጥበባት

ኪነ ጥበብ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው ከመሆኑ አንጻር የአንዲት አገር ሕዝብ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች የዛችን አገር ምንነት ገላጭ ናቸው ፡፡ ሃያል የሚባሉ አገራት ገናናነትን ያገኙት በአብዛኛው በኪነ ጥበብ ስራዎቻቸው ራሳቸውን መግለጥ በመቻላቸው ነው ፡፡ ለምሳሌ አሜሪካና ህንድን የምናደንቃቸው፤ አሜሪካም ወይም ህንድ ሄደን አይደለም፤ የአገራቸውን ባሕልና ታሪክ በመኖር አውቀነው አይደለም፤ በኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸው (በተለይም በፊልሞቻቸው) ነው፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ፤ አብዛኛው ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን በኪነ ጥበብ ይገለጻሉ፤ ዘፈኑ፣ እንጉርጉሮው፣ ፉከራው፣ ቀረርቶው ..ወዘተ የዚሁ እውነታ መገለጫ ናቸው፡፡ ለዛሬው ግን የአድዋ 128 ዓመት በዓልን በማስመልከት እለቱን በሚመለከቱ የጥበብ ሥራዎች ለማየት እሞክራለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የኖረች አገር መሆኗን ዓለም ያውቃል፡፡ ከእነዚህ የጀግንነት መገለጫዎቿ አንዱ ደግሞ የዓድዋ ድል ነው። በርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ጀግንነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርዱ ሲወራረዱ ከመጡ የስነ ቃል ትውፊቶች መረዳት እንችላለን፡፡ ይህ ከዓድዋ በፊትም ሆነ ከዓድዋ በኋላ የነበረና ያለ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው፡፡

የዓድዋን ድል የተመለከቱ በርካታ የኪነ ጥበብ ሥራዎች አሉ፡፡ የመድረክ ቴአትሮች፤ ፊልሞች አሉ፡፡ በአብዛኛው ግን የቃል ግጥሞችና የመድብል ግጥሞች ናቸው። እነዚህ ዓድዋን የተመለከቱ የኪነ ጥበብ ሥራዎች በዓድዋ ጦርነት ወቅትና ከጦርነቱ በኋላ ኩራትን ለመግለጽ የተሰነኙ ናቸው፡፡

አንዳንዶቹ በጦርነቱ ወቅት የጦርነቱ ተሳታፊዎች የገጠሟቸው ናቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በዚያው በጦርነቱ ወቅት ሕዝቡ አርበኞችን ለማበረታታትና የደስታ ስሜቱን ለመግለጽ የገጠማቸው ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ ታዋቂ ድምጻውያን የዓድዋን ድል ለማወደስ የዘፈኗቸው ናቸው፡፡ በወቅቱ ከነበሩት እንጀምር፡፡

አንዳንዶቹ በቅኔ የሚነገሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንዱ ቅኔ እንዲህ የሚል ነበር፡፡

እስኪ ለጣሊያኖች መዲሃኒት ስጧቸው

የሚያስቀምጥ ሳይሆን የሚያስመልሳቸው

የዚህን ግጥም ትርጉም በወቅቱ ዓውድ እንረዳው፡፡ ዘመናዊ ሕክምና ባልነበረበት በዚያ ዘመን ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉት ከቅጠላ ቅጠልና ሥራ ሥር የሚዘጋጁት የባሕል መዲሃኒቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች ሕመምን የሚፈውሱት ወደታች (በዓይነ ምድር መልክ ማለት ነው) እና ወደላይ (በማስመለስ) ነው፡፡

የዚህ ግጥም ሰም ጣሊያኖች ታመዋልና መድሃኒት ስጧቸው ነው፡፡ መድሃኒቱ ግን በመቀመጥ (በዓይነ ምድር ማለት ነው) ሳይሆን በማስመለስ (በአፍ) የሚፈውስ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ዋናው ትርጉም ያለው ግን ወርቁ ላይ ነው፡፡

ጣሊያኖች ታመዋል፡፡ ጤነኛ ቢሆኑ ኖሮ እንደ ኢትዮጵያውያን አይነት ጀግና ሕዝብ እንወራለን ብለው አያስቡትም ነበር፡፡ የእነዚህ ሰዎች መድሃኒት ቅጠላ ቅጠልና ሥራ ሥር ሳይሆን፣ ጎራዴና ጥይት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቀመጡ ሳይሆን በመጡበት እግራቸው ወደ አገራቸው የሚመልስ መሆን አለበት የሚል ነው።

ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ያሻትን በመኪና ያሻትን በፈረስ እየሄደች ነበር። የጣሊያን ወታደሮችም ሰውነታቸው ከኢትዮጵያ ተዋጊዎች ጋር ሲነጻጸር የለሰለሰና ያማረባቸው ናቸው፡፡ ዳሩ ግን ምን ዋጋ አለው እንዲህ ሆነ!

የሞሶሎኒ አሽከሮች ሁሉም ሎጋ ሎጋ

ሲመጡ በፈረስ ሲመለሱ በአልጋ

እንግዲህ በፈረስ ሲንሸራሸር የነበረ ሸበላ የጣሊያን ጦረኛ ፈረሱን መቀማቱ ሳያንስ በእግሩ እንኳን እንዳይሄድ በጥይት አንካሳ አደረጉት ማለት ነው፡፡ የሞተው ሞቶ የቆሰለውም በአልጋ እንዲወሰድ ተደረገ ማለት ነው፡፡ ይህ ስንኝ ግን ለዓድዋ ሳይሆን ለአምስት ዓመቱ የጣሊያን የወረራ ሙከራ የተፎከረ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ሞሶሎኒ የጣሊያን መሪ የሆነው ከዓድዋ ድል 27 ዓመታት በኋላ በ1915 ዓ.ም (እ.አ.አ 1922) ነው፡፡

የዓድዋ ድል አስገራሚ ታሪክ የሆነው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ያላት ጣሊያን ‹‹ኋላ ቀር›› እያሉ በሚሳለቁባት ኢትዮጵያ መሸነፏ ነው፡፡ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀ ወታደር ባኅላዊ ጎራዴና ጋሻ በያዘ ወታደር መማረኩ ነው፡፡ ጣሊያን በራሱ መሳሪያ መወጋቱ ነው። ራሱ ይዞት በመጣው መሳሪያ ተገደለ፡፡ ለዚህም ነው የወቅቱ ከያኒያን እንዲህ ያሉት፡፡

በሰራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ

ተፈፀመ ጣሊያን ሐበሻ እንዳይደርስ

በዓድዋ ጦርነት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ጀግኖች ተወድሰዋል፡፡ እነዚህን ጀግኖች በማወደስ ለሌሎች ጀግኖች ተጨማሪ ሞራል መስጠት ተችሏል፡፡ ከእነዚህም አንዱ ራስ አሉላ አባ ነጋ ናቸው፡፡ ራስ አሉላ አባ ነጋ በርካታ የጦር ገድል ነው ያላቸው፡፡ በኩፊት፣ በዶጋሊ፣ በጉንደት፣ በጉርዓ፣ በሰሀጢ፣ በመተማ እና በዓድዋ ከወራሪዎች ጋር ተፋልመው አንፀባራቂ ድሎችን ያስመዘገቡት ናቸው፡፡ በዚህ ጀግንነታቸው እንዲህ ተብሎላቸዋል፡፡

ጣሊያን ሰሀጢ ላይ እግሩን ቢዘረጋ

እንደ ገብስ ቆላው አሉላ አባ ነጋ

ይቺኛዋ ስንኝ ዓድዋ በመጣ ቁጥር በየመድረኩና በየመገናኛ ብዙኃኑ ተደጋግማ ትነገር እንጂ ስለአሉላ አባ ነጋ ሌሎች የውዳሴ ግጥሞችም አሉ፡፡

ዮሐንስ መብቱን ላሉላ ቢሰጠው

እንደ ቀትር እሳት ቱርክን ገላመጠው

ጣልያንም ወደቀ እያንቀጠቀጠው

አጭዶና ከምሮ እንደ ገብስ አሰጣው!

አሉላ አባነጋ የደጋ ላይ ኮሶ

በጥላው ያደክማል እንኳንስ ተኩሶ!

አሉላ አባነጋ ካስመራ ቢነሳ

ቢቸግረው ጣሊያን አለ ፎርሳ ፎርሳ፡፡

ጣሊያን በሀገርህ አልሰማህም ወሬ?

የበዝብዞች አሽከር የነ ሞት አይፈሬ

ዘለው ጉብ ይላሉ እንደ ጎፈር አውሬ!

ሌላኛው ጀግና ደግሞ ፊት አውራሪ ገበየሁ ናቸው፡፡ ፊት አውራሪ ገበየሁ በጦርነት መሃል እየገቡ የሚፎክሩ ነበሩ፡፡ በዚህ ጀግንነታቸው ጣሊያንን ሲያርበደብዱ ነበርና እንዲህ ተባለላቸው፡፡

የዓድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው

ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው!

ፊት አውራሪ ገበየሁ በተፋፋመ ጦርነት ውስጥ ገብተው ሲዋጉ በጣሊያን መድፍ ተገደሉ፡፡ ዳሩ ግን ጣሊያን ኢትዮጵያውያንን ማሸነፍ አልቻለም፡፡ ቆራጥ ጀግኖች እነ ባልቻ ሳፎ (ባልቻ አባ ነፍሶ) ሃይለኛ የመድፍ ተኳሽ ሆነው ጣሊያንን አጥረገረጉት፡፡ ወዲያውም እንዲህ ተባለ፡፡

ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ

መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ!

የዓድዋ በዓል በመጣ ቁጥር የሚታወሱት ሌሎች ግጥሞች ደግሞ ራሳቸው ንጉሱን አጼ ምኒልክን የተመለከቱት ናቸው፡፡ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ በብልህነታቸው፣ በጀግንነታቸው፣ በአጠቃላይ በነበራቸው የአመራር ብቃት ኢትዮጵያን ከጣሊያን ወረራ ታድገዋል። እነሆ ብቸኛዋ በቅኝ ያልተገዛች የአፍሪካ ነፃ ሀገር እየተባለች እንድትጠራ አደረጉ። ሕዝቦቿ በራሳቸው ባሕልና ወግ እንዲኮሩ አደረጉ፡፡ ለዚህም ነው እንዲህ የተባለው፡፡

ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ

ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ ሐበሻ

እስኪ አሁን ደግሞ በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርዱ ሲወራረዱ ከመጡት እንውጣና ወደ ሌሎች ሥራዎች እንሂድ፡፡ እነዚህኞቹ ባለቤት ያላቸው ናቸው፡፡ በዓድዋ ታሪክ ውስጣቸው ሀሴት ያደረገ ከያኒያን የሰሯቸው ናቸው፡፡ ገጣሚያንና ድምጻውያን ማለት ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የዓድዋ በዓል በመጣ ቁጥር ሁላችንም ከዓድዋ እኩል የምናውቃት ድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ናት፡፡

የጂጂ የዓድዋ ዘፈን እያንዳንዷ ስንኝ የምትተነተን ናት፡፡ ጥልቅ መልዕክት ያለው ነው፡፡ ‹‹ምን ማለት ይሆን?›› ብለን ስናስብ እያደር እየተገለጠልን የሚሄድና የሚመስጥ መልዕክት ያለው ነው፡፡ እስኪ ከስንኞቹ ውስጥ ‹‹ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን›› የሚለውን ቃል እንውሰድ፡፡ አንድ ጀግና ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ አልሞትም ብሎ አይደለም፡፡ የሚሄደው ወገኑን ለማዳን ነው፡፡ ራሱ ሞቶ ሌላውን ማዳን ማለት ነው፡፡

ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን

ሰውን ሲያከብር

በደህንነት በፍቅር በክብር ተጠርቶ

በክብር ይሄዳል ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ

የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነፃነት

ሰው ተከፍሎበታል ከደም እና ከአጥንት

አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትላንት

መቼ ተነሱና የወዳደቁት።

‹‹ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት›› አዎ! ይህ የዓድዋ ድል የተገኘው በልመና ወይም በግዥ አይደለም፡፡ በሰው ሕይወት ነው የተገኘው፤ የብዙዎች አጥንት ተከስክሶበትና ደም ፈሶበት ነው፡፡ ይህ የድል ታሪክ ዛሬም ነገም ይወደሳል፤ የጀግኖቻችን ውለታ ነውና! መቼ ተነሱና ነው የምንተወው?

እነዚህ ተወዳጅ አርቲስቶች በዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቻቸው ጀግኖቻችን እንዳይረሱ አድርገዋል፡፡ ሥራዎቻቸውን ለትውልድ አስተላልፈዋል፡፡ ከእነዚህ ዘመን ተሻጋሪ ድምጻውያን አንዱ ተሾመ አሰግድ ነው። ‹‹እንዲያው ዘራፌዋ›› በሚለው ዜማው ጀግኖችን እንዲህ ያስታውሳል፡፡

መቅደላ አፋፉ ላይ ጎበዝ ወንድ ሆነበት

በመተማም ጎራ ጀግኖች አንድ ሆኑበት

እንዳይሞት ሆነ እንጂ ስሙን እንዳይቀብሩት

የመቅደላን መንደር የዶጋሊን ሜዳ

የማይጨው ዓድዋን የመተማን ሜዳ

ተዳኘበት እንጂ መች ዋኘበት ባንዳ

አፄ ቴዎድሮስ አባ ታጠቅ ካሳ

እምዬ ምኒልክ ጥራኝ የእኔ አንበሳ

በደም ታዋጋለህ በአካል ባትነሳ!

ተሾመ አሰግድ በዚህ ዜማው ኢትዮጵያ ጥንትም የጀግኖች አገር እንደሆነች ይናገራል። አጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ዮሐንስ፣ አጼ ምኒልክ እና የጦር አርበኞችን ያወድሳል፡፡ ድል ያደረጉባቸውን ቦታዎች ይጠቅሳል፡፡ ጠላት ከእነዚህ ድሎች መማር እንዳለበት ይነግረናል፡፡

ሌላኛዋ ከያኒ ራሄል ዮሐንስ ናት፡፡ ‹‹ምኒልክ›› በሚለው ዜማዋ እንዲህ ትላለች፡፡

ብወጣው በእግሬ እንጦጦን

አላገኝም ወይ ጣይቱን

ፍቅሩን አብዝቶ ያለ ልክ

ዛሬም ይባላል ምኒልክ

እስኪ ወደ አንኮበር ተነሱ እንዝለቀው

እኛ አናየውም ወይ ምኒልክ ቢለቀው

የጣይቱን ማጀት ቢፈልጉት እዛ

አይጠፋም እስከ አሁን የጥጃ መዓዛ

እስኪ አንተ ሰውየ እንደ አባትህ ሥራ

ከጓዳ እንድትቀዳው ወተቱን በእንስራ

ያገኘህ እንደሆን ግቢን ከአዲስ አባ

የደግ አዳራሽ ነው ሰተት ብለህ ግባ

አይቆረቁረውም እንግዳ ደጁን

ገብቶ ይጥገብ እንጂ ሥጋና ጠጁን

ያ ሁሉ ደስታ ፊቴ ይደቀናል

ሰው እንዴት በሄደው ባለፈው ይቀናል

ያ የፍቅር ጊዜ ያ የደስታ ቀን

ደግሞ በአይኔ መጥቷል እፊቴ ሊደቀን

ይህ የራሄል ዮሐንስ ዘፈን የአጼ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን ዘመን ያሳየናል፡፡ ደግነታቸውን ይነግረናል፡፡ ይሄን ደግነታቸውን ልናስታውስላቸው እንደሚገባ ይገልጻል፡፡

‹‹አንኮበር›› በሚለው የገነት ማስረሻ ዜማ ውስጥ ደግሞ ይሄን እናገኛለን፡፡

እሱማ መቼ ጠፋው ብልሃቱ

ከበስተግራው አለች ፀሐይቱ

ደግ ሰው ነበር አመለ ምቹ

ፍቅር መጋቢ ለወገኖቹ

ከእንጦጦ ጋራ ዓድዋ ድረስ

ሰራዊት ይዞ በእግር በፈረስ

ስንት ቀን ይሆን የፈጀበት

ስንት በጋና ስንት ክረምት

ቀና ነው ልበ ቀና

የወገን ቤት ያቀና

አዛኝ ነው አመዛዛኝ

ሃቀኛ ብርቱ መዛኝ

እምየ አባ ዳኛው

በፍቅር የተቃኘው

ቋንቋ ሃይማኖት ሳያግደው

መሃሉን ከዳር ያገናኘው

ሕዝቡን አንድ አርጎ ሄደ ስምሪት

በአንድ ባንዲራ በአንድ ነጋሪት

እምየ ዳኛው ልበ ተራራው

በከዘራ ነው ጦሩን የመራው

ምን ቢባል ምን ቢወራ

ህያው ነው የሱ ሥራ

ያ ቢሄድ ያ ቢመጣ

እሱስ ከልቤ አይውጣ

የጎራዴው ብልጭታ

ጠላትን ድባቅ መታ

አንኮበር ላይ ደገሰው

ዓድዋ ላይ ለኮሰው!

‹‹እሱማ መቼ ጠፋው ብልሃቱ፤ ከበስተግራው አለች ፀሐይቱ›› ይላል የገነት ማስረሻ ዘፈን፡፡ ከበስተግራው ማለት እቴጌ ጣይቱ የአጼ ምኒልክ ሚስት መሆናቸውን ለመግለጽ ነው፤ በልማድ ሚስት ግራ ጎን ተብላ ትጠራለች፡፡ ለአጼ ምኒልክ ስኬት ሁሉ የእቴጌ ጣይቱ ብልህነት እንዳለበት ይነገራል፡፡

‹‹ቋንቋ ሃይማኖት ሳያግደው መሃሉን ከዳር ያገናኘው››፤ የዓድዋ ድል የተገኘው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከጫፍ እስከ ጫፍ ተጠራርተው በመሄድ ነው፡፡ አንድ ልብ፣ አንድ ሀሳብ ሆነው፤ ለአንድ ዓላማ ከአራቱም አቅጣጫ እየተመሙ ሄደው ጠላትን ድባቅ አድርገው መጡ፡፡ አንኮበር ላይ የተደገሰው የዓድዋ ጦርነት ዓድዋ ላይ ተለኮሰ፤ ዓድዋ ላይ የተለኮሰው እሳት ጠላትን ለብልቦ መለሰ፡፡

እቴጌ ጣይቱ ጀግንነትን ከብልህነት ጋር የያዙ ናቸው። በጦርነት ጊዜ ቁጣና ችኩልነት ብቻ እንደማያዋጣ፤ ይልቁንም ብልህነት መኖር እንዳለበት አሳይተዋል፡፡ ይህን የእቴጌ ጣይቱን ብልህነትና ጀግንነት የሚገልጸውን የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ስንኝ መሰናበቻ አድርገነዋል፡፡ ክብር ለጀግኖቻችን!

የቀፎው ንብ ሲቆጣ ስሜቱ

ከፊት ሆና መራችው ንግስቲቱ !

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You