
ዜና ትንታኔ
ላለፉት በርካታ ዓመታት የዓድዋ ድል ለተማሪና ሠራተኞች የዕረፍት ጊዜ፤ ለአንዳንዶች የትርፍ ሰዓት ሥራ ተጨማሪ ገቢ ከመሆን የዘለለ ብዙም ትርጉም እንዳልተሰጠው ይደመጣል። አሁን ግን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የመነቃቃት መንፈስ እያበበ እንደሚገኝም እየተነገረ ይገኛል። ለታሪካዊ ሰዎችና ቦታዎች ተገቢውን ክብር ከመስጠት ባሻገር ድሉን ከጀግኖች አባቶች ከተሰጠው አደራ ጋር ማክበር እንደሚገባ ምሁራን ይገልጻሉ። ለመሆኑ የዓድዋ ድል ለአዲሱ ትውልድ ምን አደራ ሰጠ?
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፀጋዬ ዘለቀ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ የዓድዋ ድል ፓን አፍሪካኒዝምን አሜሪካ ውስጥ ለጀመሩት የበለጠ መነቃቃትን የፈጠረ ነው። የመጀመሪው የፓን አፍሪካ ኮንፈረንስ ተብሎ የሚጠራው በ1900 ላይ የተካሔደው እና በዊሊያም ሔነሪ ሲልቪስተር ስም ለተሰየመው ኮንፈረንስ ድሉ አንዱ ትልቅ ግብዓት ሆኗል።
የዓድዋ ድል በ1919፣ 1921፣1923 እንዲሁም በ1945ም ለተካሔዱት የፓን አፍሪካ ኮንፈረንሶች ሁሉ ትልቅ ሚና ነበረው። በኋላም ከዳያስፖራው በተጨማሪ አፍሪካ ውስጥ ያሉት እነኩዋሜ ኑኩሩማ፣ ጆሞ ኬኒያታ፣ ጁሊየስ ኔሬሬ እና ሌሎችም ተሳትፈው አፍሪካ ከአውሮፓውያን ነፃ እንድትወጣ ሲጠይቁም የዓድዋ ድል አንዱ ግብዓት ሆኗል።
የዓድዋ ድል ጥቁሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኙት አንፀባራቂው ድል ነው የሚሉት የታሪክ ምሁሩ፤ ከዓድዋ ድል በፊትም ሆነ በኋላ ተመሳሳይ እና ተወዳዳሪ በዓድዋ ደረጃ ድል እንዳልተገኘ ይናገራሉ። የዓድዋ ድል ጥቁር ሕዝብ እንደሸቀጥ የሚሸጥበት እና የባሪያ ንግድ የነበረበት፤ ጥቁሮች የበታች ተደርገው አውሮፓዎች አፍሪካን ለመቀራመት የመጡበት እና አብዛኛው አፍሪካ በእነሱ እጅ ውስጥ በወደቀበት ጊዜ የተገኘ ድል በመሆኑ ጥቁሮች በነጮች ላይ ያገኙት የመጀመሪያው ድል መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ተመራማሪው እንደሚያብራሩት፤ የዓድዋ ትሩፋት ብዙ ነው። ሀገርን ወይም ሀገረ መንግሥት በመገንባት ላይ ሚናው ከፍተኛ ነው። ሉዓላዊነትን ማስከበር ከመቻል እና መንግሥትን ከመገንባት አንፃር የተገኘው ትሩፋትም ተጠቃሽ ነው። በሌላ በኩል ዓድዋ ኢትዮጵያውያን የጋራ ትርክት እንዲኖራቸው አድርጓል።
የዓባይ ንጉሶች ሚዲያ ባለቤትና በኢትዮጵያ እውነቶች ላይ ተሟጋች የሆኑት ዑስታዝ ጀማል በሽር ዓድዋ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ብሔሮችና ብሔረሰቦች የጋራ ድል መሆኑን ይገልጻሉ። በወቅቱ በሃሳብ እንኳን የተለያዩ ሰዎች ከውጭ የመጣና የጋራ የሆነ ጠላትን ያሸነፉበትና ድል ያደረጉበት አጋጣሚ ነው። ይህ አጋጣሚ በሚከበርበት ወቅት ውስጡ ካሉት ወሳኝና የማይረሱ ጉዳዮች አንዱና ዋናው አብሮነት መሆኑንም ይናገራሉ። ጠላትን በጋራ የመመከትና በጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮነት እንደሚያስፈልግ ማሳያ የሆነ ድል ነው ይላሉ።
ይህ ለአዲሱ ትውልድ ሌላ አደራ ይዞ የመጣ መሆኑን የሚጠቅሱት ዑስታዝ ጀማል፤ ጠላትን ከመገፍተር ውጪም በሀገሪቷ ላይ ያሉ የጋራ የሆኑ ብዙ የሚሠሩ ጉዳዮች መኖራቸውን አዲሱ ትውልድ ሊማርበት እንደሚገባ ይገልጻሉ። ልክ እንደ ዓባይ ግድብና የባህር ጉዳይ እንዲሁም ድንበር የመጠበቅና ሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ በአብሮነት መቆም ለአዲሱ ትውልድ የተሰጠ አደራ መሆኑንም ያመላክታሉ።
“እንዲህ አይነት የጋራ ጉዳዮች የፖለቲካም፣ የብሔር አልያም የመንግሥት ልዩነቶች ሊያግዱን የሚገቡ አይደሉም። እነዚህን ሁሉ ተሻግረው የሚሄዱ ናቸው” በማለት ነው የሚናገሩት።
“በዓባይ ግድብ ያሰቡት ሌሎች ናቸው። የተገበሩት ሌሎች ናቸው። እያስፈጸሙ ያሉት ሌሎች ናቸው። ይህ ወደፊትም በእንዲህ መልኩ ይቀጥላል። በኢትዮጵያ መሰል ጉዳዮች በርካታ ናቸው። ዓድዋ የእነዚህ ሁሉ የጋራ ጉዳዮች ተምሳሌት ነው። ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ሕዝቦች እንዲሁም ለማንኛውም ነፃነትን ለሚፈልግ አካል በሙሉ ትልቅ ምሳሌ ነው” ይላሉ ዑስታዝ ጀማል።
አንድ ሰው ጎበዝ የሚባለው “አባቴ እንዲህ ነበር ስላለ ብቻ አይደለም፤ የእርሱን ጉብዝና ሊመዝኑ የሚችሉ ተግባራትን ሲያከናውን እንጂ” የሚሉት ዑስታዝ ጀማል፤ ይህ ትውልድ “ አባቶቼ እንዲህ ሠርተው ነበር” ከሚለው ትርክት ባሻገር ከአባቶች የተገኘውን ነገር ትምህርት ወስዶ የራሱን አሻራ ሊያኖር እንደሚገባ ይመክራሉ።
ዑስታዝ ጀማል እንደሚሉት፤ ምን ሠራህ ተብሎ የሠራውን ነገር በተጨባጭ የሚያሳይ ትውልድ ሊፈጠር ይገባል። “ይሄን ሠርተናል ብለና የምንናገርለት ነገርና ኮርተን ለማለፍ መጣር ያስፈልጋል።” ይህ ለአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩም ትውልድ የሚዘከር ይሆናል። የኢትዮጵያን ከፍታና ትልቅነት ሊያሳዩ የሚችሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ ትውልዱ በአብሮነት የመሥራት ሀገራዊ ኃላፊነት አለበት።
በዓባይ ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያን እውነቶች በማሳወቅና በተለይም በአረቡ ዓለም ስለ ግድቡ የሚሞግተው መሐመድ አልአሩሲ እንደሚለው፤ የዓድዋ ድል በኢትዮጵያና በአፍሪካ መካከል ያለውን አንድነት ያጸና ነው። በወቅቱ ብዙ ልዩነቶች ነበሩ። ነገር ግን ሁሉም ዜጋ ልዩነቱን ትቶ ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም ለሀገር ህልውና ቆሟል። የጋራ ጉዳይ ለሆነው የሀገር ጥቅም አብሮነት ታይቶበታል። ልዩነቶች ስለ አንድነትና አብሮነት ከማሰብ አላገዳቸውም ነበር። ሁሉም ሀገሩን ከልዩነቱ በላይ አስቀምጦ ነው ጠላትን ለመፋለም የተነሳው። ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህል በአንድነት ላይ እንደማይደራደር ያሳየ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በየትኛውም ዘመን ለሀገር አስፈላጊ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ከልዩነት ይልቅ አንድነትና አብሮነትን ያስቀድማል ያለው መሐመድ አልአሩሲ፤ ምንም እንኳን መልከ ብዙ ችግሮችና ልዩነቶች ቢኖሩም ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ከግላዊ ጥቅም ይልቅ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የማስቀደም የቆየ ታሪክ ያለው ሕዝብ መሆኑንም ይጠቅሳል።
እንደ ቀደሙት አባቶች ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ልዩነት ሳይበግረው ለሀገር መስዋዕትነትን መክፈል፣ ችግሮችን በጋራ መጋፈጥና የሀገር ጥቅምን ማስከበር ላይ በጋራ መሥራት እንዳለበት ይመክራል። “ይህን አደራ ሲወጣ ነው እንደ ዓድዋ ጀግኖች ታሪክ የሚዘክረው” ብሏል።
ቀደምት አባቶች ለሀገር ህልውና ተዋድቀው እንዳስከበሩን፤ ሁሉም ሀገሩ ሰላም እንድትሆን መተባበርና በአንድነት መቆም እንዳለበት፤ ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤት ሀገራት በሁሉም መስክ ተምሳሌት ሆና እንድትቀጥል አዲሱ ትውልድ የዓድዋ አደራ እንዳለበትም ገልጿል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም