አምስተኛው አገር አቀፍ የግዕዝ ጉባዔ ”ግዕዝና ስነ ፈውስ” በሚል መሪ ቃል ዛሬ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል።
በጉባዔው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት ግዕዝ በርካታ ጥበቦችና ምስጢራት የተፃፈበት ቋንቋ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ግን ጥቅም ላይ አልዋለም ብለዋል።
ቋንቋውን ለመጠቀምና ለማሳደግ እየተካሄዱ ያሉ የግዕዝ ጉባዔዎች ድርሻ ከፍተኛ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የዘንድሮው ጉባዔ ግዕዝ ከስነ ፈውስ ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝንት የሚዳሰስበት በመሆኑ ከቀደሙት አራት ጉባኤዎች ለየት ያደርገዋል ብለዋል።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ህይወት በበኩላቸው የዘንድሮው ጉባኤ በስነፈውስ ላይ ትኩረት ማድረጉ ባህላዊውን የህክምና ስርዐት ከዘመናዊ ጋር በማዋሀድ ጥናትና ምርምሮችን በሰፊው ለማካሄድ እንደሚረዳና በጉባዔው የሚቀርቡ ፅሁፎችን ዩኒቨርስቲው በግብዐትነት እንደሚጠቀምባቸው ተናግረዋል።
ጉባዔውን የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፅሀፍት ኤጀንሲ እና የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያዘጋጁት ሲሆን በግዕዝና ስነፈውስ ዙሪያ የተለያዩ ፅሁፎች እየቀረቡ ውይይት ይደረግባቸዋል፤ ኤግዚቢሽኖች፣ ዝማሬዎችና ግጥሞችም የዝግጅቱ አካል ናቸው።
በድልነሳ ምንውየለት