የዓድዋን ድል መሠረት አድርጎ ነገ የራስን ታሪክ ለመስራት

የዓድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደምና አጥንቱን የገበረበት ነው። የዓድዋ ድል ለአሁኑ ትውልድ አብሮነትን፣ ሕብረትን፣ መደማመጥንና በጋራ መቆምን ያስተምራል። ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በባህልና በቋንቋ ወዘተ ሊለያዩ ይችላሉ፤ ነገር ግን የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ዘመናት የተሻገረና ሌላው ዓለም ትምህርት የወሰደበት የአብሮነት እሴት አላቸው። ይህንን መልካም እሴት ሊንከባከቡትና ጠብቀው ሊያቆዩት ይገባል።

ሀገራችን አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት በአንድ በኩል በውስጥና በውጭ ኃይሎች ሴራ አገርን የማተራመስ በሌላ በኩል ደግሞ የማፍረስ ጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ የታየበት፤ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ጋር ከፍተኛ ግብግብ ውስጥ የተገባበት ነው። በዚህ ወቅት አገርን መታደግ የሚቻለው በአንድነት በመቆም ብቻ ነው። ኢትዮጵያን ከወቅታዊ ፈተናዎች መታደግ፣ የበለጸገችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች አገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ከዓድዋ ድል የምንማረው ሌላኛው ገጽታ ነው።

አሁን የተጋረጡብንን ችግሮች ልንፈታ የምንችለው ስንደማመጥና አንድ ሆነን ስንቆም ብቻ ነው። አለበለዚያ ግን የሚገጥሙን ማናቸውም ፈተናዎች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሊያንበረክኩን እንደሚችሉ ግልጽ ነው። “ካልተደራጀ ትልቅ ሀገር የተደራጀች ትንሽ መንደር ትልቅ ስራ ትሰራለች” እንደሚባለው ችግሮቻችንን ለመወጣት በአንድነት አብሮ መቆም ምን ያህል ትርጉም እንዳለው የዓድዋ ድል ህያው ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ ዜጎቿ በአንድነት የሰሯት፣ አንድነታቸውን ያስመሰከሩባት፣ በጥረታቸው ነፃነቷን ጠብቀው ለትውልዱ ያቆዩዋት አገር ነች። ዓድዋ የአባቶችን ታሪክ ተገንዝቦ፤ ያወረሱንን መልካም ገጸ በረከት ማስቀጠልና ለቀጣዩ ማስተላለፍ የሚችል ትውልድ መሆን እንደሚገባ ያስታውሰናል። የዓድዋ ድል ስኬታማ የሆነው በመላ ኢትዮጵያውያን የአንድነት መንፈስ በመሆኑ አሁንም ሆነ ወደፊት የአገራችንን እድገትና ብልጽግና የምናረጋግጠው አንድ ላይ በመቆም ብቻ ነው።

የአገር ጉዳይ ሲነሳ በየዘመናቱ እየመጣ የሚሄድ ትውልድ የራሱን ታሪክ ሠርቶ ያልፋል። የሚሠራው ታሪክም ዘመኑ በሚጠይቀው ዕውቀት፣ ዕሳቤ፣ የአገር ተጨባጭ ሁኔታና ዓለም አቀፋዊ ጫና ጭምር ነው። በዚያን ዘመን የነበሩ ሰዎች እንደተባለውም በተገለጸላቸው መጠን ታሪክ ሠርተው አልፈዋል። የአገርን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ጋር በመፋለም አስከብረው ነፃ አገር ለመጪው ትውልድ አስረክበዋል።

እንደሚታወቀው አውሮፓውያን በበርሊን ኮንፈረንስ በወሰኑት መሠረት አፍሪካን ዕጣ ተጣጥለው እንደ ቅርጫ ሲቃረጡ፣ ብቻዋን ቅኝ ገዥዎችን ተፋልማ ያልተደፈረች አገር ኢትዮጵያ ነበረች። ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ይህንን በመሰለ የጀግንነት ተጋድሎ የሚያኮራ ታሪክ ሠርተው ሲያልፉ፣ ተከታዩ ትውልድ እንደተባለው በጎደለው እየሞላ የራሱን ታሪክ መሥራት ይገባው ነበር። የሚሠራው ታሪክ አኩሪ እንጂ አንገት የሚያስደፋ እንዳይሆንም መጠንቀቅ ነበረበት። ከዚያ ውጪ ትናንት የጎደለውን ወይም የተዛነፈውን ዛሬ እየሞሉና እያስተካከሉ በዕድገት መራመድ ሲገባ፣ የትናንቱ ትርክት ላይ ተቸንክሮ እግርን መጎተት ፋይዳ ቢስ ነው። ለዘመኑ የዕድገት ደረጃም አይመጥንም።

አሁን ላይ እዚህም እዚያም የፖለቲካ ስልጣንና የኢኮኖሚ የበላይነት ለመያዝ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች፣ ወጣቶችን ያልተገባ ሳጥን ውስጥ በመክተት የኢትዮጵያ ሰላም እንዲደፈርስ ጥረት ማድረጋቸው የቀደመውን አርበኞች ታሪክ መዘንጋት ይሆናል። አገሪቱ አሁን የገጠማት ፈተና በአድዋ ጦርነት ከገጠማት ችግር አይበልጥም ወጣቶች የታሪክ ባለእዳ መሆናቸውን ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን ከተወጡም እዳው ገብስ ነው።

የዓድዋ ድል ትውፊት ከአገር አልፎ ዓለም አቀፋዊ ሲሆን፤ በጥንት አባቶችና እናቶች የደም ዋጋ የተገኘው የዓድዋ ድል የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ መሆኑ ሁሉም ይህንን ታሪክ ሊዘክረው ይገባል። የኢትዮጵያውያንን የጋራ የድል ታሪክ ወደ ጎን በመተው ዛሬ ላይ የጎጠኝነት ዝንባሌዎች እንዲፈጠሩና አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከተው ማድረግ ተገቢ ባለመሆኑም በተለይ ወጣቱ ለግል ጥቅማቸው ብለው ትልቁን ታሪካዊና አገራዊ ስዕል እንዳያይ ከሚያደርጉት አካላት ፖለቲከኞች በሚቀዱለት ቦይ ውስጥ መፍሰስ የለበትም። በመሆኑም ጀግኖች አባቶችና እናቶች ለአገራቸው ሲሉ ከፈፀሙት አኩሪ ገድል ብዙ ልንማር ይገባል።

ኢትዮጵያ በየጊዜው የሚነሱባት ጠላቶቿን እንድትመክትና ሽንፈት እንዲቀዳጁ ምክንያት የሆነው፣ ሕዝቦቿ ለሰንደቅ ዓላማቸው ክብር በአንድነት የሚታገሉባት አገር በመሆኗ ነው፤ አሁን ላይ የሚስተዋለውን አክራሪ ብሔርተኝነትና ጎጠኝነትን ወደ ጎን በመተው፣ ቅድመ አያቶች የሰሩትን ታሪክ በማወቅ ወቅታዊ ፈተናዎችን በጥበብና በእውቀት ማለፍ ይገባል።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ትምህርት ክፍል ተማሪና የተማሪዎች ሕብረት ፕሬዚደንት የሆነው ወጣት ያሬድ ላቀው እንደሚለው ቤተሰቦቼ ስለ አድዋ ብዙ ነገሮችን ነግረውኛል እኔም ከአንደኛ ደረጃ ትምህርቴ ጀምሮ ዓድዋ የአንድ ብሔር ወይም ጎሳ ድል ሳይሆን፤ የመላው ኢትዮጵያዊ አኩሪ የድል ታሪክ መሆኑን ተምሬያለሁ ይላል።

እንደ ወጣት ያሬድ ገለጻ፤ ኢትዮጵያውያን ለነጭ አንገዛም ብለው በሌላቸው መሳሪያና ቴክኖሎጂ ከዳር እስከዳር ያላቸውን ስንቅና ትጥቅ በመያዝ ታላቁን ፋሽስት ሳያስበው ድል የነሱበት አኩሪ ታሪካችን በመሆኑ እኔም በዚህ ስሜት ውስጥ በመሆን የማከብረው ታላቅ የድል በዓል ነው።

ድልን እንደ አገር ስናገዝፍና ስናከብር ነው ወደሌሎች ድሎች የምናመራው የሚለው ወጣት ያሬድ በተለይም ዓድዋ ከድልነትም ባሻገር የእኛነታችን መገለጫ በመሆኑ አከባበሩም አገራዊ መልክና ቅርጽ ቢኖረው መልካም ስለመሆኑ ያብራራል።

አሁን ባለውና በምናየው ሁኔታ ወጣቶች ዓድዋን ይደግማሉ ማለት ከባድ ነው። ነገር ግን ስራዎች ከተሰሩ ወጣቶች ስለ አገራቸውና ስለታሪካቸው እንዲያውቁ ከተደረገ ወጣቱ ነገን በተሻለ መንገድ አያስብም ወይም ተስፋ ይቆርጣል ማለት እንዳልሆነም በመናገር፤ ነገር ግን እንደ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ ሌሎች ከፍተኛ የትምህርተ ተቋማት ታሪክ ላይ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅባቸው ብሏል።

ሌላው አገር በጣም ትንሽ የሆነ ታሪኩን በትምህርት በጥበብ ስራ ብቻ በተገኘው ነገር በሙሉ በማጉላትና ደጋግሞ በማውራት የዓለም ሕዝብ ጆሮና አይን ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል። በአንጻሩ እኛ ደግሞ ይህንን የሚያክል የድል ታሪክ እያለን እንኳን ሌላውን ለማሳወቅ ለራሳችንም ያወቅነው በጣም ጥቂቱን ነው። በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ እንደ አገር ዓድዋ በትምህርት ስርዓት ውስጥ ራሱን ችሎ የሚገባበትና ከታችኛው የክፍል ደረጃ ጀምሮ ሕጻናት እየተማሩት እያወቁት እየኮሩበት እሱን ምርኩዝ አድርገው በተሰማሩበት መስክ ታሪክ እየሰሩ እንዲሄዱ ማገዝ ይገባል በማለት አስረድቷል።

“……ወጣቱ ታሪክን የሚጠላ ወይንም ደግሞ የአባት የእናቶቹ ታሪክ እሱን የማይመለከተው ሆኖ አይደለም ይልቁንም ታሪኩ ላይ ትኩረት እንዳያደርግ ኑሮ አልተመቸውም። የሚፈልገውን ነገር አያገኝም። በዚህ ምክንያት ደግሞ ቀዳዳውን ደፍነው አገራዊ ፍቅሩንና አንድነቱን የሚሸረሽሩበት ብዙ ናቸው፤ በመሆኑም ወጣቶች በተለይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ላይ ያሉ ዛሬን ሳይሆን ራቅ አድርገው እያሰቡ እያመዛዘኑ ሁሉንም በልኩ ማስኬድ አለባቸው”ሲልም ይገልጻል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ተማሪና የተማሪዎች ሕብረት ዲሲፕሊንና መልካም አስተዳደር ዘርፍ ተጠሪ የሆነው ወጣት ረመዳን ኑርጌታ በበኩሉ እንደተናገረው፤ ዓድዋ አይቻልምን ወደ ይቻላል የቀየረ ነው። በዓሉን ማክበር ስናስብም ይህንን መለስ ብለን ማሰብና መገንዝብ ይገባናል።

ጣሊያኖች ለወረራ ሲመጡ ያሰቡትና ሆኖ ያገኙት ነገር ፍጹም የተለያየ ነበር፤ በቀላሉ ቅኝ ሊገዙንም እንደሚችሉ እርግጠኞች ነበሩ። ነገር ግን በወቅቱ የነበሩት እናት አባቶቻችን እንዲሁም አያቶቻችን ምንም እንኳን ያልተማሩ ዘመናዊ መሳሪያም ያልታጠቁ ቢሆኑም በገባቸው ልክ በአንድነትና በሕብረት በነቂስ ተመው እንኳን ለአገራቸው ለመላው ዓለም የሚያስደምም አንጸባራቂ ታሪክ ሰርተዋል።

ዓድዋ ከዛሬ 128 ዓመት በፊት አልፏል። ያንን አንጸባራቂ ድል መድገም ካለብን ግን አመቺው ጊዜ አሁን ነው የሚለው ወጣት ረመዳን በአገራችን እዚህና እዚያ እየሆነ ያለው ነገር ሁላችንም የምናውቀውና የምንገነዘበው ነው። በመሆኑም እነዚህን አለመግባባቶቻችንን በምክንያታዊነት ለአገር ክብርና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተን ማየት ይገባናል።

ወጣቱ ትላንት ሳይማሩ በሕብረታቸውና በአንድነታቸው ጠላትን ያሳፈሩ የአባቶቹን ገድል በመከተል ዛሬም ለአገሩ ክብርና አንድነት መጠበቅ የበኩሉን መወጣት ይገባዋል።

“…..አገር ላይ ጦርነት ሲኖር ሄዶ የሚዋጋው ወጣቱ ነው። እንዲሁም በቤቱ ቁጭ ብሎ በማኅበራዊ ሚዲያው የጥላቻ ንግግሮችን እየዘራ የሚያፋጀው ወጣቱ ነው፤ በመሆኑም የሚያደርገው ነገር መጨረሻው ምንድን ነው? ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ማየትና ዛሬ ካለችን አገር ነገ እንድትሆንልን ከምንመኛት ኢትዮጵያችን አንጻር ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን መመዘን ይገባል”ብሏል።

ዛሬ ጣሊያን አልያም ሌላ የነጭ ወራሪ መጥቶብን አይደለም ዓድዋን የምንደግመው ይልቁንም እግር ተወርች አስሮን ባለው ድህነት። ብሔርተኝነት። ጎጠኝነት ላይ በመዝመት ዓድዋን በእያንዳንዳችን ዘንድ መድገም ይገባል በማለት ወጣት ረመዳን ያስረዳል።

ሁላችንም አሁን ባለው ስርዓት ላይ የማይመቹን ነገሮች ሊኖሩ፣ ልንከፋም እንችላለን። ነገር ግን ያ ሁሉ ነገር ከኢትዮጵያችን በታች መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። በባሕል በሀይማኖት በአስተሳሰብና አመለካከት የተለያየን ብንሆንም ሁላችንም መጠለያችን አገራችን ናት። በሌላ በኩል ደግሞ እምነታችንንም አመለካከታችንንም ለማራመድ አገር ያስፈልገናልና ይህንን መጠበቅ ከወጣቱ የሚጠበቅ ኃላፊነት ስለመሆኑ አስረድቷል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ተማሪው ወጣት እንዳልካቸው ተስፋዬም ትላንት አባቶቻችን በሰሩልን አኩሪ ታሪክ ቀና ብለን ሄደናል። አሁንም በየዓመቱ ቀኑን እንዘክረዋለን፤ ይህ በጣም መልካም ነገር ነው። ነገር ግን እኛም ነገ ልጆቻችን የሚዘክሩት ታሪክ ልንሰራ ይገባል ይላል።

እንደ ወጣት እንዳልካቸው ገለጻ፤ ወጣቱ ብዙ የሚጠበቅበት ሚና አለ ለምሳሌ ገበሬ ክረምት ላይ ለፍቶ የዘራውን ነው በበጋ የሚሰበስበው፤ እኛም ዛሬ የሰራነው በጎም ሆነ መጥፎ ነገር ነገ እንደሚጠብቀን አስበን ቢያንስ የማናፍርበትን ታሪክ ሰርተን ለማለፍ መሞከር ይገባናል።

ዓድዋ መላው ሕዝብ አጥንቱን የከሰከሰበት ደሙን ያፈሰሰበት የነጻነት በዓላችን ነው፤ በዚህም ከቅኝ ግዛት ነጻ የሆነች አገርን ሊያስረክቡን ችለዋል፤ እኛ ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ ጥሩ ታሪክን ለማውረስ ዛሬ ላይ በተሰማራንበት መስክ ሁሉ ተግተን መስራት ይጠበቅብናል እንደ ወጣት እንዳልካቸው ገለጻ።

ብዙ የሚያራርቁን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን በሚያመሳስሉን ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል እንደዛ ካደረግን አገራችን የትላንት ገናናነቷ ላይ የማትመለስበት ምክንያት የለም ይላል።

አዎ ዓድዋ የእኛ ብቻ ሳይሆን፤ የመላው ዓለም ድል የይቻላል መንፈስን ያመጣ ታላቅ በዓል ነው። እኛም ዛሬ የዓድዋ ልጆች ነን ብለን በየአካባቢው በትንሽ በትልቁ መራራቅና መቃረናችንን ትተን ልዩነቶቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ ፈተን ነገን ብሩህ ለማድረግ የራሳችንንም ታሪክ ለመጻፍ ዛሬ መነሳት አለብን።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን የካቲት 22 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You