የካቲት በአትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ሥፍራ አለው፡፡ የአትዮጵያውያን የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ በደምና አጥንት የተፃፈበት ወር ነው፤ ከእነዚህ አበይት የታሪክ ክስተቶች አንዱ የዓድዋ ድል ነው፡፡ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡ የመላው ዓለም ተፈጥሯዊ ግብር እና ሰብአዊ ክብር የታደሰው፤ በእውነት በፍትህ እና ኅልውና ላይ የተቃጣው ጥቃት ድባቅ የተመታው በዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ታላቅ ድል ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን በአድዋ ጦርነት በጣሊያን ላይ የተቀዳጁት ድል መላው አፈሪካውያን ከነጭ ቅኝ ተገዥነትና ከባርነት መውጣት እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጠ ምሳሌ በመኾን ያገለገለ የነጻነት ደወል ነው፡፡ በአፍሪካውያን የጦርነት ታሪክ ውስጥ ከተከበሩና ከተደነቁ ጦርነቶች መካከል አንዱ ኢትዮጵያውያን አውሮፓውያንን ድል የነሡበት የአድዋ ጦርነት መኾኑ በታሪክ ይታወቃል።
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በግሩም ስነስርዓት የተደራጀ ግዙፍ የኢትዮጵያ ሠራዊት የማይታሰበውን ፈጽሟል። ወራሪው የጣሊያን ኃይል ላይ ድባቅ በመምታት ድልን ተቀዳጅቷል። ስግብግብነት በተጠናወተው የአውሮፓውያን መስፋፋት፤ ኢትዮጵያ ነጻነቷን በተሳካ መልኩ አስጠብቃለች ሲሉ ያነሳሉ፤ ዝነኛው የታሪክ ፕሮፌሰር ራይሞንድ ዮናስ፦ «የዓድዋ ጦርነት፤ በዘመነ ቅርምት የአፍሪቃ ድል» በተሰኘው መጽሐፋቸው። ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት፤ በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮፓ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን አረጋግጧል ይለናል የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ፡፡
የዓድዋ ጦርነትና ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በተሰኘና ዳኘው ኃይለሥላሴ ወደ አማርኛ በተረጐሙት መጽሐፍ ላይ፤ የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ፈረሱ ላይ ሆኖ የጋሻውን እምብርት መሬት ላይ እያጠቀሰ ጐራዴውን አየር ውስጥ እየቀዘፈ በተቆጣና በቆረጠ መንፈሥ በጀግንነት ተዋግቷል፡፡ ጦርነቱ በተጀመረ ከአምስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሃምሣ ስድስቱም የኢጣሊያ መድፎች ሙሉ ለሙሉ ተማርከዋል፡፡ የቅኝ ገዢውን ወራሪ ሠራዊት ከመሩት ጀኔራሎች ጄኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ከጥቂት አጃቢዎቹና በሽንፈት ከተበታተኑ የጣሊያን ወታደሮች ጋር ሸሽቷል፡፡
በዚህ ድብልቅልቅ ያለ ውጊያ ከሃምሣ ስድስቱ የጣሊያን መድፎች በተጨማሪ ብዙ ሺህ ቀላልና ከባድ መትረየሶች እንዲሁም የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎች በአሥር ሺዎችና በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ መሰል ጥይቶቻቸው ጋር ተማርከዋል፡፡ በአጠቃላይ ምርኮው ወደ አዲስ አበባ የተጓጓዘው በአምስት መቶ አጋሰሶች ተጭኖ ነው፡፡ ታላቁ የጥቁር ሕዝቦች ድል የዓድዋ ድል በመላው ዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛና ዋነኛ ለውጦች አምጥቷል፡፡
የእንግሊዝ ጋዜጦች በዓድዋ ድል ማግስት የዓለም ታሪክ ተገለበጠ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪካ ተቀሰቀሰ … ብለው ፃፉ፡፡ ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠሩ የተባሉት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በአካል ባልተገኙበት የነፃነት ተጋድሎ መሪዎች ጉባኤ የአፍሪካ ብሎም የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መሪ ተደርገው ተመርጠዋል።
በዚህ ለነፃነት፣ ለፍትህና ለእኩልነት በተደረገው ተጋድሎ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ጦሩን እያስተባበሩ መርተዋል፡፡ በቀጥታ በጦርነቱ ከመሳተፍ በተጨማሪ በተለያየ መስክ በመሰማራት ለድሉ መገኘት ጉልህ አስተዋጽኦ ያደረጉ ኢትዮጵያንም አሉ። ከእነዚህ ጀግኖች መካከል በስለላ ጥበባቸው የተካኑት ባሻ አውአሎም በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
የመስኩ ሰዎች የጠላትን ጦር እንዳያገግም አድርጎ ድባቅ ለመምታት የስለላ ጥበብ ከሁሉ የላቀ ሳይንስ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሄንን ጠንቅቀው የሚያውቁት ጥቁሩ ንጉሥ ምኒልክ ከጣሊያን ጋር ጦርነት ላለማድረግ በዲፕሎማሲ የተቻላቸውን ሁሉ ቢያደርጉም ጦርነቱ እንደማይቀር ሲረዱ፤ ከዘመቻና የጦር መሳሪያ ዝግጅት ጎን ለጎን እሳት የላሱ ሰላዮችንም ማፈላለግ ላይ አተኩረው እንደነበር ይነገራል። በዚህም አሰሳ በራስ መንገሻ አማካኝነት የተገኘው የሐማሴኑ ተወላጅ ባሻይ አውኣሎም አንዱ ነበሩ።
ባሻ በዐፄ ምኒልክና አማካሪዎቻቸው እንደተመከረው ሆነና ለጣሊያኖች ያደረ መስሎ … ስለ ዐፄ ምኒሊክ ጦር፣ ስለ አደረጃጀቱ ደካማነት እውነት አስመስሎ ማውራት ሲጀምር፤ ጀኔራል ባራቴሪ እውነተኛ ሰላይ ያገኘ መስሎት ሙሉ በሙሉ እምነቱን ጣለበት። እናም ባሻይ የሚናገረውን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባው ይወስናል።
ባሻም “… ዐፄ ምኒልክ ጦራቸው በርሃብና በውሃ ጥም ስለተጎዳ በድጋሚ አዋጅ እስኪነገር ወደየቤታቸው እንዲመለሱ አዝዋልና ከጥቂት ወታደሮች ጋር ብቻቸውን በአድዋ ስለሚገኙ በቀላሉ ትይዟቸዋላችሁ…..” ሲል ለባራቴሪ ይነግረዋል።
ባራቴሪም ጉዳዩን በማመን ጦሩን አሰልፎ ያለምንም ማመንታት አነጋግሮ ወደ አድዋ ሲገሰግስ…ሳያስበው የሐበሻ የጦር ቀለበት ውስጥ ይገባል!! እነሆ በስንት ዝግጅትና ስልጠና ባሕር አቋርጦ የመጣው ዘመናዊ ጦር በነባሻይ የተቀነባበረ ሴራ በግማሽ ቀን ብቻ የጦር ውሎ እንዳይሆኑ ሆኖ ቅስሙ ተሰበረ!
የታሪክ መዛግብት ባሻ አውአሎም ከጦርነቱ አስቀድሞ ከጣሊያን ጦር ጋር እንዲሰሩ ሆን ተብሎ ተመልምለው የተላኩ የአርነት አርበኛ ናቸው ይላቸዋል፡፡ ከጣሊያን ጋር አብረው፤ ለጣሊያን አድረው፤ ጣሊያንን ሰልለው እንዲመጡ በትዕዛዝ የተላኩ፤ የታዘዙትንም በቁርጠኝነት የፈፀሙ አርበኛ መሆናቸውን ታሪክ ይዘክርላቸዋል፡፡
በየካቲት ወር 1888 ብዙ ቀን በመፋጠጥ ጊዜው ካለፈ በኋላ ዐፄ ምኒልክና ሹማምንቶቻቸው የኢጣልያ ጦር ልብ አግኝቶ ምሽጉን ለቆ ወደ ውጭ እንዲወጣላቸው በበኩላቸው ልዩ ልዩ የመሳቢያና የማታለያ ወሬ ይፈጥሩ ጀመር ከዚህም አንደኛው የኢትዮጵያ ወታደር ስንቅ አልቆበት ለዘረፋ በያገሩ ተበታትኗል ይበልጡም ወደየአገሩ ገብቷል እነ ራስ እከሌም ሞተዋል ወይም ከድተዋል፤ ዐፄ ምኒልክም ታመዋል፤ እያሉ አውቀው ያስወሩ ጀመር በአንድ ወገን ደግሞ እነ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት፣ እነ ራስ መኮንን፣ እነ ራስ ሚካኤል ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር እየተማከሩ ጦርነት ብትጀምሩ ዞረን ወደናንተ እንገባለን እያሉ ቢቸግራቸው ለጣልያኑ አዛዥ ደብዳቤ ይፅፉ ነበር።
ጀነራል ባራቲዬሪ የመጨረሻ ውሳኔ ለመወሰን (ከኢትዮጵያ) ሰፈር ያሉት ሰላዮቻችን የሚያመጡልኝን ከሰማሁ በኋላ አንድ ውሳኔ እቆርጣለሁ ብሎ ሲጠባበቅ የእንትጮው ተወላጅ ባሻ አውአሎም መጡና ከላይ ያለውን ሀሳብ ማለትም የኢትዮጵያ ጦር እንደተበታተነ ነገሩት።
ታሪክ እንደሚነግረን በተለይ ባሻ አውአሎም ጣሊያኖች ባልፈለጉት ጊዜ እና ሁኔታ ወደጦርነት እንዲገቡ በማድረግ የተሳካ ስራ ሰርተዋል፡፡ በእርሳቸው የስለላ ጥናት መሰረት የኢትዮጵያ ተዋጊዎች የጦርነት ብልጫ ማግኘት እንዲችሉ አስተዋፅኦ አድርገዋል ይላሉ። እነሆ የካቲት 22 ቀን 1888 ዓም ለሊት ባሻ አውአሎም ከአሉላ አባነጋ ጦር የተቀላቀሉበት- ለሊቱን ሙሉ ብርቱ ጦርነት የተደረገበት – በነጋታው የአድዋ ድል የጥቁሮች ሁሉ ድል መሆኑ የተበሰረበት ቀን ነው፡፡
ከጠላት ሰፈር ያሉት ሰላዮቻችን የሚያመጡልኝን ከሰማሁ በኋላ አንድ ውሳኔ እሰጣለሁ ባለው መሠረት የሰላዮችን ወሬ ከሰማ በኋላ የሰላዮችን ቃል አምኖ የኢጣልያንና የኢትዮጵያን ዕድል የሚወሰንበትን ትልቁን የዓድዋ ጦርነት ለማድረግ የካቲት 22 ማታ ጦሩን አሰልፎ ከምሽግ ወጣ፡፡ አንደኛ ጀነራል ዳቦርሜዳ ከነ ወታደሩ 18 መድፍ ይዞ በቀኝ በኩል ተሠለፈ፡፡ በሌላ በኩል ጀነራል አሪሞንዲ ከነ ወታደሩ 12 መድፍ ይዞ ሠፈረ፡፡ በመካከል ጀኔራል አልቤርቶ ከነ ወታደሩ 14 መድፍ ይዞ በግራ በኩል ሲሰለፍ፤ ጀነራል ኤሌና ከነ ወታደሩ 12 መድፍ ይዞ ከኋላ ደግሞ ጀነራል ባራቲዬሪ 6 የማዦር አሚሊዮ ጦር ይዞ ተንቀሳቀሰ፡፡ ሁሉም በሰሜን በኩል በየ ጦር ግንባሩ ከፊት ሆኖ በታላቅ ጥንቃቄ ከምሽግ ወጥቶ ድንገተኛ ጥቃት ለማድረስ ወደ ፊት ገሰገሰ።
እያንዳንዱ ወታደር 112 ጥይት የሁለት ቀን ስንቅ ከላይ የሚደርበውን ካባ የውኃ ኮዳና የዳቦ መያዣውን ይዞ የእርድ ከብት ከነ መሳሪያው ከሠራዊቱ ኋላ ሆነው ስልከኞችና ቴሌግራም አስተላላፊዎች መሣሪያዎቻቸውን ይዘው አንዱ ሰራዊት ከሌላኛው ርቆ እንዳይሄድና ተነጥሎ በመገሥገስ ከጠላት ጦር ጋር ብቻውን ገጥሞ አደጋ እንዳይደርስበት ጥብቅ ትዕዛዝ ተሰጥቶት የመንገድ መሳሳትም እንዳይኖር ተጠንቶ የተዘጋጀ የካርታ ፕላን ይዘው በአገር ተወላጆች ባላገሮች ጭምር መንገድ እየተመሩ ለመጋጠም ገሰገሱ፡፡
በአካባቢ በሜዳ ላይ ተበታትነው የሚታዩ ብዙ ጉብታዎች ስላሉ በእነዚህ ጉብታዎች ላይ ሆነው ቴሌግራፍ ኦፕቲክ በሚባል መሣሪያ እየተመለከቱ ለእከሌ ረዳት ጦር ይጨመርለት እከሌ ወደፊት ይግፋ ወይም ወደኋላ አፈግፍጎ ለእከሌ ይደረብና ይህን ስፍራ ይያዝ የሚል ትዕዛዝ እየተሰጠው ጦርነት ተጀመረ።
ተዋጊ የጦር አባል ቢሞት ወይም ቆስሎ ከወደቀ በቶሎ እንዲነሳና የሕክምና እርዳታ የሚያደርጉ ሁሉ ተመድቦላቸው እንደዚሁም ወሬው ለኢትዮጵያ ጦር ደርሶ ተጠንቅቆ እንዳይጠብቁ በማለት ከሰፈር የመነሻውን ጊዜና ሰዓት ለማንም እንዳይነገር በጥብቅ ታዞ በታላቅ ጉጉት ወደፊት ገሰገሱ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ከኢትዮጵያ ባላሥልጣኖች ጆሮ ያመለጠ አልነበረም።
የኢንቲጮ ተወላጅ የሆኑት ባሻ አውአሎም ሐረጎት፤ የካቲት 22 ቀን 1888 ከጣሊያን ጦር ጋር ወደ አድዋ እየተጓዙ ነበር፡- ያውም የጣሊያንን ጦር እየመሩ፡፡ የካቲት 22 ቀን ለሊት ለየካቲት 23 አጥቢያ በጄኔራል ባራቴሪ የሚታዘዘው የጣሊያን ጦር በባሻ አውአሎም መንገድ መሪነት ከአድዋ ተራሮች ፊት ለፊት ተፋጠጠ፡፡
ይኼን ጊዜ ባሻ አውአሎም በድንገት ከጣሊያን ጦር መሃል አፈትልከው ወደ ኢትዮጵያውያን ገበሬ ተዋጊዎች ምሽግ ገሰገሱ፡፡ ጄኔራል ባራቴሪ ከጉያው አፈትለከው ወደ ኢትዮጵያውያን ጦር የሚሮጡትን ባሻ አውአሎምን አያቸው፡፡ እና ጮክ ብሎ ጠራቸው፡፡
“ባሻ አውአሎም! ባሻ አውአሎም!”
ባሻ አውአሎም ሩጫቸውን ሳይገቱ ጥቂት ዘወር ብለው እንዲህ አሉት፡-
“ዛሬ አንተን አያድርገኝ!”
እናም ዘለው ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያንን ጦረኞች ተቀላቀሉ፡፡
የአድዋ ድል ሲነሳ የባሻ አውዓሎምን ድርሻ አለማስታወስ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ እኚህ ጀግና በስለላ የተጫወቱት ሚና አንድ ጀግና አርበኛ ተኩሶ በመግደል ካደረገው ድርሻ ከፍ ቢል እንጂ የሚያንስ እንዳልሆነ ብዙዎች ይመሰክራሉ። ከድል በኋላ ባሻይ “… በዚያ በየካቲት 22/1888 ዓ.ም ሌሊት፣ የጠላትን ሰራዊት ይዤ ስገሰግስ አድሬ ንጋት ላይ የካቲት 23 1888 ዓ.ም በዐፄ ምኒልክ እቅፍ ውስጥ አስተኛሁት!” ሲል ቃሉን ሰጥቷል።
ባሻይ የጠላትን ጦር በተሳሳተ መረጃ ማደናገር ብቻ ሳይሆን ጠላትን እየመራ ካደረሰ በኋላም ከወገኖቹ ጎን በመሰለፍ ተዋግቶ አንድ ነጭ እንደማረከም ይነገራል። በዚህ ስራው ባሻይ ከድል በኋላ በንጉሡ እንደተወደሰና በራስ መንገሻ ስር ሆኖ የወረዳ አስተዳዳሪነት ሹመት እንደሰጡትም ተጽፏል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም