ማኅበሩ የዓይነ ስውራን ሴቶችን ሕይወት ለማቅናት ድጋፍ ይሻል

ከመጀመሪያ ደረጃ ተማሪነቷ ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ እስክትወጣ ድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በቅርቡ ተመርቃለች። ዛሬም ቢሆን የችግሩ ዓይነት ይለይ እንጂ ፈተና ላይ ናት። ዓይነ ሥውሯ መስከረም መኩሪያ፣ ሥራ ለማግኘት ቀጣሪ ድርጅቶችን ደጅ ብትጠናም አልሆነላትም። ግራ ቢገባት ለምታውቃቸው ሁሉ ‹‹የሥራ ያለህ?›› እያለች ነው። ዘወትር ሥራ እንዲፈልጉላት የምታውቃቸውን ሰዎች በመማጸን ላይ ትገኛለች።

ይህ ዓይነቱ ችግር የመስከረም ብቻ ሳይሆን የብዙ ዓይነ ሥውር ሴቶች ችግር ሊሆን እንደሚችል ነጋሪ አያሻውም። ዓይነ ሥውራን በብዙ ነገር አለመመቻቸት በየቀኑ ከሚገጥማቸው ፈተናዎች አንዱ የሥራ ዕድል ማግኘት ጎልቶ ይነሳል።

ብራይት ወርልድ ፎር ብላይንድ ውሜን አሶሴሽን (ማኅበር) ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ማኅበር ሲሆን የሴት ዓይነ ሥውራንን ችግር ለማቅለል ጥረት ያደርጋል። ሴት ዓይነ ሥውራን በጎ አድራጊ በሆኑት በወይዘሮ አዳነች ቸኮል አማካኝነት በ2005 ዓ.ም ብዙ ዓላማ ሰንቆ ነው የተቋቋመው። ከዓላማዎቹ መካከል ሴት ዓይነ ሥውራንን ማሰልጠን፣ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል፣ ከጥገኝነት እና ከልመና ማላቀቅ አንዱ ነው።

የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዘነበች በላቸው እንደሚናገሩት፣ ማኅበሩ ከሚሰጣቸው ሥልጠናዎች መካከል የብሬል፣ የኮምፒውተር፣ ለወጣት ሴቶች የሥነ ተዋልዶ፣ ኤች አይቪ/ኤድስ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ተጠቃሾቹ ናቸው። ማኅበሩ በሦስት መንገዶች ለሴት ዓይነ ሥውራን አባላቶቹ ድጋፍ እንደሚያደርግ የጠቆሙት ሥራ አስኪያጇ፤ አንደኛው በዕድሜ የገፉና አቅመ ደካማ የሆኑ ሴት ዓይነ ሥውራንን፣ ከቤት መውጣት  የማይችሉትን፣ ወጥተውም በልመና ለሚተዳደሩት ሕይወታቸውን ለማቅናት እንዲሁም ከችግር እንዲላቀቁ ማኅበሩ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ያስረዳሉ። ዕድሜያቸው ለገፋና እና መሰልጠን ለማይችሉ አቅመ ደካማ ዓይነ ሥውራን ሴቶች ደግሞ የምግብ፣ የንጽህና መጠበቂ፣ የአልባሳት እና የገንዘብ ድጋፎችን ያደርጋል።

ማኅበሩ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ሴት ዓይነ ሥውራን እንዲሁም ያለ አባት ልጆቻቸውን ለሚያሳድጉ ዓይነ ሥውራን እናቶች የዳንቴል፣ የኮምፒውተር፣ የብሬል እና መሰል ሥልጠናዎች እንደሚሰጥ የተናገሩት የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ፤ እነኚህ ሴቶች በብዛት የሚተዳደሩት በልመና እና ሎተሪ በመሸጥ መሆኑን ገልፀዋል። ማኅበሩ ይህን ችግር በመረዳት ከልመና ወጥተው የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ጥረት እያደረገ ይገኛል። የእጅ ሥራ ሥልጠና ለወሰዱ ሴቶች ደግሞ የሠሩትን ዳንቴል ራሳቸውም ሆኑ ማኅበሩ በሚሳተፍባቸው የተለያዩ ባዛሮች ላይ በመገኘት ምርቶቻቸው እንዲሸጥ በማድረግ ገንዘብ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ሕይወታቸውን ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ ወይዘሮ ዘነበች ያስረዳሉ።

በሁለተኛ ደረጃ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚማሩ ችግረኛ ሴት ዓይነ ሥውራን ተማሪዎች በአቅም ማጣት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ ለማድረግ የትራንስፖርት የሚሆን ገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

ማኅበሩ ከተመሠረተ 11 ዓመታትን አስቆጥሯል። በነዚህ ዓመታት ውስጥ ሴት ዓይነ ሥውራን ቤታቸው ከሚቀመጡ እና የሰው እጅ ከሚያዩ እየሠሩ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ዕድሉን አመቻችቶላቸዋል። ከተለያዩ ዓይነ ሥውራን ጋር ስለሚገናኙም የተለያዩ እውቀቶችን እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር ማኅበራዊ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር በር ከፍቷል። ማኅበሩ በእስካሁኑ ጉዞው ከ90 በላይ ሴት ዓይነ ሥውራንን በገንዘብ፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ ፣የበትር ድጋፍ፣ በምግብ እና በመሳሰሉት ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። በተጨማሪም ከማኅበሩ 120 አባላት ባሻገር ብዙዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።

ይሁን እንጂ ማኅበሩ በችግር ላይ ነው። ከካናዳ በመሥራቿ በኩል ከሚገኝ የአልባሳት፣ የገንዘብ፣ የክር፣ የነጭ በትር (ኬን) ከሚያገኘው ድጋፍ ውጪ ሌላ ድጋፍ ባለማግኘቱ ብዙ መሥራት እንዳልተቻለና እንዲያውም አደጋ ላይ እንደሆነ ሥራ አስኪያጇ ይገልፃሉ። ሌላው ችግር የእጅ ሥራ ሥልጠና ለመስጠት አመቺ እና በቂ ቦታ ባለመኖሩ ማኅበሩ ከአቅም በላይ በሆነ መንገድ እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ማኅበሩ ከግለሰብ ቤት ተከራይቶ ድጋፍ እደረገ ሲሆን፤ ድጋፍ የሚደርግለት አካል ቢያገኝ እንዲሁም የእጅ ሥራ ውጤቶቻቸውን ገዢ እንዲገኙ የገበያ ትስስር ቢፈጠር ከተቋቋመበት ዓላማ በተጨማሪ ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ሥራ አስኪያጇ ይናገራሉ።

ዓይነ ሥውራን ሴት ተማሪዎች የሚማሩት ከዓይናማ ተማሪዎች (የዕይታ ችግር ከሌለባቸው) ጋር ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም የኮምፒውተር ፣ ላፕቶፕ ፣ታብሌት እና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶች እጥረት ስላለባቸው በርካቶች በትምህርታቸው እንደሚወድቁ የጠቆሙት ወይዘሮ ዘነበች ፤ በቀጣይ እንደዚህ ያሉትን ተማሪዎችን ለመደገፍ ታስቧል። ይሁን እንጂ ድጋፍ ለማግኘት አዳጋች ሆኗል ይላሉ።

በመንግሥት በኩል ያለው ድጋፍ አጥጋቢ እንዳልሆነ የገለጹት ሥራ አስኪያጇ፤ ከዚህ ቀደም በመንግሥት በኩል ስልጠና ይሰጥ እንደነበር ያስታውሳሉ። አሁን ግን የመቀዛቀዝ ነገር ይታያልና መንግሥትም ሆነ ሌሎች ደጋፊዎች የማኅበሩን ችግር ተመልክተው ድጋፍ ቢያደርጉ የብዙ ሴት ዓይነ ሥውራንን ሕይወት ለመቀየር እንደሚቻል ያስረዳሉ።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን የካቲት 21/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You