የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን በዘላቂነት የማሳደግ ጥረት

በምጣኔ ሀብታቸውና በፖለቲካ ተፅዕኗቸው የዓለም ኃያላን የሆኑት ሀገራት ባለሀብቶቻቸውን በመደገፍ ረገድ በርካታ ተግባራትን ያከናውናሉ። እነዚህ ሀገራት ባለሀብቶቻቸውን በማገዝና በመጠበቅ እረገድ የሰሩት ስራ የአምራችነት አቅማቸውን አሳድጎ የምጣኔ ሀብት እድገታቸው ዘላቂ እንዲሆን አስችሎታል። ለማይናወጥ ምጣኔ ሀብትና ለኃያልነታቸው መሰረት የሆነው ከውጭ ጥገኛነት በመላቀቅ የማምረት አቅም ማሳደግ መቻላቸው እንደሆነ ይታወቃል። እነዚህ ሀገራት አሁንም ቢሆን ባለሃብቶቻቸውን የሚያበረታቱባቸው ልዩ የድጋፍና ጥበቃ መርሃ ግብር አላቸው። የምጣኔ ሀብት ጥናቶች እንደሚያስረዱት፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ለዘላቂ የሀገር ልማትና እድገት አስተማማኝ ዋስትና መሆን የሚችሉ የልማት አንቀሳቃሾች ናቸው።

ኢትዮጵያውያን የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎና ድርሻ በየጊዜው እየተሻሻለ እንደመጣ ባይካድም በቂ የሚባል ግን አይደለም። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚታየው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ተሳትፎና ድርሻ ተስፋ ሰጭ ሆኗል።

የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መደረጉ፣ ለኢንቨስትመንት እድገት መሰናክል የነበሩ ሕጎችና መመሪያዎች መሻሻላቸው፤ በመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና ተያያዥ ዘርፎች እየተገበረ ያለው ቀልጣፋና ፈጣን አሰራር፤ የኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራዎች፤ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ በመንግሥት ልዩ አቅጣጫ መቀመጡና ትኩረት መሰጠቱ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለሙ የሪፎርም ስራዎች መተግበራቸው ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ተሳትፎና ድርሻ ማደግ ምክንያቶች ሆነው ይጠቀሳሉ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በማምረቻው ዘርፍ የነበራቸው ተሳትፎ አበረታች እንደሆነ ሰሞኑን የመስሪያ ቤታቸውን የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ገልፀዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ 30 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚያስመዘግቡ 301 የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን በአምራች ዘርፉ ለማሰማራት ታቅዶ፣ ከ29 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 292 ባለሃብቶች አምራች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ተችሏል። በግማሽ ዓመት በአምራች ኢንዱስትሪው ከተፈጠረው 120ሺ 793 የስራ እድል መካከል 105ሺ 910 የሚሆነው የስራ እድል የተፈጠረው በሀገር ውስጥ ባለሃብቶች አማካኝነት ነው።

በምግብና መጠጥ ዘርፍ (በዱቄት፣ በዳቦ፣ በምግብ ዘይት፣ በፓስታና ሞኮሮኒ፣ በውሃ፣ በጁስ፣ በብርዕና አገዳ እህሎች ማቀነባበር፣ በቡና ማቀነባበር፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበር እና በለስላሳ መጠጥ ምርት) 104፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን (የወረቀትና ካርቶን እና፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ) 94፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንጂነሪንግ (ኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ፣ አውቶሞቲቭ እና ማሽነሪ ምርት) 80፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት 12 እንዲሁም በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ሁለት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ስራ ገብተዋል።

አቶ መላኩ የፀጥታ ችግሮች፣ የመስሪያ ቦታዎች በበቂ ሁኔታ አለመዘጋጀት እና በአዲስ አወቃቀር ምክንያት የአንዳንድ ክልሎች ፈጥነው ወደ ስራ አለመግባት አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም መሰናክል መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለእነዚህ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች አቅም ማደግ መሰረት ሊሆኑ የሚችሉትን የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ልማት ስራዎችን በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ፣ በ2016 ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከገቡ አምራቾች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እንደሆኑ ይገልፃሉ። እንደ አቶ አክሊሉ ማብራሪያ፣ ባለፈው አንድ ዓመት በልዩ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከተከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን የማነቃቃት፣ የማበረታታትና ወደ አምራች ዘርፉ ገብቶ ውጤታማ ስራዎችን እንዲሰራ የማድረግ ስራ ነው። በዚህ ሂደት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ አምራች ዘርፉ እንዳይገቡ መሰናክል የነበሩ ችግሮች ተለይተው መፍትሄ እያገኙ ነው።

ዋና ስራ አስፈፃሚው እንዳሉት፣ ከዚህ ቀደም ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የሚሰጠው ቦታ አነስተኛ ነበር። በ2015 እና 2016 ዓ.ም የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲነቃቁ ባለሃብቶቹ ያሉባቸውን የፋይናንስና ሌሎች ክፍተቶችን የሚሞሉ ተግባራት ተከናውነዋል። በመሆኑም በ2015 እና ዘንድሮ ከተመዘገቡት ባለሃብቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ናቸው። አንዳንድ ችግሮች ሲፈጠሩ ጓዙን ጠቅልሎ የሚሄድ የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ጥገኛ ሆኖ መቀጠል ተገቢ ስላልሆነና ተወዳዳሪ የሆነ የሀገር ውስጥ ባለሃብት ማሳተፍና መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የተጀመረው ስራ ውጤት እያመጣ ይገኛል። ሀገር በቀል ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በምርት ስራ ላይ ለመሰማራት የሚያሳዩት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ የኩባንያዎቹ የማምረት አቅማቸው አድጎ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ተወዳዳሪ የመሆን አቅማቸው ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ አመላካች ነው።

‹‹ሀገር በቀል ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲገቡ ያስደስታል›› የሚሉት አቶ አክሊሉ፤ ‹‹ሀገር በቀል ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በምርት ስራ ላይ ለመሰማራት የሚያሳዩት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ የኩባንያዎቹ የማምረት አቅማቸውና ተወዳዳሪነታቸው ማደጉን ከማመላከቱም በተጨማሪ የውጭና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች በሽርክና (Joint Venture) የሚሰሩበት የቢዝነስ ሞዴል እድገት እያሳየ እንደሆነም ጠቋሚ ነው›› ብለዋል።

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየር አይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ጥያቄ ሊነሳበት የማይገባ ጉዳይ እንደሆነና ተጨባጭ ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረዋል። ባለሀብቶቹ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ከሚኖራቸው ሚና ባሻር ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር፣ ገቢ ምርቶችን በመተካት እና የወጪ ንግድን በመጨመር ትልቅ አስተዋፅዖ ስለሚኖራቸው ይህን ሚናቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ በመንግሥት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ገልፀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍ ጥረት በብዙ መልኮች ሊገለፅ ይችላል። ባለሀብቶቹን የሚያበረታቱ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን በመቅረፅ፣ ፋይናንስን ጨምሮ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በማሟላት እንዲሁም ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ውጣ ውረዶችን በማቃለል ለባለሀብቶቹ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል።

እንደ ሞላ (ዶ/ር) ገለፃ፣ በተለይ ኢትዮጵያ በስራ አጥነትና በዋጋ ንረት እየተፈተነች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነው። የመንግሥት ድጋፍ ምጣኔ ሀብቱን በማነቃቃት፣ የሥራ እድል በመፍጠር፣ የገቢ ንግድ እቃዎችን በመተካት፣ የወጪ ንግድን በማሳደግ ጥቅል ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንዲኖረው ያደርጋል።

የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል የግብዓቶች (መሰረተ ልማቶች) አለመሟላት፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቁመው፤ መንግሥት የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን ጨምሮ የባለሀብቶቹን ችግሮች ለማቃለል የሚረዱ የፖሊሲና የመዋቅር እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚኖርበትና ለባለሀብቶቹ የሚያደርገውን ድጋፍ በየጊዜው መገምገምና ማሻሻል እንዳለበትም ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ሀገር በራሷ አምራቾች ላይ እንድትተማመን ያስችላል። ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ ምክንያት በሚፈጠሩ ችግሮች ከሚከሰት አደጋ ለመዳንም ይረዳል። በዚህ ረገድ ሞላ (ዶ/ር) ‹‹የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በፋይናንስና በቴክኖሎጂ አቅም ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ምጣኔ ሀብታዊ ስብራትና ክፍተት እንዳይፈጠር ለማድረግ ያግዛል። ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉት የውጭ ኩባንያዎች በሀገር ውስጥ የሚቆዩት የሀገር ውስጥ ፖለቲካው እስከተመቻቸው ድረስ ነው። ፖለቲካው ሳይመቸው ቀርቶ ኩባንያዎቹ ከሀገር ቢወጡ ሀገሪቱ በርካታ ዓመታት እንደገና ወደኋላ እንድትመለስ የሚያደርግ አደጋ ይከሰታል። ስለሆነም ይህን ስጋት ለማስወገድ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍ አቅማቸውን እንዲጎለብቱ ማድረግ ያስፈልጋል›› ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹በምጣኔ ሀብታቸው የበለፀጉት የዓለም ሀገራት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን ቀደም ባሉት ጊዜያት ብቻም ሳይሆን አሁንም ከፍተኛ ድጋፍና ጥበቃ ያደርጉላቸዋል። ሀገራቱ በፋይናንስ አቅርቦትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ለባለሀብቶቻቸው የተለየ የድጋፍ መርሃ ግብር አላቸው። የበለጸጉት ሀገራት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸው የሚያደርጉት ድጋፍ፣ ገና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ከሚያደርጉት ድጋፍ ቢበልጥ እንጂ አያንስም›› በማለት ገልፀዋል።

መንግሥት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው። የማምረት አቅምን ማሳደግ፣ ለዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› መርሃ ግብር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ንቅናቄው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በማቃለል ረገድ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል። የማምረት አቅምን በማሳደግ የወጪ ንግድን ለመጨመርና ገቢ ምርቶችን ለመተካት ለሚደረገው ጥረት አወንታዊ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሆነም ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በንቅናቄው በኢንዱስትሪ ደረጃ ከተለዩ ሁለት ሺህ 167 ችግሮች (የግብዓት፣ የመሠረተ ልማት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፣ የመስሪያና የማስፋፊያ ቦታ ዝግጅት፣ የጉምሩክና የሎጂስቲክስ አገልግሎት … ችግሮች) መካከል፣ አንድ ሺህ 34 የሚሆኑት መፍትሄ እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን በቀሪዎቹ አንድ ሺህ 133 ላይ ደግሞ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝና ችግሮቻቸው ከተፈቱላቸው አምራቾች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ አምራቾች መሆናቸውን አቶ መላኩ ገልፀዋል። ከንቅናቄው ምሠሦዎች መካከል አንዱ የሀገር በቀል ምርቶችንና አመራረትን ማሳደግ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ሳይደግፉ ይህን ማሳካት እንደማይቻል አስረድተዋል።

የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ሀገር በራሷ አምራቾች ላይ እንድትተማመን ያስችላል። አምራችነቱን ያላሳደገ እና ፍላጎቱንና አቅርቦቱን በራሱ የማምረት አቅም ላይ ያልመሰረተ ምጣኔ ሀብት ደግሞ ዘላቂ እድገትን ሊያስመዘግብ አይችልም። ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ ምክንያት በሚፈጠሩ ችግሮች ከሚከሰት አደጋ ለመዳንም ይረዳል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገት እንድታስመዘግብ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍና ተወዳዳሪ ማድረግ ይገባል።

‹‹የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ›› እንዲሉ፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍና ተወዳዳሪ የማድረግ ጉዳይ በምጣኔ ሀብት ትብብርና በእርዳታ ስም የሚደረግን የሀብታም ሀገራትንና ተቋሞቻቸውን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት ሉዓላዊነትን እስከማስከበር ድረስ የዘለቀ ትርጉምና ፋይዳ አለው። ሀገራዊ የማምረት አቅምን በማሳደግ ምጣኔ ሀብታዊ እድገትን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ደግሞ ሁነኛው መፍትሄ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው ዋነኛ ተዋንያን እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

አንተነህ ቸሬ

 አዲስ ዘመን የካቲት 21/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You