በጤናው ዘርፍ የማኅበራዊና ባህሪ ለውጥ የማምጣት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፡- በሦስተኛው ሀገር አቀፍ የማኅበራዊና ባህሪ ለውጥ ጉባዔ በኢትዮጵያ የማኅበራዊና ባህሪ ለውጥ ለማምጣት የተከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በጉባኤው መክፈቻ ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት፣ እስካሁን በጤና ዘርፍ የማኅበራዊና ባህሪ ለውጥ ለማምጣት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል።

በአሁኑ ወቅት የጤና ሚኒስቴር የተለያዩ የቴሌቪዥንና ሌሎች ሚዲያዎችን በመጠቀም ለሁሉም ፕሮግራሞቹ እየሠራበት ይገኛል ያሉት ሚኒስትሯ፤ በዚህም ማኅበራዊና ባህሪያዊ ለውጥ በማምጣት አምራች ዜጋ የመፍጠሩ እንቅስቃሴ አበረታች ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።

ዶክተር መቅደስ እንዳሉት፤ በጤና አጠባበቅ ረገድ የሚኖር የማኅበራዊና ባህሪ ለውጥ በሽታን ለመከላከልና ጠንካራ የጤና ሥርዓት እንዲኖር ይጠቅማል። ኢትዮጵያ ለምትከተለውም የቅድመ መከላከል ፖሊሲ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። እንደ ሀገርም በጤናው ዘርፍ በዘላቂ ልማት ግብ የተቀመጠውን አላማ ለማሳካት መሠረታዊ ስትራቴጂ በመሆን የሚጠቅም ይሆናል። በመሆኑም የማኅበራዊና ባህሪ ለውጥ የማምጣቱ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ለዚህም የአጋር ድርጅቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ድርሻ ስለሚኖረው በቅንጅት የምንሠራ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የጤና ትምህርትና ፕሮሞሽን ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር እሸቱ ግርማ በበኩላቸው የማኅበራዊና ባህሪ ለውጥ ለማምጣት የተሠሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል። እንደ ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ በጤና ዘርፍ የማኅበራዊና ባህሪ ለውጥ ለማምጣት እንደ ሀገር የተሠሩ ሥራዎች ውጤት እያስመዘገቡ ቢሆንም አሁንም መሠራት ያለባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ። ግንዛቤ የመፍጠሩ ሥራ ደግሞ ከፍተኛ ጊዜ፤ ወጪና ሞያተኛ የሚፈልግ በመሆኑ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፎ ይጠይቃል።

በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው ጉባኤም የማኅበረሰቡን ጤና በማሻሻል ዜጎች የራሳቸው ጤና ባለቤት በመሆን እንዲጠብቁ ለማስቻል ግንዛቤ ለመፍጠር ሁኔታዎች የሚመቻቹበት ይሆናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በጉባኤው ከሀገር ውስጥና ከውጭ የመጡ ከ400 በላይ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ አድራጊዎችን ጨምሮ የሚሳተፉበት እንደሆነም ጠቁመዋል።

በቀጣዮቹ ቀናትም በርካታ ጥናቶችና ተሞክሮዎች የሚቀርቡ እንደሚቀርቡ በመጥቀስ፤ ይህም በመድረኩ ከሚኖረው የእውቀትና ልምድ ሽግግር ባለፈ ለፖሊሲ አውጪዎችና ተግባሪዎች እንዲሁም ለሚድያ ግብአት የሚገኝበት ነው ብለዋል።

ሦስተኛው የማኅበራዊና ባህሪ ለውጥ ጉባኤ በየሁለት አመቱ የሚካሄድ ሲሆን ዘንድሮም «የማኅበራዊና ባህሪ ለውጥ፤ ለዘላቂ ልማት» በሚል መሪ ቃል ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ይሆናል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን የካቲት 20 / 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You