ኢፕድ የሥልጠና ማዕከሉን ወደ ኮሌጅ ለማሳደግ አቅዷል

  • 24ተኛ ዙር ሥልጠና ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሥልጠና ማዕከሉን ወደ ኮሌጅ ለማሳደግ ማቀዱን አስታወቀ። የሥልጠና ማዕከሉ «በፎቶና ቪዲዮ ኤዲቲንግ እንዲሁም በዲዛይን» ለስምንት ተቋማት የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሲሠጥ የነበረውን ሥልጠና ትናንት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድም ተክሉ ለሠልጣኞች ሰርተፍኬት በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ 84 ዓመታትን ያስቆጠረው ኢፕድ መረጃዎችን ለሕዝብ ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር በዘርፉ ያካበተውን ልምድ ለማጋራት የሥልጠና ማዕከል ከፍቶ እያገለገለ ይገኛል።

ኢፕድ በሥልጠና ማዕከሉ የቴክኒክና የጽሑፍ ሥልጠና፣ ተቋማዊ ክህሎትና አሠራርን የሚያሳድጉ እንዲሁም የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ወደፊት የሥልጠና ማዕከሉን ኮሌጅ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንና ለኮሌጁ የሚሆን ሕንፃ የማዘጋጀት ሥራም ተጀምሯል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሥልጠናና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንግዳ መኮንን በበኩላቸው፤ የኢፕድ ሥልጠና ማዕከል በ23 ዙሮች የፌዴራልና የክልል ተቋማትን እንዲሁም የሌሎች ተቋማትን ሠራተኞችና አመራሮች በተለያዩ የሥልጠና ፕሮግራሞች ማሰልጠኑን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁት የሥልጠና ማዕከሉ 24 ዙር ሰልጣኞች ሲሆኑ፤ የሥልጠናው ዓይነት «የፎቶና ቪዲዮ ኤዲቲንግ እንዲሁም የዲዛይን» ክህሎትና እውቀት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ዲና ሽፈራው በበኩሏ፤ በኢፕድ ሥልጠና ማዕከል ስትሰለጥን የመጀመሪያዋ እንደሆነና ተቋሙ የሥልጠና ማዕከል እንዳለው እንደማታውቅ ገልፃለች።

ሥልጠናውን ለ10 የሥራ ቀናት እንደተከታተለችና ከሥልጠናው ጥሩ እውቀትና ክህሎት እንዳገኘች የገለጸችው ዲና፤ የሥልጠናው የአሰጣጥ ሂደት፣ የአሠልጣኞች የፈጠራ ችሎታ እና የሥልጠናው ይዘት እርስ በእርስ የተጣጣመ ነው። ይህም የሠራተኞችን ችሎታና አቅም ያሳድጋል ስትል ሃሳቧን ሰጥታለች። ተቋማ ከኢፕድ ጋር በመተባበር ተጨማሪ ሥልጠናዎችን ለሠራተኞች እንዲያዘጋጅ እንደምትፈልግና በሥልጠናው ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ መልካሙ ማሞ በበኩሉ፤ በኢፕድ ሥልጠና ማዕከል ለ10 የሥራ ቀናት ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና በዘርፉ ዕውቀትና ልምድ ባላቸው አሠልጣኞች የተሰጠ በመሆኑ ሥራውን ለማሳደግ እንደሚያግዘው አስረድቷል።

በፎቶና ቪዲዮ ኤዲቲንግ እንዲሁም በዲዛይን ዙሪያ መሠረታዊ ዕውቀት እንደነበረውና ከሥልጠናው ያገኘውን ክህሎትና ለተቋሙ ውጤታማነት እንደሚያግዘው ተናግሯል።

ሥልጠናው ከሰባት ተቋማት ለተውጣጡ 23 ሠልጣኞች የተሰጠ ሲሆን፤ ሠልጣኞቹ ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ ከአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፣ ከአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ፣ ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እና ከስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የተውጣጡ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ናቸው።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን የካቲት 20 / 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You