31 ሺህ የዩክሬን ወታደሮች መሞታቸውን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ገለጹ

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት ባለፉት 2 ዓመታት ውስጥ 31 ሺህ ወታደሮቿ እንደሞቱባት ተናግረዋል።

ዘለንስኪ በትናንትናው ዕለት ባደረጉት ንግግር ከዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የዩክሬን ወታደሮችን የሞት መጠን ይፋ አድርገዋል። ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በኪቭ በሰጡት መግለጫ፤ በጦርነቱ የቆሰሉ ወታደሮቻቸውን ቁጥር ግልጽ አላደረጉም የተባለ ሲሆን፤ መረጃውን ይፋ ማድረግ ለሩሲያ እቅድ ሊጠቅም ይችላል በሚል መደበቃቸው ተነግሯል።

«እንደሚወራው 300 ሺህ አሊያም 150 ሺህ ሳይሆን፤ 31 ሺህ ወታደሮቻችንን አጥተናል» ያሉት ዘለንስኪ፤ «የሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲን እየዋሹ ነው» ብለዋል። ሆኖም ግን «31 ሺህ ወታደሮቻችንን ማጣት ለእኛ ትልቅ ኪሳራ ነው» ብለዋል ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ። ዩክሬን ከፈረንጆቹ 2022 መጨረሻ ወዲህ የሞቱባት ወታደሮቿን ቁጥር ግልጽ አድርጋ የማታውቅ ሲሆን፤ በወቅቱም ዩክሬን ባወጣችው መረጃ የሞቱ ወታደሮቿ ቁጥር 13 ሺህ ነው ብላ ነበር።

የአሜሪካው ኒው ዮርክ ታይምስ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ዋቢ በማድረግ ባወጣው መረጃ በጦርነቱ 70 ሺህ የዩክሬን ወታደሮችና 120 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች ሞተዋል ብሏል። የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው በጦርነቱ የሞቱ የሩሲያ ወታደሮች ቁጥር 180 ሺህ እንደሆነ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር የገጠመችውን ጦርነት 2ኛ ዓመት አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር «ዩክሬን ሩሲያን ታሸንፋለች»ብለዋል። «ማናችንም ብንሆን ዩክሬን እንዲያበቃላት አንፈቅድም» ብለዋል ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ባደረጉት ንግግር።

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ባሳለፍነው ቅዳሜ ሁለተኛ ዓመቱን ደፍኗል። ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን «ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ» ማካሄድ መጀመራቸውን ያወጁት በፈረንጆቹ የካቲት 24 2022 ነበር። ዘመቻው እንደተባለው በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ግን አልሆነም፤ በሁለቱም ወገን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈትና ለጉዳት ዳርጎ ሦስተኛ ዓመቱን አሃዱ ብሏል ሲል የዘገበው አልዓይን ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን የካቲት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You