ህልፈቱ ጥበብን ያጎደላት ጌታቸው

አዲስ አበባ፣ የካ ሚካኤል ጌታቸው ጸጋዬ ይሄን ምድር የተቀላቀለበት ሰፈር ነው። «አዲስ አበባ» በተሰኘው ዘፈኑ∶-

ውብ አዲስ አበባ

የትውልድ ሀገሬ

ያደኩብሽ መንደር

መርካቶ ሰፈሬ

ሲል ያቀነቀነላት መርካቶ ደግሞ አብዛኛው የልጅነት ሕይወቱን የኖረባት አለሙ ነች። ወደ ሙዚቃ የገባው ቋንቋውን በማያውቀው፣ የስድስት ዓመት ልጅ እያለ በሰማውና «አዝማሪኖ» (ከአስመራ በወጡና አስመራን በናፈቁ ጣልያኖች የተዘፈነ) በተሰኘ ዘፈን በመመሰጥ ነው። ያኔ የዘፈኑ ምንነት ባይገባውም ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ መሆኑን አስመስክሯል። እቤታቸው በሚገኘው ሬድዮ ዘወትር አባቱ የሚከፍቷቸውን ሙዚቃዎች በተመስጦ ያጣጥም ነበር፤ በተለይ «አዝማሪኖ» ቋንቋው ባይገባውም ለዘፈኑ የተለየ ፍቅር አደረበት። መጀመሪያ አካባቢ ሥራዬ ብለው ያላስተዋሉት አባቱ የሱ በሙዚቃ መመሰጥ ሲበዛባቸው ልጃቸው አዝማሪ ሲሆን ታያቸው። እሱን ለመከላከል ትልቁን ቴፕ አንስተው ደበቁት። ያኔ ታዲያ ከቤት ወደ ውጪ ሙዚቃን ፍለጋ ውሎውን ቀየረ፤ መርካቶ በሚኘው ካሊፎርኒያ ሻይ ቤት የሚከፈቱትን ሙዚቃዎች ለማጣጣም ማልዶ መነሳትና ሻይ ቤቱ ደጃፍ ላይ መሰየም የዘወትር ሥራው ሆነ።

ካሊፎርኒያ ደጃፍ የሚሰማቸው ስቲቪ ዎንደር፣ ሀሪ ቤላፎንቴና ሌሎች ጥቁር አሜሪካውያን የተጫወቷቸው የእንግሊዝኛ ዘፈኖች የጉሮሮው ማሟሻ ናቸው። ጥሎበት ለድራም (የሙዚቃ መሣሪያ) ለየት ያለ ፍቅር ነበረው። በዚህ የተነሳ ቆርቆሮ እንደድራም እየመታ ይለማመድ ነበር። ይሄንን ድርጊቱን ያየ፣ ከየመን የመጣ በርካታ የሙዚቃ መሣሪያዎች በቤቱ ያለው ግለሰብ ወደ ቤቱ ወሰዶ የሚለማመድበትን ሁኔታ አመቻቸለት። በዚህ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም ግሩም ድራም ተጫዋች ነው። ፒያኖ ሲጫወትም ከራሱ አልፎ ሌሎችን የሚያዝናና ሆኗል። ከሻይ ቤት ደጃፍ ዘወትር የሚሰማውን ኤልቪስ ለመሆን ይሞክራል። በየሄደበት ያንጎራጉራል፤ የሱን ሁኔታ ያስመስላል፤ በአፍላነት ዕድሜው የመርካቶው ኤልቪስ ለመሰኘት ጊዜ አልፈጀበትም።

አባቱ ይህ ሁኔታ አልተመቻቸውም። ሁለተኛ ስታዜም ብሰማ ውርድ ከራሴ አሉት። ያኔ ከሙዚቃ ከምለያይ ብሎ ይመስላል ወደ ድሬዳዋ ኮበለለ። ከድሬዳዋ ወደ ሐረር አቀና። በዚያም በምሥራቃዊ ሰጎን ኦርኬስትራ ሙዚቃን መሥራት ጀመረ። አባት በዘመኑ አጠራር የልጃቸው «አዝማሪ» መሆን ሊዋጥላቸው አልቻለም። ከምንም በላይ ደግሞ የእሳቸው ሥም በየመድረኩ መነሳቱ አንገበገባቸው። በዚህ የተነሳም ስሜን እንዳታስጠራ ሲሉ ለልጃቸው ቀጭን ትእዛዝ አስተላለፉ።

ሙዚቃ ከማንም በላይ ናት ያለው ድምጻዊ እሱም የአባቱን ሥም ከጸጋዬ በወቅቱ የፍቅር ጓደኛው በነበረችው አባት ካሳ ቀየረ። «ጌታቸው ጸጋዬ» ከሚለው ሥያሜ ይልቅ የሕይወቱን አብዛኛውን ክፍል «ጌታቸው ካሳ» በሚለው መጠሪያ ተጠርቶበታል። ሐረር እያለ ጥበቡ በላቸው በተሰኘ ሰው የግጥም ደራሲነት «እመኛለሁ» ግጥም ተጻፈ። በጌታቸው የዜማ ደራሲነት እመኛለሁን ይዞ ከአድማጭ ጋር ተገናኘ። ሆኖም የምሥራቅ ቆይታው ማብቃቱን በማመኑ ወደ ትውልድ መንደሩ አዲስ አበባ ተመለሰ። ያኔ የኦርኬስትራው አመራሮች የሱ ከኦርኬስትራው መጉደል የኦርኬስትራው መጉደል መሆኑን በማመናቸው አዲስ አበባ ድረስ አፈላላጊ ልከው በግድ ይዘውት ተመለሱ። ሆኖም «ወታደር ልታደርጉኝ እንደሆነ ስለሰማሁ እዚህ ከዚህ በላይ አልቆይም» ብሎ በመወሰኑ ምንም ማድረግ ሳይችሉ ቀሩ። «እመኛለሁ» ከሕዝብ ጋር ያስተዋወቀው የመጀመሪያ ብሎም ተወዳጅ ሥራው ነው።

እመኛለሁ

እመኛለሁ

እመኛለሁ

ዘወትር በየለቱ

ላሳካ ኑሮን ከብልሀቱ

ኑሮና ብልሀቱ

እንስኪቃናልኝ

በሃሳብ ግስጋሴ

ወደርም የለኝም

አልቃና እያለኝ

ኑሮና ብልሀቱ

መቼውም አልቀረ

ምኞት መዘግየቱ

አሰብኩት አለምኩት (2 ጊዜ)

እኔ ሁሌም

አዲስ ነኝ ለዛሬ

እንዳለውም ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፤ ውቤ በረሃ ይገኝ በነበረው ፓትሪስ ሉቡምባ ቤት የቤቱ ድምቀት ሆነ። ወዲያው ፈላጊው በዛ እሱን ብለው ሰዎች መጉረፋቸውን ያዩ የምሽት ቤት ባለቤቶች እሱን ለማግኘት ተሻሙ። የአምስት ብር ደሞዙ ወደ አስራ አምስት ብር አድጎ ሰንጋ ተራ አካባቢ ወደ ነበረው ሶንፕሮሬ ክለብ አመራ። ሶንፕሮሬ እየሠራ «ሳይሽ እሳሳለሁ» ለተሰኘ ሥራው ዜማ በመድረስ እውቅናው ይበልጥ ናኘ። እዚያም ብዙ ሳይቆ ወደ አክሱም አዳራሽ ተሸጋገረ።

ጌታቸው ተፈላጊ ገበያ ከፋች ድምጻዊ ነውና ዝውውሩ እንደ ደራ ቀጠለ። ፒያሳ ወደሚገኘው ቬነስ የምሽት ክበብ በማቅናት መሥራት ቀጠለ። እዚያ ሳለ «ምን ይሆን ምስጢሩ» እና «ፍቅርሽን እሻለሁ» የተሰኙ ሙዚቃዎቹን እንካችሁ አለ። በመቀጠልም ወደ ዋቢ ሸበሌ በማቅናት ሙዚቃ መጫወቱን ቀጠለ። በ1964 ዓ.ም የወጣው «ትዝታ» የተሰኘ የትዝታ ሥራው የትዝታ ሥራን ከእንጉርጉሮ አላቆ ለውዝዋዜ ሲጋብዝ የሱም ተወዳጅነት ከፍ አለ። ይሄንን ሥራውን እሱ «እኔ ሳልከፋ ነው» ይላል። ቦብ ዲለን የተሰኘ ዓለማቀፋዊ አርቲስት ምርጥ ስብስቦች መካከል የተካተተ ድንቅ ሥራው ነው።

«ሀገሬን አትንኳት» የተሰኘ ሀገራዊ ሥራው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቁርኝቱ ጥብቅ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው፤ በ1969 ዓ.ም ሀገር አማን ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ «ኢትዮጵያ ትቅደም!!!» ብሎ በሰላም ሀገሩን ከፊት ለማስቀደም ደፋ ቀና የሚልበት ወቅት ነበር። ያኔ ታዲያ በዚያድ ባሬ የሚመራው የሱማሊያ ጦር ከምሥራቅ አቅጣጫ «ታላቋን ሱማሊያ መፍጠር» በሚል ቅዠት ወረራ ማካሄዱ ተሰማ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ሬድዮ ጋዜጠኛ የነበሩት ደራሲ አበራ ለማ በየአቅጣጫው በመዘዋወር ሁነቱን የመዘገብ ዕድል ነበራቸው። ያኔ የጠላት ጦር ወደ ሐረር ከተማ ተቃርቦ የወገን ጦርም ሐረርን ላለማስረከብ የሚከፈለውን መስዋእትነት ታዝበው ወደ አዲስ አበባ ቢመለሱም፤ ሀገሬ ተደፈረች የሚለው ቁጭት ከውስጣቸው አልወጣም ነበር። በዚህ ስሜት ውስጥ ሆነው የጻፉት «ሀገሬን አትንኳት» የተሰኘ ግጥም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ወጣ።

ወቅቱ ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ «አሪፍ ግጥም የሚሰጠኝ ሰው ካለ» ብሎ ገጣሚ የሚፈልግበት ወቅት ነበር። ግጥሙን እንደ ብዙሀኑ ኢትዮጵያውያን በጋዜጣው አንብቦ የወደደው ጌታቸው ግጥሙን ለመዝፈን ተነሳስቷል። በዚህ ወቅት ጌታቸውና አበራ ለማን በሚያውቅ፣ ጌታቸው ደገፉ በሚሰኝ ፒያኒስት አማካኝነት ገጣሚውና ዜመኛው ይገናኛሉ። ገጣሚ አበራም በሃሳቡ በመስማማቱ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የወጣው ሀገሬን አትንኳት ተቀንሶና ለዘፈን በሚሆን መልኩ ተስተካክሎ እንዲሠራው ተስማሙ። ያኔ ታዲያ ጌታቸውም ሃሳቡን ስለወደደው 24 ሰዓት ባልሞላው ጊዜ ዜማ ሠራለት። ከደራሲ አበራ «አደሴዋ» የተሰኘ የፍቅር ግጥምም ተቀብሎ ነበርና ሁለቱ ሙዚቃዎች በአንድ ሸክላ ላይ ወጡ። በተለይ «ሀገሬን አትንኳት» ሀገር በጭንቅ ላይ በነበረችበት በዚያ ወቅት የወታደሩን ሞራል ገንቢ ከመሆኑም ባሻገር፤ አሁን ድረስ የሀገር ስሜት ቀስቃሽ፣ ተወዳጅ ዘፈን እንደሆነ አለ።

ሀገሬን አትንኳት

የብዙሀን እናት

መጠጊያ የምንላት

እማማ ናትና

ሀገሬን አትንኳት

በዓድዋ በማይጨው

ጀግኖች የሞቱላት

ሕፃን ሽማግሌ

የተሰየፈላት

ደመ መራራና

ቁጡነት ያለባት

ጎጆዬ ናትና

ሀገሬን አትንኳት

የጌታቸውና የሙዚቃ ፍቅር የተለየ ነው። ሙዚቃን ሲል በአፍላነት ዕድሜው ከቤት ኮብልሏል። ዘመዴ፣ ጓደኛዬ ብሎም ሁሉ ነገሬ ለሚላት ሙዚቃ ፍቅር ሲል የአባት ሥም እስከመቀየር የደረሰ መስዋእትነትን ከፍሏል። ያኔ በወጣትነቱ ሒልተን በሳምንት ሰባት ቀን ዘፍኗል። ሰባቱንም ቀን ሙዚቃን ተለማምዷል። በሀገር ቤት ቆይታው ከአማርኛ ሙዚቃዎች በተጨማሪ የእንግሊዝኛ ዘፈኖችንም ይጫወት ነበር። በተለይ ሒልተን ሆቴል ለረዥም ጊዜ የሠራበት ቤት ነው።

በ1981 እ.አ.አ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ በመሄድ ሥራውን ጀመረ፤ በ1986 እ.አ.አ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። ያኔ ታዲያ ወደ አሜሪካ ከማቅናቱ በፊት ለዘጠኝ አመታት ወደ ሠራበት ሂልተን ተመልሶ ለሁለት ዓመታት ከኢትዮ ስታር ባንድ ጋር ሠርቷል። ቀጣዩን አንድ አመት በግዮን ሲሠራ፤ ሦስቱን ዓመታት አዲስ ያዘጋጀውን አልበም በማጥናት አሳልፏል። ያኔ «አመሰግናለሁ»፣ «እወድሻለሁ»እና ሌሎች ተወዳጅ የሙዚቃ ሥራዎችን የያዘው አልበም ተሠራ። በተለይ አመሰግናለሁ የተሰኘው ተወዳጅ ሥራው አሁን ድረስ የተለያዩ መድረኮች ማጠቃለያ፣ መዝጊያ ሙዚቃ በመሆን እንደተወደደ ዘልቋል።

አመሰግናለሁ

(አንጓዎቹን በመድገም ሁለት ሁለት ጊዜ ነው የሚላቸው)

መሄዴ ነው እኔ

መሰናበቴ ነው

በሉ ደህና ዋሉ

አመሰግናለሁ

አብረን ባለን ጊዜ

ብዙ አሳልፈናል

ደጉንም ክፉንም

አብረን ተጫውተናል

መለየት ቢከብድም

ከሚወዱት ሰው

አይጠፋም ምንጊዜም

አለን ትዝታው

ስደትን ምርጫው በማድረግ ከ27 ዓመት በላይ መኖሪያውን በአሜሪካ አድርጎ ቢቆይም ዜግነቱን ከመቀየር ይልቅ ተያዝኩ/አልተያዝኩ ብሎ በሰቀቀን መኖርን ምርጫው አድርጓል። በርካቶች ሕይወቱን በቀላሉ እንዲመራ ዜግነት መቀየር ምንም ማለት መሆኑን በመንገር ሊያሳምኑት ቢሞክሩም፣ እሱ ግን «ሀገሬን አትንኳት» ያላትን ሀገሩን መቀየር አሻፈረኝ እንዳለ ኑሮ ባይደላውም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ መቆየትን ምርጫው አድርጓል። ያለፉትን አስር ዓመታት መኖሪያውን ሀገር ውስጥ ያደረገ ሲሆን፤ በሀገር ውስጥ በተለያዩ መድረኮችና የምሽት ክበቦች ሙዚቃን ሲጫወት ቆይቷል። ሙዚቃ ከመጫወቱም ባሻገር አብዛኛውን ጊዜ ቤቱ ውስጥ ከፒያኖ ጋር ያሳልፍ ነበር።

50 ዓመታትን በተሻገረው የሙዚቃ ሕይወቱ አምስት አልበሞችን ለአድማጭ አድርሷል። «ብቻዬን ተክዤ»፣ «ትዝታ» ፣ «የኔ አለም»፣ «ብርቱካን ወይ ሎሚ» እና «እንዲህም ናቸው» የሚሉ አልበሞችን ለሕዝብ አድርሷል። «በቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ አላውቃቸውም» እስኪል ድረስ የበረከቱ ሙዚቃዎችን ተጫውቷል። በተለይ «ሀገሬን አትንኳት»፣ «ሳይሽ እሳሳለሁ»፣ «እወድሻለሁ»፣ «ትዝታ»፣ «አዲስ አበባ»፣ «ውበትም ይረግፋል» ፣«ትዝ ባለኝ ጊዜ»፣ «የከረመ ፍቅር»፣ «ልውሰድሽ አንድ ቀን»፣ «አትጥፊ ከጎኔ»፣ «አመሰግናለሁ» እና «ቀና ብዬ ባየው» በተሰኙ ተወዳጅ ሙዚቃዎች በደንብ ይታወቃል። ከድምጻዊነቱ ባሻገር በዜማ ደራሲነቱ፣ በድራም እና ፒያኖ ተጫዋችነቱ ይታወሳል። ደግሞም ግሩም መድረክ ተቆጣጣሪም ነበር።

«እንዴት ነህ?» ሲባል በቃል ከማስረዳት በላይ የጄምስ ብራውንን «አይ ፊል ጉድ» በፈገግታ ታጅቦ ማቀንቀን መለያው ነበር። ያለፉትን 79 ዓመታት በዚህ ምድር የኖረው የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች፣ የዜማ ደራሲ፣ ድምጻዊው የጥበብ ሰው ጌታቸው ካሳ፤ የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊት በሕክምና ሲረዳ በቆየበት የካቲት 12 ሆስፒታል ሕይወቱ አልፏል። የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም በብሔራዊ ትያትር የክብር ሽኝት ተደርጎለት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ወዳጅ፣ አድናቂዎቹና ቤተሰቦቹ በተገኙበት ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል። አዲስ ዘመን ለወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ መጽናናት ከመመኘቷም በተጨማሪ ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ ስለተወልን ዘመን አይሽሬ ሙዚቃዎች «አመሰግናለሁ!!!» ማለት ትወዳለች።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን  የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You