ከኅብረቱ ጉባኤ ምን አተረፍን

የ37ተኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በመዲናችን አዲስ አበባ ለቀናት ሲካሄድ ቆይቶ በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ አድርጓል። ጉባኤው የኅብረቱን አባላት አጀንዳ ከማሳካት ባሻገር አዘጋጅ ሀገር ለሆነችው ኢትዮጵያ በርካታ ድሎችን አስመዝገቦ ያለፈ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ጉባኤው ከመካሄዱ በፊት የተሳታፊዎችን ደህንነት ከመጠበቅ፣ ከመስተንግዶና የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ የሚገነቡ የቱሪዝም መስህቦችን ከማስተዋወቅ አንፃር ቅድመ ዝግጅቶች ሲደረጉ ነበር። ጉባኤው ከተጠናቀቀ በኋላ በእቅድ የተቀመጡትን ግቦች በማሳካት ድሎች መመዝገባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።

‹‹37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ የተከበረችበትና የተመሰገነችበት ነው›› በማለት ከጉባኤው ማግስት የተገኙ ድሎችን ይፋ ያደረጉት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ዋናው የመሪዎች ስብሰባና ቀደም ሲል የነበሩ ስብሰባዎች በስኬት መጠናቀቃቸውን አብስረዋል። ኢትዮጵያም ይህንን ተከትሎ የተከበረችበትና የተመሰገነችበት መሆኑን ያነሱት አምባሳደር ብርቱካን፣ ጉባኤው ያለምንም የጸጥታ ችግር የተጠናቀቀ እንደነበር አንስተዋል። እንግዶች በክብር መጥተው በክብር ተሸኝተዋል። በየአመቱ እንግዶች አዳዲስ ነገር እንዲያውቁና እንዲለምዱ ችለዋል፣ በቀጣይም ከፍ ባለ ሁኔታ ለመቀበል ዝግጅት እንደሚደረግም ይፋ አድርገዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ ቀደም ብሎ ለሦስት ወራት ሲካሄድ ነበር። በዚህም 35 የሚደርሱ ተቋማት ተሳትፈውበታል። እንግዶችን ለመቀበል በሌሎች ሀገራት ያልተለመዱ የእንግዳ አቀባበል ዝግጅት መደረጉንም እነዚሁ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም ኢትዮጵያን ያስከበረና በልዩነት የታየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጉባኤው ማግስት አሳውቋል።

በስብሰባ ቱሪዝም እንዲሁም ታላላቅ ጉባኤዎች ለሀገራት ስለሚኖራቸው ተያያዥ ጥቅሞች በተደጋጋሚ ሲናገሩ የሚደመጡት ምሁራን የአፍሪካ ኅብረትን የመሰሉ ዓለም አቀፍ ሁነቶች የሀገርን ገፅታ ለመገንባት፣ ቱሪዝምን ለማሳደግ እንዲሁም መሰል ዝግጅቶችን በተመራጭነት ለማሰናዳት ትልቅ ዕድል የሚከፍቱ መሆናቸውን ይናገራሉ። የዘንድሮው የኅብረቱ ጉባኤ በስኬት መሰናዳትም የዚሁ ማሳያ እንደሚሆን ይገመታል። እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ በ37ተኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ እንግዶች በተደረገላቸው አቀባበል እንግዶችም ደስተኛ መሆናቸውና ምስጋና ማቅረባቸው ታውቋል። ሚኒስትሮችም እንግዶችን ሲቀበሉና ሲሸኙ ስለ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በማስረዳትና በማስተዋወቅ እንደነበር ተገልጿል።

የዝግጅት ክፍላችን 37ተኛው የኅብረቱ ጉባኤ ከመካሄዱ ሁለት ሳምንታት አስቀድሞ ‹‹ኢትዮጵያ ከቱሪዝምና ከሀገር ገፅታ ግንባታ አኳያ ዕድሉን በምን መልኩ ልትጠቀምበት ትችላለች›› የሚል ጥያቄ አቅርቦ ሰፋ ያለ ዳሰሳ ማቅረቡ ይታወሳል። ጉባኤው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ‹‹የታቀዱት ግቦች ከምን ደረሱ፤ ምን ዓይነት ስኬቶችስ ተመዘገቡ›› በማለት ጥያቄውን ብሔራዊ ኮሚቴ ውስጥ በቀዳሚነት ተሳታፊ ወደነበረው ቱሪዝም ሚኒስቴር ይዞ ቀርቦ ነበር። በምላሹ በሚኒስቴር መሥሪያቤት ውስጥ የስትራቴጂክ ዩኒት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው እንደሚከተለው ምላሽ ሰጥተውበታል።

እርሳቸው እንደሚሉት ጉባኤው ከመካሄዱ ሦስት ወራት ቀደም ብሎ ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ ልዩ ልዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተው ነበር። በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤን የማዘጋጀት ዕድል ስላላት ይህንን መልካም አጋጣሚ ለብሔራዊ ጥቅም በሚያግዝ መልኩ ለማሰናዳት ዝግጅቶች አድርጋ ነበር። በተለይ ቱሪዝምን ለማሳደግ፣ ለማስተዋወቅና በገበያ ልማትና ድርሻ ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነ ታምኖበት ከዚህ ለማትረፍ በርካታ እቅዶች ተይዘው እንደነበር ያስታውሳሉ።

በጉባኤው በርካታ ቁጥር ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና የተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳታፊ መሆናቸውን ያነሱት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፤ እንግዶቹ የሚስተናገዱባቸው ሆቴሎችና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሀገርን ስም በመልካም ሊያስጠራና የሀገርን ገጽታ የሚገነባ ጥራት ያለው አገልግሎት ማቅረባቸውንና በዚያም ስኬት መገኘቱን ያነሳሉ። ሆቴሎቹ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ጥሩ ትዝታን የሚጥል የኢትዮጵያን መልክ የሚያሳይ መስተንግዶ መስጠታቸውንና በዚያም ስኬት መገኘቱን ይናገራሉ።

ለዚህ ስኬት መገኘት የቱሪዝም ሚኒስቴር ቀደም ብሎ ከሆቴሎች ጋር በመነጋገር እና ቅድመ ገለፃዎችን በመስጠት ፍፃሜው እንዲያምር በርካታ ሥራዎች መሥራቱን የሚያነሱት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፤ ለተሻለ ስኬት መመዝገብ አስቀድመው የተሠሩት ቅድመ ዝግጅቶች አስተዋፆ እንደነበራቸው ተናግረዋል። ከሆስፒታሊቲው ባሻገር በኅብረቱ ግቢ ውስጥ ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች መሠራታቸውን በመግለፅም የኢትዮጵያ ዋንኛ መገለጫ የሆነውን ባህላዊ የቡና ማፍላት ሥነሥርዓት ማስተዋወቅ መቻሉን ተናግረዋል።

ስብሰባው በሚካሄድበት የኅብረቱ ግቢ ውስጥ የኢትዮጵያን መገለጫዎች የማስተዋወቅ ሥራ መከናወኑን የሚናገሩት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፣ ይህም ዋና ዋና የኢትዮጵያ ምልክቶችን ለአፍሪካውያንና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች በሚገባ ማሳየት የተቻለበት አጋጣሚ የፈጠረ እንደሆነ ይገልፃሉ። ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ (ምድረ ቀደምት) መሆኗን የሚያሳዩ የተለያዩ ማስታወቂያዎችና ግንዛቤ መስጫ ሁነቶች ተካሂደዋል የሚሉት ስትራቴጂክ ቡድን መሪው ምድረ ቀደምትነቷን ከሚያሳዩ መገለጫዎች ውስጥ አንዱ ማስረጃም የቡና መገኛ መሆኗ አንደሆነ ይናገራሉ።

‹‹ሌላው ምድረ ቀደምትነቷን አስረግጦ የሚያሳየው ማስረጃ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ መፍለቂያና መነሻ መሆኗ ነው›› የሚሉት የስትራቴጂክ ቡድን መሪው አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፤ እነዚህ ሦስት አስረጂ ሀብቶችን የኅብረቱ ጉባኤ በሚካሄድበት ስፍራ በመጠቀም ብራንዱን (ምድረ ቀደምት) የማስተዋወቅ ሥራ መከናወኑን ይናገራሉ።

በወቅቱ በኅብረቱ ስብሰባ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ሌሎች ባለድርሻዎች በብዛት እንደተገኙ የሚገልፁት አቶ ቴዎድሮስ፤ ሁሉም ስለ ኢትዮጵያ እንዲያውቁ ብሎም በርካታ የመስህብ ሀብቶች መገኛ እንደሆነች እንዲረዱ ለማድረግ መቻሉን ይናገራሉ። ሂደቱም አጋጣሚውን ተጠቅሞ የኢትዮጵያን ገፅታ መገንባት እንዲቻል የተደረገበት መሆኑን ያስረዳሉ።

የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ የመጀመሪያው እርምጃ ስለ መስህብና ሀብቶች መረጃ መስጠት ቀዳሚው ተግባር መሆኑን የሚያነሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ አንድ ጎብኚ ወደ ኢትዮጵያ ቢመጣ ምን ዓይነት አገልግሎቶችን፣ የመስህብ ስፍራዎችን፣ የታሪክና የመዝናኛ ቦታዎችን በምን መንገድ ማግኘት እንደሚችል መረጃ መስጠት ያስፈልጋል ይላሉ። የኅብረቱ ስብሰባ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የተገኙ እንግዶችም ይህ መረጃ እንዲኖራቸው በማስቻል በመዲናዋ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ መስህቦችን እንዲያውቁና ያላቸውን ጥቂት ጊዜ ተጠቅመው እንዲመለከቱት መደረጉን ይናገራሉ።

‹‹በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ የተገኙ ሁሉም የኢትዮጵያን መስህብ ስፍራዎች ላይጎበኙ ይችላሉ›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ ወደፊት ጊዜ ሲኖራቸው ግን በእቅድ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በቂ መረጃ እንዲኖራቸው እነርሱንም ታሳቢ በማድረግ የማስተዋወቅ ሥራ መከናወኑን ይናገራሉ። በኢትዮጵያ ቆይታ አድርገው ሲመለሱም ስለ ሀገሪቱ መልካም እይታ እንዲኖራቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ለማጋራት ዕድሉ ሊፈጠር ስለሚችል የገፅታ ግንባታ ሥራ መከናወኑን ያስረዳሉ።

የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በሚካሄድበት ወቅት ጎን ለጎን የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ የማስተዋወቅና የገፅታ ግንባታ ሥራዎች ይደረጋሉ የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ዘንድሮው በተመሳሳይ በዝግጅት ኮሚቴ ውስጥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አባል በመሆን በተመሳሳይ ዘንድሮም ተግባራዊ ሥራዎች መካሄዳቸውን ያነሳሉ። ይሁን እንጂ ከዚህም በበለጠ ወደፊት የጎንዮሽ ዝግጅት በመፍጠር የበለጠ በቱሪዝም ኢትዮጵያን ተጠቃሚ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ይናገራል።

የኅብረቱ ስብሰባ በርካታ ተሳታፊዎች ያሉትና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም ሽፋን የሚሰጡት መሆኑን የሚያነሱት አቶ ቴዎድሮስ ይህንን ዕድል በቀላሉ ማየት እንደማይገባ ይገልፃሉ። በመጪዎቹ መሰል ዝግጅቶች ላይ የኢትዮጵያን ቱሪዝም የሚያሳድጉ፣ የሚያስተዋውቁ አሳታፊ ዝግጅቶችን መፍጠር እንደሚያስፈልግም ያነሳሉ። የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ቋሚ እንደመሆኑ አጋጣሚውን መጠቀም እንደሚያስፈልግ በማንሳት የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ተፈጥሮና ሌሎች ልዩ ልዩ ሀብቶችን ማስተዋወቅ የሚያስችል የቱሪዝም የጎንዮሽ ሁነት በቋሚነት ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ። ለዚህም እንደ ሚኒስቴር መሥሪያቤት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ያነሳሉ።

አቶ ይታሰብ ስዩም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው ‹‹በቀጣይ ከዚህ መሰል አጋጣሚ ኢትዮጵያን በምን መልኩ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል›› በሚለው ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ። በዚህም የሆስፒታሊቲ ዘርፉ ተዋንያን እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለድርሻዎች የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ሲደርስ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ዝግጁ ሆነው መጠበቅ እንዳለባቸው ይገልፃሉ። የይድረስ ይድረስ ዝግጅት የኢትዮጵያን የማይስ ቱሪዝም እና የቱሪስት ፍሰቱን እንደማያሳድገው በማንሳትም ሁል ጊዜም ቢሆን ሆቴሎችና የመስህብ ስፍራዎች ለውጥና የማያቋርጥ እድገት ማምጣት እንደሚጠበቅባቸው ያነሳሉ። የትምህርትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ያነሳሉ።

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቁ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት እንደሚገኝ የማይስ ቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን ዕድሉን የሚከፍት ልምድ ለማዳበር እንደሚጠቅም ይናገራሉ። ይሁን እንጂ መሪዎች የሚገኙበት እና በኅብረቱ ጽሕፈት ቤት የሚደረግ ጉባኤ ከመሆኑ አኳያ ከደህንነትና ጥበቃ አንፃር ጥበቃ የሚደረግበት መሆኑን ነው የገለጹት። ይህ አጋጣሚ ልክ እንደሌሎቹ ጉባኤዎች ነፃነት የሚሰጥ ባይሆንም ጎን ለጎን በሚካሄዱ ዝግጅቶች መሪዎችን፣ ዲፕሎማቶችን እና ልዑካኑን ስለ ኢትዮጵያ መስህቦች እንዲያውቁ ዕድል መፍጠር አስፈላጊና የግድ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህን ማድረግ ከተቻለ የኢትዮጵያን ገፅታ ከመገንባት ባሻገር ቱሪዝም ሀብቶችን ማስተዋወቅ እንደሚያስችል ያስረዳሉ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ማይስ ቱሪዝም (ስብሰባዎችን መሠረት አድርገው የሚካሄዱ የቱሪዝም ሁነቶች) አንድ ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ ኢንዱስትሪ እንደሆነ ነው። ይህ አሃዝ እስከ 2025 (ከሁለት ዓመታት በኋላ) ወደ አንድ ነጥብ 5 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚመነደግ ቅድመ ግምቱን አስቀምጧል። ከዚህ መረዳት የምንችለው የሆቴል፣ ኮንፍረንስ፣ ኤግዚቢሽንና ባዛር እንዲሁም ልዩ ልዩ የማይስ ቱሪዝም ንዑሶችን የሚይዘው ኢንዱስትሪ ለዓለማችን የምጣኔ ሀብት ምንጭ እንደሆነ ነው። ለዚህ ነው በዘርፉ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ምሁራን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በማዘጋጀት ተጠቃሚ መሆን አለባት በማለት የሚሞግቱት።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን  የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You