በአሁኑ የይርጋለም ከተማ፤ በቀድሞ ገበሬ ቀበሌ ማኅበር በነበረው መሲንቾ ነው ተወልደው ያደጉት። መሲንቾ ቀድሞ በደቡብ አሁን ደግሞ በሲዳማ ክልል ውስጥ ነው የምትገኘው።
የመሲንቾ ፍሬ የሆኑት አቶ አርጋው አየለ መሲንቾ፣ አፈር ፈጭተው ከአብሮአደጎቻቸው ጋር ቦርቀው፣ የቀለም ትምህርት ተምረው፣ የእርሻ ሥራንም ቀስመው፣ ቤተሰብ ማክበርና መውደድን ሥነምግባርና ሰብአዊነትን ተጎናጽፈው የሕይወታቸውን መሠረት የጣሉት በትውልድ ቀያቸው ነው።
አስተዳደጋቸውን፣ የልጅነት ጊዜያቸውን እንዲህ ነበር ያጫወቱን፤‹‹በገጠር ሳሎን፣ መኝታ ቤት፣ ኩሺና፣ ሌላ ተጨማሪ ክፍል የለም። አባት፣ እናት፣ ልጆች፣ የቤት እንስሳውም በአንድ ቤት ውስጥ ነው የሚያድረው። እናታቸው ልጅ ሲወልዱ ላሞቹም እኩል የሚወልዱባቸው አጋጣሚዎች ነው የነበሩት። እናታቸውም ላሞቹም ምጥ ሲያፋፍማቸው አያታቸው ነበሩ የሚያዋልዷቸው።››
እናታቸው ስምንት ልጆች ነው የወለዱት። አቶ አርጋው አራተኛ ልጅ ናቸው። ከጊዜ በኋላ ግን አባታቸው ሌላ ሚስት አግብተው ልጆች በመውለዳቸው የልጆች ብዛት ወደ 14 ከፍ ብሏል። አባታቸው ሁለተኛ ሚስት ያገቡት ከአቶ አርጋው እናት ጋር ፀብ ስለነበራቸው አይደለም። የአካባቢው ማኅበረሰብ በልማድ የሚያደርገውና እንደባህልም የሚወስደው በመሆኑ ነው። አባታቸው ከሁለተኛ ሚስታቸው ጋር ሲሆኑ የአቶ አርጋው እናት ብቻቸውን መሆኑን መረጡ።
የቀድሞ ባለቤታቸውን ሚስት ግን በጥሩ ወዳጅነት ነው የሚቀርቧቸው። ልጆችም ከሁለተኛ ሚስት ከተገኙት ልጆች ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት አላቸው። በተለይም አቶ አርጋው ለአባታቸው ሁለተኛ ሚስት ጥሩ ስሜት አላቸው። በልጅነታቸውም አብረው ኖረዋል።
አቶ አርጋው አባታቸው ጎበዝ ገበሬ ብቻ ሳይሆኑ፤ በሥነምግባራቸው ትላልቅ ከሚባሉ፣ በሥራም ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሰዎች ጋርም በመዋል ሀገራዊም ሆነ በተለያየ ጉዳይ ላይ ጠቅላላ እውቀት ያላቸው ንቁ የሚባሉ እንደሆኑ ይገልጻሉ። ይህ ነው የሚባል የትምህርት ደረጃ ባይኖራቸውም በመጠኑ ተምረዋል። ከተማ ቀመስም ናቸው።
ከተለያዩ ሰዎች ጋር በአብዛኛው የሚገናኙት በመዝናኛዎች ሥፍራ በመሆኑ ገንዘብ ሲያስፈልጋቸው እህል ወይንም ሌሎች ንብረቶችን በመሸጥ በመሆኑ ስለ ገንዘብ ሲጠየቁ ‹‹ሰው ገዛሁበት›› የሚል ነበር መልሳቸው። አብረዋቸው ከሚውሉ ሰዎች የሚያገኙአቸውን ጥቅሞች ለመግለጽ ነው ይህን ቃል የሚጠቀሙት።
አቶ አርጋው እንደሚሉት አባታቸው ከተለያዩ ሰዎች ጋር መዋላቸው የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በር ከፍቶላቸዋል። አብዛኛው ገበሬ የልጁን ጉልበት ለመጠቀም ነው ቅድሚያ የሚሰጠው። የእርሳቸው አባት ግን እንዲማሩ ነበር የሚያበረታቷቸው። ልጆች በእርሻ ሥራ፣ ከብት በማገድና የሚታዘዙትን ሁሉ በመሥራት ቤተሰብ እያገዙ ነው የተማሩት።
በገጠር ምቾት የሚባል ነገር የለም። ምግብም ቤት ያፈራው ነው የሚቀርበው።አካባቢው በእንሰትም የሚታወቅ በመሆኑ ከእንሰት የሚዘጋጅ ቆጮ፤ አንዳንዴም የበቆሎ ቂጣ ዋና ምግባቸው ነው። ማባያው ወተት አብሮ ይቀርባል። የቆጮው ተረፈምርት ደግሞ ለመኝታ ያገለግላል። ፍራሽን የሚተካው ሳርም አሹቾ ይባላል። ቅያሪ ልብስም አይታሰብም።
አቶ አርጋው አሁን ሁሉ ነገር ተሟልቶላቸው እንኳን የገጠሩን ያህል ጣዕም ያለው ሆኖ እንዳላገኙት ይገልጻሉ። በገጠሩ የኤሌክትሪክ መብራት፤ በአጠቃላይ ዘመናዊ የሚባል ነገር የለም። ለጥናት ጊዜ ነው ኩራዝ የሚለኮሰው። አለበለዚያ ቤት ውስጥ በሚነደው እንጨት ብርሃን ነው የሚጠቀሙት። ማታ ከነደደው እንጨት ፍም በአመድ ተዳፍኖ አድሮ ነው ለጠዋት ቁርስ መሥሪያ ደግሞ እሳቱ የሚነደው። ፍሙ እንዳይጠፋ እርግጠኛ መሆን በሚቻልበት ሁኔታ ነው የሚዳፈነው።
ክብሪት መጠቀም የተለመደ አይደለም። ቢጠፋ እንኳን እሳት ከጎረቤት ነው የሚዋሱት። ሁሉም ሰው ሥራ ሠርቶ፣ ያለውን በጋራ ተካፍሎ፣ ባለው ነገር ተደስቶ ነው የሚኖረው። ሁሉንም ነገር የሚያሸንፈው ቤተሰባዊ ፍቅሩ ነበር። አቶ አርጋውም በዚህ ጊዜ ያገኙትን ደስታ ነው ዛሬም በዓይነኅሊናቸው በማስታወስና ለማጣጣም የሚሞክሩት።
ልጆችን በማነጽ የወላጆች ሚና የጎላ ቢሆንም የአካባቢው ማኅበረሰብም ያለው አስተዋጽኦ ልጆችን የተሻለ የሚያደርግ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አርጋው፤ የእርሳቸውን እናትና አባት አስተዳደግ በልዩ ሁኔታ ይገልጹታል። እርሳቸው እንዳሉት አባታቸው ሲበዛ ቁጡና ኮስታራ ናቸው። ልጅ የሚያቀብጡ አይደሉም። ያጠፋ ይገረፋል። እርሳቸውም የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሆነው ከጓደኞቻቸው ጋር ቁማር ሲጫወቱ አግኝተዋቸው ገርፈዋቸዋል። ከተገረፉ በኋላ ወደ ቁማር ጨዋታው አልተመለሱም።
አባታቸው ልጆች የሚያስፈልጋቸውን በማሟላት አይታሙም። የእናታቸው ግን ከአባታቸው ይለያል። በዱላና በቁጣ ሳይሆን፣ በፍቅር ነው ከጥፋታቸው የሚመልሷቸው። የእናታቸው ዘዴም ጥፋተኝነት እንዳይኖር የሚያደርግ ሆኖ ነው ያገኙት።
አቶ አርጋው አባታቸው ‹‹ሰው ገዛሁበት›› ብለው የሚሰጡት ምላሽ አሁን ላይ ነው የገባቸው። ሰው ለማግኘት የተለያየ ነገር እንደሚደረግ ከአባታቸው መማራቸውን ያስታውሳሉ።
ከአባታቸው ትልቅ ትምህርት ያገኙበትን አጋጣሚም እንዲህ ያስታውሳሉ። ለአባታቸው የተለያዩ ነገሮችን ማድረግ በመቻላቸው በአባታቸው ዘንድ የተለየ ቦታ እንደሚሰጣቸው ያስባሉ። ታዲያ አባታቸውን ከልጆቻቸው ማንን አብልጠው እንደሚወዱ ይጠይቋቸዋል። የአባታቸው ምላሽ ከጠበቁት ውጪ ነበር የሆነባቸው።
ምንም ለማድረግ አቅም የሌለው በቤተሰቡ ድጋፍ የሚኖረው ልጃቸውም ሆነ ሌሎቹም ልጆቻቸው ለእርሳቸው ልዩነት እንዳልነበራቸው ነበር በወቅቱ ምላሽ የሰጧቸው። አቶ አርጋውም በምላሹ ልባቸው ነበር የተነካው። አባታቸውን እንደፈጣሪ ተምሳሌት ነው ያዩዋቸው። አለማዳላትና በእኩል ማየትን ነው ከአባታቸው የተማሩት።
አቶ አርጋው፤ መልካም ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የአካባቢ ማኅበረሰብም ሚና እንደነበረው በማስታወስ፤ ለዛሬ ማንነታቸው ጥሩ መሠረት እንደሆናቸውና ባለውለታቸው እንደሆኑም ይገልጻሉ። በማኅበረሰቡ ውስጥ ያዩትን በጎ ሥራ እርሳቸውም በዚህ ውስጥ እንዲያልፉ እንዳደረጋቸውም ይናገራሉ። ሕይወት በትግል ውስጥ የሚታለፍበት እንጂ በምኞት የሚገኝ እንዳልሆነም ተገንዝበዋል።
እርሳቸውም ዛሬ የልጆች አባት በመሆናቸው፤ ከወላጆቻቸውም ሆነ ከማኅበረሰቡ ያገኙትን የቤተሰብ መምራት ተሞክሮ እንደጠቀማቸው ይናገራሉ። መሻሻል አለበት ብለው ያሰቡትን ግን በልጆቻቸው ላይ እየተገበሩት ነው። የእርሳቸው አባት ለልጆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚያሟሉ ቢሆኑም ለልጆቻቸው ፍቅር የሚያሳዩበት መንገድ ባለመኖሩ እንደሚወዷቸው እርግጠኛ አልነበሩም።
በተለይም ልጆች ወደ ጉርምስና ሲሸጋገሩ ስለሚገጥማቸው መጥፎም ሆነ መልካም ነገር ከአባታቸው ጋር የመወያየት ዕድሉ አልነበራቸውም። እንዲህ ያለው ነገር በዚያን ጊዜ እንደነውር ስለሚታይ ሊሆን ይችላል። ይሄኛውን መንገድ ነው እርሳቸው ለማሻሻል ጥረት ያደረጉት።
ምንም እንኳን እርሳቸው በተወለዱበት ጊዜ ያለው ነባራዊ ሁኔታና አሁን ዘመኑ የሚጠይቀው የልጅ አስተዳደግ የሚለያይ እንደሆነ የሚገነዘቡ ቢሆንም፤ በወላጆችና ልጆች መካከል ግልጽነት መኖር እንዳለበት ያምናሉ። በተለይም ጾታዊ ግንኙነትን በተመለከተና ስለ ዓለም ነባራዊ ሁኔታ ከልጆቻቸው ጋር በግልጽ የመወያየት ባህል በማዳበራቸውና እንደጓደኛም በመቅረብ ስለልጆቻቸው ፍላጎትና ያላቸውንም አስተሳሰብ ለመረዳት ችለዋል።
እርሳቸው ያለፉበትን መንገድም ለልጆቻቸው ብቻ ሳይሆን፤ ለልጆቻቸው እናትም ቢሆን ግልጽ ሆነው ነው ወደ ትዳር የገቡት። ሰው እራሱን መደበቅ የለበትም የሚል እምነት አላቸው። ከየትኛው ማኅበረሰብ እንደመጡና በምን ሁኔታ እንዳደጉ ለባለቤታቸው በእጮኝነት ዘመናቸው ነበር የነገሯቸው። ምስጢር ሆኖ የሚቆይ ነገር ዘግይቶ ችግር እንደሚያመጣና ትዳርንም እስከ ማፍረስ የሚደርስ ነገር እንደሚገጥም በሌሎች ላይ ደርሶ አይተዋል።
ስለትምህርት፣ የሥራ ሁኔታ፣ ወደ ትዳር የገቡበትን አጋጣሚና ስለቤተሰባቸው አቶ አርጋው እንዳጫወቱን፤ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ክፍል ድረስ ተወልደው ባደጉበት መሲንቾ ገጠር ነው የተማሩት። ወደ አራተኛ ክፍል ሲዘዋወሩ ይርጋለም ውስጥ በሚገኝ ሚሲዮን ትምህርትቤት ገቡ። በሚሲዮን እስከ ስምነተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ደግሞ ይርጋለም ከተማ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት እስከ 12ኛ ክፍል ተምረው ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
ፈጣንና ነገሮችን ቶሎ የሚረዱ፣ ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል እንደሆኑ እራሳቸውን ይገልጻሉ። አጋጣሚ ግን በ12ኛ ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት አልመጣላቸውም። ውጤቱ ያልመጣላቸው ጎበዝ ተማሪ ስላልሆኑ እንዳልሆነ ነው የሚያምኑት። ውጤት ያልመጣላቸው ብዙ ተማሪዎች እንደነበሩም ያስታውሳሉ። በወቅቱ ግን ይርጋለም ሆስፒታል ውስጥ እየሠሩ መማር የሚችሉበትን ዕድል አግኝተው በሆስፒታሉ ውስጥ ረዳት የላቦራቶሪ ቴክኒሻን ሆነው ተቀጠሩ።
በሥራቸውም በትምህርታቸውም ውጤታማ መሆን የቻሉት በአጭር ጊዜ ነበር። በሆስፒታሉም ትጉህና ጎበዝ ሠራተኛ ለመባል ጊዜ አልወሰደባቸውም። የሥራ ዕድላቸውንም በማስፋት ገቢያቸውንም ለማሳደግ እንዲሁ ፈጣን ነበሩ። በሌሎች የሕክምና ተቋማት ውስጥ በመሥራት ከመደበኛ ደመወዛቸው ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ኑሮአቸውን ለመለወጥ ይጥሩ ነበር። ገቢያቸው አንድ ሐኪም በወር ደመወዝ ከሚከፈለው በላይ የሚሆን ነበር። የላቦራቶሪ ቴክኒሻን ባለሙያ ቁጥር ውስን በመሆኑም በቀላሉ ነበር በሌሎች ዘንድ እውቅና ያገኙት።
ውሎአቸውም ከእርሳቸው ዕድሜ በላይ ከሆኑ እና በትምህርትም ከሚበልጧቸው ሰዎች ጋር ነበር። በሙያው ከሚቀርቧቸው በሕክምና ውስጥ ካሉት ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ኢንጂነሮች፣ የሕግ እና ሌላ ሙያ ካላቸው ጋር ጭምር ነበር። በዚህም ከዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር ተለዩ። ለመቀራረብ ቢሞክሩ እንኳን መግባባት አልቻሉም።
በዚህ ሁኔታ ለስድስት አመታት የላቦራቶሪ ቴክኒሻን ሆነው ሠሩ። በሆስፒታሉ የተመቻቸላቸውንም የትምህርት ዕድል አጠናቅቀው የምስክር ወረቀት አግኝተዋል። በሕክምናው ውስጥ ለመሥራት ፍላጎቱ ስለነበራቸው የ12ኛ ክፍል ነጥባቸውን ለማሻሻል ዳግመኛ ፈተና በመውሰድ ጥሩ ውጤት በማምጣታቸው በነርሲንግ ሙያም ለመሥራት ትምህርት ጀምረው ነበር። ግን አልገፉበትም።
የሥራቸው፣ የትምህርታቸውና አብረዋቸው የሚውሏቸው ሰዎች ሁኔታ ‹‹እኔ ማነኝ›› የሚለው ነገር በውስጣቸው እንዲፈጠር አደረገ። በትምህርታቸውም ሆነ በሥራቸው፣ አብረዋቸው ከሚውሉት ሰዎች ጋር የሚመጣጠን ሆኖ ባለማግኘታቸው ነበር ይህ ስሜት የተፈጠረባቸው። ከዚህ ሁኔታ ለመሸሽ የመጨረሻ ውሳኔያቸው የነበረው ከሀገር መውጣት ነው። ይህን ለማመቻቸት ደግሞ ዩክሬን ውስጥ የሚኖር የሚያውቁት ወዳጅ ስለነበራቸው እርሱ እንዲያመቻችላቸው አደረጉ። ዕድል ቀንቷቸው በትምህርት ዕድል እኤአ በ2000 ነበር ከኢትዮጵያ የወጡት።
ዩክሬንን ወደ እንግሊዝ ሀገር መሸጋገሪያ ለማድረግ ነበር እቅዳቸው። በዩክሬን ውስጥ እየተማሩ ለስድስት ወር ያህል ነበር የቆዩት። በዚህ በአጭር ጊዜ ቆይታቸው አንድ የታዘቡት ነገር ደግሞ ዩክሬኖች ለጥቁር ያላቸው አመለካከት በጣም መጥፎ መሆኑን ነው። በትራንስፖርት ውስጥ እንኳን ጥቁር ካዩ እስከ መደብደብ የሚደርሱበት ሁኔታ ለመታዘብ ችለዋል።
ዩክሬን ኮሚኒስት በነበረችበት ዘመን ብዛት ያላቸው ጥቁሮች የነበሩበትና በኑሮም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደነበሩ በታሪክ ተረድተዋል። ዩክሬናውያን ነፃ ሲወጡ ጥቁሮች የኢኮኖሚ አቅም መፍጠራቸው የቅናት መንፈስ እንዲያድርባቸው ስላደረጋቸው ወደ ጥላቻ እንደተቀየረም እንዲሁ ሰምተዋል። በዚህም በዩክሬን መቆየቱን አልወደዱትም።
ከዩክሬን በሕገወጥ መንገድ ለመውጣት ያደረጉት ሙከራም ለአንድ ወር ያህል አንገላቶአቸዋል። ሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹ አንዳንዴ ከአሳማ ጋር ሌላ ጊዜ ደግሞ ለመቆየት ምቹ ባልሆነ ውስጥ ያሳድሯቸው ስለነበር ፈተናው ከባድ ነበር። ድንበር ለመሻገር ያጋጠማቸውን ፈተና ሁሉ ተቋቁመው በመጨረሻ ተሳክቶላቸው ወደ ሀንጋሪ ተሻገሩ።
በሀንጋሪም የስደተኞች መጠለያ (ካምፕ) ውስጥ ነበር የገቡት። በካምፑ ውስጥም ወደ ተለያዩ ሀገራት ለመሄድ የተዘጋጁ ወደ 28 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን አገኙ። በካምፑ በነበራቸው ቆይታ የሚሲዮን አስተማሪዎች ወደ እነርሱ በመምጣት የሥነልቦና ምክርና የኃይማኖት ትምህርት (መጽሐፍቅዱስ) ያስተምሯቸው ነበር።
አቶ አርጋው፤ በኃይማኖታዊ ትምህርቱ ተስበው ስደተኛ መሆናቸውን እስኪዘነጉ ነበር በዚያው መቆየቱን የመረጡት። አብረዋቸው የነበሩት ሁሉ በየተራ ሲሄዱ እርሳቸው አላስተዋሉም። አንድ አመት አለፋቸው። በኋላ ላይ ከካምፕ ወጥተው ወደ ከተማ ሄዱ። ሥራም ጀመሩ። እየሠሩ ለመማር መኖሪያ ፈቃድ ማግኘት ስላለባቸው ተንቀሳቀሱ። ተሳክቶላቸው ያሰቡትን አሳኩ። በባይብል ኮሌጅ ውስጥ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው፤ ለሦስት አመታት የኃይማኖት ትምህርት ተምረው በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቁ።
ትምህርት ከጨረሱ በኋላ ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀምና ለቁምነገር ለማዋል እንዳለባቸው ለራሳቸው ቃል ገቡ። ይህን ቃላቸውን የሚያፀናላቸው የግራጎናቸውን አገኙ። እርሳቸው በተማሩበት ኮሌጅ ከአሜሪካን ሀገር የመጣች ወጣት ጋር ተዋወቁ። ከወጣቷ ጋር ተዋውቀው ሃሳብ ሲለዋወጡ የተጎዳን ማገዝ፣ መርዳት የእርሷም ፍላጎት ነበር። በተለይ ደግሞ እንዲህ ያለውን በጎ ተግባር ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት እንደምትፈልግ በነገረቻቸው ጊዜ የበለጠ ተቀራረቡ።
ወጣቷ ስለኢትዮጵያ የምታውቀው ነገር ኖሯት አይደለም። ኢትዮጵያም የት እንደምትገኝ አታውቅም። ግን በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረ ድርቅ ብዙ ሰዎች መጎዳታቸውን በመስማቷ ነበር እንዲህ ያለው ሃሳብ ወደ አእምሮዋ የመጣው። ሰዎችን በሥነልቦና፣ በሕክምና በሌላም በምትችለው መርዳት ዘማሪ መሆን ፍላጎቶቿ ነበሩ። ዓላማቸው አንድ ሆነ፤ ትውውቁ ወደፍቅር ተቀየረ። ብዙም ሳይቆዩ ወደ ትዳር ገቡ። እኤአ 2005 ነበር ጋብቻቸውን የፈጸሙት። አቶ አርጋው ያኔ 22 አመታቸው ነበር።
አቶ አርጋው ከሚኖሩበት ሀገር የመኖሪያ ፈቃድም አግኝተው ስለነበር ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ጊዜ አልወሰዱም። ከባለቤታቸው በፊት ከሌሎች በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ሆነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ። እንደመጡም አዲስ አበባ ከተማ የክብር ዶክተር አበበች ጎበናን የሕፃናት ማሳደጊያ ጎበኙ። የብዙዎች እናት የሆኑትን የክብር ዶክተር አበበች ጎበናን በጎ ተግባር ካዩ በኋላ በዕድሜ ዘመናቸው በትምህርትና በሥራ ልምድ ያገኙት ተሞክሮ ተደምሮ እርሳቸው የሠሩትን ያህል ሆኖ እንዳላገኙት ነው በወቅቱ የተሰማቸው። በመቀጠል ሀዋሳም ሄደው ነበር።
ከሀገር ቤት መልስ ከባለቤታቸው ጋር በውጭ ሀገር አልቆዩም። ጋብቻቸውን በአሜሪካን ሀገር ካደረጉ በኋላ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት። እኤአ 2006 (ጥር 1997 ዓ.ም)። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሀዋሳ ውስጥ እየኖሩ ነው። አቶ አርጋው ባለቤታቸውን ይዘው ወደ ሀገር ሲመጡ ፈተናው ከቤተሰባቸው ነበር የጀመረው።
ባዶ እጃቸውን መምጣታቸው ብቻ አልነበረም የውጭ ዜጋ አግብተው መምጣታቸው ጭምር ነበር ያስወቀሳቸው። ቤተሰብ እነርሱንም ወደ ውጭ ያወጣል ብለው ሲጠብቁ እንዳሰቡት ባለመሆኑ ነበር ቁጣቸው የበረታው። የኃይማኖት ተቋማት ጭምር ነበር ከውጭ ሀገር መመለሳቸውን ያልደገፉላቸው። ሃሳባቸውን የሚረዳላቸው ሰው ለማግኘት ጊዜ ወስዶባቸዋል።
ይሄ ሁሉ ግን ጥንካሬን እንጂ ከዓላማቸው ወደ ኋላ እንዲሉ የሚያደርጋቸው አልነበረም። ባልና ሚስቱ መኖሪያቸውን ካመቻቹ በኋላ እየተጋገዙ ያሰቡት በጎ ሥራ ውስጥ ገቡ። ወደ ሥራው ሲገቡም ባንክ ውስጥ ገንዘብ አስቀምጠው ሳይሆን ልባቸው ውስጥ ትልቅ እምነት አስቀምጠው በፍላጎት ብቻ እንደገቡበት የሚናገሩት አቶ አርጋው፤ እርሳቸው ሲበሳጩ ሚስታቸው እየደገፈቻቸው፤ ሚስታቸው ሲከፉ ደግሞ ተስፋ እየሆኗቸው የጀመሩትን ለመቀጠል ይተጋገዙ ነበር።
የበጎ ተግባር ሥራቸውን ለማከናወን ሲንቀሳቀሱ 2000 ዓ.ም ሚሊኒየም የሚከበርበት ወቅት ነበር። መንግሥትም ጎዳና ላይ ልጆች እንዳይኖሩ ከጎዳና የማንሳት ሥራ ይሠራ ስለነበር ፍላጎታቸው ከመንግሥት እቅድ ጋር የተስማማ ሆኖ አገኙት። ሀዋሳ ከተማ ላይ ቤት ተከራዩ። በተለያየ ምክንያት ወደ ጎዳና የወጡ ልጆችንም ሰብስበው በተከራዩት ቤት ውስጥ በማኖር የሚያስፈልጋቸውም ነገር አሟልተው ለማስተማር እንቅስቃሴ ጀመሩ። በወቅቱም ከ8 አመት እስከ 17 አመት ዕድሜ ያላቸው 27 ልጆችን ነበር ከጎዳና ላይ ያነሱት።
አቶ አርጋው እንዳሉት፤ ልጆቹ ከባድ ሱስ ውስጥ የነበሩ በመሆናቸው ከሱስ አላቆ፤ ከመጥፎ ተግባራቸው መልሶ መልካም ዜጋ እንዲሆኑ ለማድረግ ፈታኝ ነበር። መማር የሚፈልገው ትምህርትቤት እንዲገባ፣ በአነስተኛ ንግድ ላይ መሰማራት የሚፈልግ ደግሞ እንዲሠራ እንደየፍላጎታቸው ለማገዝ ጥረት አደረጉ። ልጆቹ እንደፈለጉት ሊሆኑላቸው አልቻሉም። ከእነርሱ ይልቅ ጎዳና ላይ በነበሩ ጊዜ የሚያዟቸውን ነበር የሚሰሙት። በድብቅ ከእነርሱ ጋር ይገናኛሉ። አምጡ የሚሏቸውንም እየወሰዱ ይሰጧቸው ነበር። ልጆቹ ከቀድሞ ሕይወታቸው ሊቀየሩ አልቻሉም። በራሳቸው ጊዜም ወደነበሩበት ጎዳና ተመለሱ።
አቶ አርጋውና ባለቤታቸው ጎዳና ላይ የወጣን ሳይሆን መመለስ ሳይሆን፣ ወደ ጎዳና የሚያወጣቸውን ምክንያት ከምንጩ በማድረቅ ልጆችን መታደግ ወደ ሚለው ሥራ ገቡ። ልጆች ለምን ወደ ጎዳና እንደሚወጡ ለመገንዘብ ቻሉ። በብዛት ለጎዳና ተጋላጭ የሆኑባቸውን አካባቢዎችንም ለዩ። ልጆቹ በምግብ ማጣት ጎዳና እንደሚወጡ ካረጋገጡ በኋላ የትምህርትቤት ምገባ ማካሄድ ጀመሩ። ለዚህ ሥራቸውም መንግሥት አካባቢዎችንና ትምህርትቤቶችን በመለየት አግዟቸዋል። ሐመር፣ ምዕራብ አባያና ሲዳማ ውስጥ 31ሺ700 ልጆችን በመመገብ ነበር ሥራ የጀመሩት። ለአምስት አመት በዚህ መልኩ በመሥራት ልጆች ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ታድገዋቸዋል።
በዚህ መካከል ሐመር አካባቢ የጥናት ሥራ ላይ የነበረ ወዳጃቸው በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የሚጎዱ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ልጆች መኖራቸውን ይነግሯቸዋል። በሐመር ሚንጊ በሚባለው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሕፃናት ይገደላሉ።ከወዳጃቸው በተሰጣቸው ሃሳብ መሠረት አካባቢው ላይ በመሄድ ልጆችን ለማትረፍ ተንቀሳቀሱ።
በወቅቱ በቦታው ሲደርሱ በሚንጊ የሚገደሉ እስኪወለዱ ድረስ የሚጠበቁ አስር እርጉዝ ሴቶችን ነበር ያገኙት። ከግድያ ለማትረፍ ይመለከታቸዋል ያሉትን አካላት በሙሉ ማነጋገሩን ተያያዙት። ግን እንዳሰቡት አላተረፏቸውም። ተቀባይነትም አላገኙም። በዚህም የተለያየ ተጽእኖ ደርሶባቸዋል።
ቁጭትም፤ እልህም፤ ስለያዛቸው ጥረታቸውን ቀጠሉ። በአጋጣሚ በአንድ ሰው እርዳታ ከመገደል ተርፈው የተጣሉ ሰባት ልጆችን ሰብስበው መረዳት ቻሉ። አሁን ላይ የተለያየ ጉዳት ያለባቸውን ጨምሮ የሚረዷቸው ቁጥራቸው ጨምሯል። 115 የሚሆኑት በተከራዩት ቤት ውስጥ የሚያግዟቸው ሲሆኑ፤ ከ60 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በውጭ የተለያየ ድጋፍ የሚደረግላቸው ናቸው።
ከነዚህ ውስጥም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ተመርቀው ሥራ ይዘው እራሳቸውን መርዳት የጀመሩ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል የሆኑ ዜጎችን ማፍራት ችለዋል። እንዲህ ያለውን ሥራ የሚሠሩት በሀገር ውስጥም በውጭም የተለያዩ ሰዎችን ድጋፍ በመጠየቅ ነው።
አሁን ከሚረዷቸው በላይ ለማገዝ የቦታ ጥያቄ ከፍተኛ ፈተና ሆኖባቸዋል። ለገቢ ምንጭና ድጋፍም ለሚያደርግላቸው መኖሪያ የሚሆን ሕንፃ በመገንባት እነርሱ ባይኖሩ እንኳን ድጋፉ ዘላቂ እንዲሆን ፍላጎቱ ቢኖራቸውም ተባባሪ ባለማግኘታቸው ውስን ሰዎችን በቤት ኪራይ ውስጥ ለመርዳት መገደዳቸውን ነው አቶ አርጋው የሚናገሩት። የሚችሉትን ከማድረግ ወደኋላ እንደማይሉ ግን ተናግረዋል።
በግለሰብ ደረጃ የሚሠሩት በጎ ሥራ ተጽእኖ መፍጠር ቢችልም፤ ለሀገራዊ ችግር መፍትሔ የሚሆን ነገር ግን መፍጠር እንዳልቻሉ የሚሰማቸው አቶ አርጋው ከበጎ አድራጎት ሥራው የመነጨ ሌላ በጎ ሥራም ፈጥረዋል። ሰላም ከሰፈነ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮች ይፈታሉ የሚል እምነት አላቸው። ዜጎች ሃሳብ የሚያዋጡበት የሰላም ባንክ እንዲኖር እየተንቀሳቀሱ ነው።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዓላማው በሀገር ሰላም እንዲኖር ነው። የሰላም ባንኩ ሀገር አሁን ከምትገኝበት ችግር እንድትወጣ የሚያስችል የእርቅ፣ የፍቅር፣ የአንድነት ሃሳብ ሁሉም ዜጋ እንዲያዋጣ ዕድል የሚያመቻች ነው። በተለይም ጎረቤት ከጎረቤቱ ሰላም መፍጠር ከቻለ ሀገር ሰላም ትሆናለች ይላሉ። በሰላም ባንኩ አማካኝነት የማኅበረሰብ የጋራ ውይይት መድረክ በማዘጋጀትና በተለያየ መንገድ ነው ሥራውን ለመሥራት ነው ያቀዱት። ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ ሊያቀራርብ የሚችል በቀን ተሰይመው የሚታወሱ መርሐግብሮች እንዲኖሩም ለማድረግ ነው ፍላጎታቸው።
ለአብነትም የመታረቅ፣ የጎረቤት ቀን እያለ በየቀኑ የሚካሄዱ መርሐ ግብሮች በተከታታይ ይተገበራሉ። ሥራውን ለመሥራት የሚያስችላቸው ፈቃድ ከማግኘት ጀምሮ የቅድመዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ነግረውናል። መላው ማኅበረሰብ የዚህ የሰላም ባንክ አካል እንዲሆን ነው ፍላጎታቸው። ‹‹ሰላም የሁሉም ፒኤልሲ መሆን አለበት›› ይላሉ።
ሰላም ባንክ በውስጡ ብዙ ሥራ እንዳለውና የመንግሥት እገዛም እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። የውስጥንም የውጭ ጠላቶችን ለማሸነፍም ያግዛል ብለው ያምናሉ።
አቶ አርጋው አየለ የአቤነዘር ሰፖርቲቭ ኤንድ ዲቨሎፕመንት አሶሴሽን መሥራች እንዲሁም የግሎባል ፒስ ባንክ ሃሳብ አፍላቂና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው የመሪነቱን ሚና ይወጡ እንጂ ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ከጀርባቸው እንደሚያግዟቸው ነው የነገሩን።
ስለልጆቻቸውም እንደነገሩን፤ ልጆቻቸው የወላጆቻቸውን ሃሳብ የሚደግፉና የሚያግዙ ናቸው። ውጭ ሀገር የመኖር ቀርቶ ረዘም ላለ ጊዜ እንኳን ለመቆየት ፍላጎት የላቸውም። ልጆቻቸው የሚኮሩባቸውና ሥራውንም እንደሚያስቀጥሉ ይተማመኑባቸዋል።
ልጆቻቸው ከሚረዷቸው ልጆች ጋር ቤተሰብ ሆነው ያደጉ በመሆናቸው ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር መልካም የሆነ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው ያስቻላቸው መሆኑም አቶ አርጋው አጫውተውናል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም