ጀልዱ፡- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚፈጀው 63 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሽኩቴ – ጩልቴ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የመንገድ ግንባታው መጀመርን ባበሰሩበት ወቅት እንዳስታወቁት የመንገድ ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ ክልሉና የፌዴራል መንግስት በጋራ ይሰራሉ።
መንገዱን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ወጭ ተመድቦላቸው የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ለአንድ ሰዓት እንኳን መቋረጥ እንደሌለባቸውና በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታውቀው ‹‹ለሙግት ጊዜ የለንም›› በሚል አስተሳሰብ እንደሚከናወኑ ርዕሰ መስተዳደሩ አስገንዝበዋል። በዚህም መልኩ ፕሮጀክቶቹን በቅርበት እንደሚከታተሉ ቃል ገብተዋል።
የወሰን ማስከበርና በአካባቢው የሚገኙ የድንጋይና የአፈር ግብዓት አቅርቦቶች ፕሮጀክቶችን የሚያጓትቱ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመው ነዋሪው በዚህ ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል። በዚህም የወጣቶች በሥራው ላይ በመሳተፍ፤ ዕውቀት በመቅሰም ለሃገር ዕድገት እንዲተጉ ተሳትፎ አቶ ሽመልስ አሳስበዋል፡፡
አቶ ሽመለስ አክለውም የፕሮጀክቱን ባለቤት አቶ ገምሹ በየነን እንደ ሃገር እየሰሩት ላለው ሥራ ምስጋና አቅርበዋል። የመንገድ ግንባታውም በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ እንዲያጠናቅቁ ለአቶ ገምሹ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ወጣቶችንም የሙያ ባለቤት በማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኜ እንደተናገሩት የመንገድ ሥራው ዳንዲ፣ ጀልዱና ግንደ በረት ወረዳዎችን የሚያገናኝ ሲሆን ለመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱም መንግስት አንድ ቢሊዮን 267 ሚሊዮን 54 ሺ 518 ብር በጀት መድቧል።
የመንገድ ሥራው ገምሹ በየነ ለተባለ የሃገር ውስጥ ተቋራጭ የተሰጠ መሆኑንና ሥራውም በሁለት ዓመት ከስምንት ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ኢንጅነር ሃብታሙ ጠቁመው የመንገዱ ስፋት በከተማ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 19 ሜትር በገጠር ደግሞ አስር ሜትር መሆኑን አመልክተዋል።
መንገዱ ከዚህ ቀደም ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ መሰረተ ልማት ያልተዘረጋበትና በጠጠር መንገድ ደረጃ እንደነበር ያስታወሱት ኢንጂነሩ በአሁኑ ጊዜ ወቅት አስፋልት ማደጉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
በፕሮግራሙ ላይ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የአካባቢው አርሶ አደሮችና ወጣቶች የመንገድ ስራው የረጅም ጊዜ ጥያቄያቸው እንደነበርና ምላሽ አግኝቶ ማየት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል ወጣት ማሞ ቶሎሳ “አያቶቻችን እንደሚነግሩን ስንቅ ይዘው ሁለት ቀን የእግር ጉዞ በማድረግ አምቦ ከተማና የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚሄዱ ነግረውናል።አሁን መኪና ቢገባም መንገዱ በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ በዋጋም በጊዜም እየተጎዳን ነው” ብሏል።
በግንደ በረት ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ባልቻ ጉዲሳም ለአንድ ኩንታልና ለራሳቸው እስከ ሁለት መቶ ብር ወጭ በማውጣት ለገበያ በማጓጓዝ ብዙ ችግሮችን እንዳሳለፉ በማስታወስ አሁን የመንገዱ ሥራ ሲጀመር በማየታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።በሥነ ሥርዓቱ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ የኦሮሚያና የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011
ለምለም መንግስቱ