የከተሞችን አቅም ለማሳደግ የሚተገበረው መርሀ ግብር

የከተማ ነዋሪውን ማህበረሰብ ያሳተፉ የከተማ መሰረተ ልማት ሥራዎች በሀገሪቱ በበርካታ ከተሞች ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ። የመንገድ፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች ልማት፣ ከተሞችን ለኢንቨስትመንት እና ለነዋሪው ምቹ የማድረግ ሥራዎችም በፕሮግራሙ እየተሰሩ ይገኛሉ። 30 በመቶ ማህበረሰቡ የተሳተፈበት እና 70 በመቶ በዓለም ባንክ ድጋፍ እየተከናወነ የሚገኘው የከተሞች መሰረተ ልማት ፕሮግራም ዋና ትኩረቱ የከተሞችን አቅም ማሳደግ ነው። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በ117 ከተሞች መተግበር የጀመረው ፕሮግራም ከትግራይ ክልል ውጪ በሌሎች ክልሎች ከተሞች በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። በዋናነትም የከተሞችን አቅም የማሳደግ እና የራሳቸውን የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ እንዲጨምሩ እንዲሁም ለዜጎች የሥራ እድል እንዲፈጠር ያለመው ፕሮግራም በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በኩል ተፈፃሚ እየሆነ ይገኛል።

በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶችና ከተማ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሄለን ደበበ፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ፕሮግራሞች ተቀርጾ መንግሥትን ውጤታማ ከማድረግ ጎን ለጎን በከተሞች አቅም ግንባታ ላይ ያተኮረ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም እየተሰራ መሆኑን ይገልፃሉ። ከእነዚህ መካከል አሁን እየተከናወነ የሚገኘው፣ ከ2011 ዓ.ም እስከ 2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ታስቦ የተጀመረው ፕሮግራም ነው። ‹‹ይሁንና በኮቪድ፣ በሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም በሌሎች የተለያዩ የውስጥ ጉዳዮች ምክንያት በሚፈለገው መልኩ ለማስኬድ አልተቻለም። በዚህም የተነሳ አንድ ዓመት ተራዝሞ እስከ በተያዘው በጀት ዓመት እየተተገበረ ይገኛል›› በማለት የከተሞች አቅም ግንባታ እና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች በሚገኙ 117 ከተሞች ላይ ተጨባጭ ውጤቶች የሚጠበቅበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የፕሮግራሙ ዋና ዓላማም ከተሞች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በዘላቂነት እየተደገፉ የከተሞችን የኑሮ ችግሮች እንዲፈቱ እና በዘላቂነትም አቅማቸው አድጎ በራሳቸው ገቢ የከተማውን ፍላጎት ወይንም አጠቃላይ ካፒታላቸውን ሊሸፍን የሚችል ገቢ መሰብሰብ እንዲችሉ ትኩረት በማድረግ የሚሰራበት ነው። የከተማ ነዋሪው ማህበረሰብ ከእቅድ እስከ ተግባር ድረስ በሚገኙ ሂደቶች ተሳትፎ እንዲያደርግ በእቅድ፣ በማሳተፍ፣ በሳይት መረጣ፣ በመዋጮ፣ ጥራትን በማስጠበቅ ማሳተፍ አንዱ የስራው ሂደት አካል መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በየዘርፉ የማህበረሰብ ተሳትፎ እያደገ የመጣ መሆኑን ይገልጻሉ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ተያያዥ የአሰራር ሥርዓት እና የህብረተሰበ ተሳትፎ በምን መልኩ ይመራል የሚል መመሪያ አዘጋጅቶ በከተሞቹ ተደራሽ አድርጎ 30 በመቶ እና ከዚያ በላይ በማዋጣት በየአካባቢው በሚሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ። መፀዳጃ ቤቶች፣ የመታጠቢያ ቦታዎች፣ የቆሻሻ መጣያ ቦታዎች ዝግጅትም የፕሮግራሙ አካል ሆነው በስፋት የሚሰሩ ናቸው። በሌላ በኩል የከተሞችን የማዘጋጃ ቤት ገቢ የመሰብሰብ አቅም ማሳደግ አንዱ የፕሮግራሙ አካል ነው። በ117 ከተሞች ፕሮግራሙ አሁን ያለበት ግምገማ ሲደረግ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች አሉት ይላሉ።

አንዱ የፕሮግራሙ አቅም ግንባታ ሥራ ሲሰራ የከተሞች የገቢ ምንጭ የትኛው ነው? የበለጠ ገቢ ሊገኝ የሚችለው የትኛውን አገልግሎት ማስፋት ሲቻል ነው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ጥናት ይደረጋል። ጥናቶቹ በሚያመላክቱባቸው ዘርፎችም የተለያዩ የገቢ ማሻሻያ ርዕሶች በየምክር ቤቱ እየፀደቁ ተግባራዊ እየሆኑ መጥተዋል። በዚህ ሂደት በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑ ከተሞች በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገቢ የመሰበሰብ አቅም ላይ መድረሳቸውን ይገልፃሉ።

ሌላኛው የፕሮግራሙ አካል የተሻሻለ መሰረተ ልማት ለከተማ ማቅረብ እና ሲስተም መዘርጋት መሆኑንም ይናገራሉ። ከዚህ አንፃርም ፕሮግራሙ ሲጀመር በከተሞቹ የነበረው በዋናነት የከተማ መሰረተ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ የሥራ እድል በስፋት እንዲፈጠር ይፈለጋል። ይህም በከተሞቻችን የሥራ አጥነት ችግር በስፋት ያለ በመሆኑ ነው። ከአካባቢው ጋር ተስማሚ የሆኑ ኢንቨስትመንቶችም በፕሮግራሙ የተካተቱ ናቸው።

በፕሮግራሙ ባለፉት አምስት ዓመታት አንድ ሺህ 353 ኪሎ ሜትር የኮብልስቶን መንገዶች ተሰርተዋል። በየዓመቱም ጥገና ለሚያስፈለጋቸው ጥገና የሚደረግበት አሰራር ተዘርግቷል። የግራቭል (መንገድ የሚከፈትባቸውና በቀጣይ ለኮብልስቶን ወይም ለአስፋልት የሚያድጉ) 914 ኪሎ ሜትር መንገዶች ተሰርተዋል።

በፕሮግራሙ የግራቭል መንገዶችን በመስራት እና ለአስፓልት ግንባታዎች ዝግጁ በማድረግ ቀጣይ የአስፓልት ንጣፍ ሥራ እና ሌሎች ዋና ዋና የመንገድ ይዘቶችን፣ በግራና በቀኝ ዳር ያሉ የውሃ ማፋሰሻዎችን፣ የእግረኛ መንገዶችን እና የመንገድ አካፋዮች ሁሉ ከተሰሩ በኋላ የአስፓልት ንጣፉን በከተማው ወጪ የሚሰራባቸው ሁኔታዎች አሉ።

ከዚህ አንፃርም ውጤታማ ሥራ የሰሩ ከተሞች መካከል ጅግጅጋ፣ ሀዋሳ፣ ቢሾፍቱ፣ ጎንደር ከተሞችን ጨምሮ በርካታ ከተሞች ተስፋ ሰጪ ስራዎች መሰራታቸው በዓለም ባንክ፣ በከተማና መሰረት ልማት ሚኒስቴር፣ እንዲሁ በፓርላማም በተለያዩ አካላት ምልከታ ተደርጎበት ጥሩ አፈፃፀም ተመዝግቧል።

በፕሮግራሙ ትኩረት ተደርጎ የሚሰራው ሌላው የውሃ ማፋሰሻዎች ሥራ መሆኑን ሲያስረዱ፤ አብዛኞቹ የሀገራችን ከተሞች ከውሃ ማፋሰሻ አንፃር ጉድለት የሚታይባቸው ናቸው። በዚህም 974 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፍሳሸ ማስወገጃዎች ተሠርተዋል።

በፕሮግራሙ ከተሞችን ለኢንቨስትመንት እና ለነዋሪው ምቹ ከማድረግ አኳያም ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውንም ይናገራሉ። ከዚህ ሥራ አንፃርም በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአብዛኛው ከተሞች ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጡ ያሉባቸው ሁኔታዎች አሉ። በፕሮግራሙ 205 ሄክታር የአረንጓዴ ስፍራዎች እና ፓርኮች የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች በባቱ፣ በጅማ፣ ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ ከተሞችን ጨምሮ በአብዛኛዎቹ ከተሞች ተከናውነዋል። እነዚህ ስራዎች ሲሰሩም የመንገድ ላይ መብራት ዝርጋታ፣ የገበያ ማዕከላት ግንባታ እና ሌሎች በርካታ ተያያዥ ስራዎች ከመንግሥት ጋር በጋራ ፋይናንስ ተደርገው የሚሰሩ ናቸው።

ከዓለም ባንክ በሚገኘው በጀት በተጨማሪ ከተሞች እና ክልሎች ለፕሮግራሙ የየድርሻቸውን መዋጮ ያደርጋሉ። ከዚህ አኳያም ባለፉት አምስት ዓመታት 859 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር በፕሮግራሙ ተግባራዊ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዚህም ውስጥ 691 ሚሊዮን ዶላሩ ከዓለም ባንክ የተገኘ ሲሆን፤ ከከተሞች እና ከክልሎች መዋጮ ደግሞ 248 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር መዋጮ በማድረግ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በከተሞች ለመስራት የተቻለ መሆኑን ይገልጻሉ። ስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ያህል የህብረተሰብ ክፍሎች በፕሮግራሙ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

አጠቃላይ ፕሮግራሙ ካሳካቸው ግቦች መካከል በገንዘብ ሚኒስቴር የፖርቲፎሊዮ ግምገማ መሰረትም ሀገር ውስጥ ካሉ በርካታ ፕሮጀክቶች አኳያ ውጤታማ ፕሮጀክት መሆኑ የታየበት ነው። በአሁኑ ወቅትም ፕሮግራሙን በማጠቃለል ሁለተኛውን ዙር የከተሞች የአቅም ግንባታ እና የመሰረተ ልማት ፕሮግራም ለማስቀጠልም የቅድመ ዝግጅት እና የፕሮግራም ዲዛይን ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

በፕሮግራሙ አማካኝነት ከተሞችን ገቢ ከማሳደግ አንጻር አንዱ የፕሮግራሙ አካል ረጂና አጋር አካላቱ ለሁልጊዜ ድጋፍ እያደረጉ የሚቆዩ ሳይሆኑ የከተሞቹን አቅም የማሳደግ እና ራሳቸውን ችለው ገቢ የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው።

በእነዚህ የመሰረተ ልማት ድጋፎች ረጂ አካላት ጨርሰው ሲወጡ ከተሞቹ ወደኋላ እንዳይመለሱ ተጨባጭ የመሰረተ ልማት ስራዎቹ ከተሞቹ ላይ ሲሰሩ ከተወሰነ ጊዜ ድጋፍ በኋላ የከተማው ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም ያድጋል። በከተሞች መሰረተ ልማት ሲዘረጋ አካባቢው መኖሪያ ከሆነም መንገድ ሲወጣለት መብራት ሲዘረጋለት የውሃ አቅርቦት ሲሟላለት አካባቢው እድገት ያሳያል። በዚህ መካከልም የመሬት አጠቃቀሙ እየተቀየረ ይመጣል። ከተማውም መሬቱን በጨረታ፣ በምደባ እና በተለያየ መንገድ ሲሰጥ የመሬት ዋጋ ያድጋል። በአካባቢውም ከዚህ ቀደም መኖሪያ ከሆነ ወደ ንግድ ሲያድግ ብዙ ነጋዴዎች ይፈጠራሉ። ለሥራ አጥ ዜጎችም የሥራ እድሎች እንዲሁም ተጨማሪ ወደ ታክስ ሥርዓት የሚገቡ ሰዎች እና ቦታዎችም ይፈጠራሉ። በዚህ ሂደትም የከተሞች ገቢ እየጨመረ ይሄዳል።

በቋሚነትም መሬት ላይ የሚመጡ ማሻሻያዎች ከመሬት የሚሰበሰበውን ግብር በማሻሻል የሚያመጧቸው ለውጦች አሉ። ለከተሞች መሰረተ ልማት በተዘረጋ ቁጥር ለኢንቨስትመንት ሳቢ እየሆኑ ይመጣሉ። አዳዲስ የሚፈጠሩ የኢንቨስትመንት እድሎችን ተከትሎም ሰፊ የሥራ እድል ይኖራል። በአረንጓዴ ስፍራዎችና ፓርኮች ላይ የሚሰሩት ፕሮግራሞቹ ፕሮጀክቶቹ ከተጠናቀቁ በኋላ ማዘጋጃ ቤቶች ቦታውን እያስተዳደሩና የራሳቸውን ገቢ እንዲፈጥሩ ለማስቻል እንዲሁም የሥራ ዕድል ለሚፈጠርላቸው ወጣቶች የማስረከብ ሥራ ይሰራል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለፃ፣ ፕሮግራሙ ሁለት ዋና ዋና ምሰሶዎች አሉት። አሠራር ማዘመን እና የአቅም ክፍተትን መሙላት ነው። ከዚህ አንፃር የከተሞች የመረጃ አያያዝ፣ ፋይል የማደራጀት አቅም ላይ የነበረውን ክፍተት አቅም በመገንባቱና የምዝገባ ስራዎች በመጀመሩ እንዲሁም ወደ ዲጂታላይዜሽን ሥራ እየተቀየሩ በመምጣታቸው ምክንያት ወደ ታክስ ሥርዓት ያልገቡ ግለሰቦች እና ቦታዎች ወደ ታክስ ሥርዓት እንዲገቡም እድል እየተፈጠረ መሆኑን ነው ያስረዱት። ጥናቶች እየተደረጉ የማይሰበሰቡ ወይንም ገበያ አይገኝባቸውም ተብለው ችላ የተባሉ ጉዳዮች ላይም ትኩረት በማድረግ የመጡ ለውጦች ስለመኖራቸው ያምናሉ። ባለፉት አምስት የፕሮጀክት ዓመታትም በ117 ከተሞች ለ749 ሺህ 854 ዜጎች በቋሚና በጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

በፕሮጀክቱ የመጨረሻ ዓመት ለማሳካት ከታቀደው አንፃር እስካሁን ከ90 በመቶ በላይ ውጤት ማግኘት ተችሏል። ማሳካት ያልተቻለው ማነቆም ተገምግሟል። በበርካታ ከተሞች ላይ ፕሮግራሙ ተደራሽ መሆን ቢችልም እንደሀገር ከነበረው የሕግ ማስከበር ጉዳይ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል ፕሮጀክቱ በ2013 እና 2014 ዓ.ም መካከል ተግባራዊ መሆን አለመቻሉ ክፍተት የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሰላም ስምምነቱ በኋላም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ አጠቃላይ ግምገማ ተደርጎ ከተሞቹ ወደ ተግባር የሚገቡባቸው ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸው ተረጋግጧል። በመሆኑም በ2016 ዓ.ም ለትግራይ ክልል ገንዘቡ ተላልፎ አካላዊ ሥራዎቹ እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች መሬት ላይ እየተሰሩ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።

ሌላው ተግዳሮት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በተለይም ባለፉት ዓመታት በሀገር ደረጃ የግንባታ ቁሳቁሶች ዋጋ መጨመር ምክንያት በታቀደው መሰረት ማሳካት ያልተቻሉ ሥራዎች አሉ። እንዲሁም ከጥራት አንፃር እየተሻሻሉ የመጡ የመሰረተ ልማት ስራዎችና ማቴሪያሎች ቢኖሩም አሁንም ትኩረት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት በዓለም ባንክ የከተሞች ተቋማዊና የመሰረተ ልማት መርሀ ግብር (Urban Institutional and Infrastructure Development Program – UI­IDP) በኩል ገቢ መደረግ የሚገባው ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት አካውንት ሙሉ በሙሉ ገቢ ተደርጓል።

በትግራይ ክልል ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ከግንቦት ወር ጀምሮ ባለፉት ስድስት ወራት ሰፊ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። በፕሮግራሙ ስለሚሰሩ ስራዎች ከሁሉም የክልሉ ከተሞች ለተውጣጡ አካላት በዓድዋ ከተማ ሥልጠናዎች ተሰጥቷል።

በመቀጠልም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በገንዘብ ሚኒስቴር መካከል የተቋቋመ ቡድን በክልሉ በሚገኙ ከተሞች አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን ምልከታ አድርጓል። በየደረጃውም ስራውን የሚያረጋግጡ ኮሚቴዎች መኖራቸው ተረጋግጧል። ከዚህ ቀደም የተከፈቱ አካውንቶችም ኦዲት ተደርገው መዘጋታቸው እና ሌላ አዲስ አካውንት መከፈቱን እና መዋቅሮቹ ሥራ ላይ የሚውሉ መሆናቸው ፍተሻ ተደርጓል።

በተጠናቀረው መረጃ ባለፉት ስድስት ወራት በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ከሆኑ ከተሞች መካከል 272 ሚሊዮን ብር ወደ ትግራይ ክልል ተላልፏል። በዚህም የተለያዩ የመሰረተ ልማተ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከመስሪያ ቤቱም የተውጣጣ ቡድን በሳይት ላይ ይገኛል። የዚህ አፈጻጸም ከተገመገመ በኋላም የሁለተኛው ዙር ቀጣይ ቀሪ ገንዘብ የሚላክ መሆኑንም ይጠቁማሉ።

አሁን ላይ ከትግራይ ክልል ውጪ ያሉ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ከተሞች ገንዘቡ እየተላለፈ ሳይሆን የነበረውን ፕሮግራም የማጠቃለል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ይገልፃሉ። እስካሁን የተንጠባጠቡ ስራዎች በተለይ ሰፋፊ ፓርኮች፣ ደረጃውን የጠበቀ ትላልቅ ቄራዎች ባሉባቸው ከተሞች ከመጪው ሰኔ ወር በፊት እንዲጠናቀቁ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑንም አመላክተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን  የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You