አዳማ፡- የወጪ ንግዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍታኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የንግድ ሚኒስቴር የሴክተር መስሪያ ቤቶችን እና የክልል እንዲሁም የከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎችን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር እንደገለጹት፤ የወጪ ንግዱ በተለያዩ አሳሪ ምክንያቶች ከዓመት ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱ አሳሳቢ ነው።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ ዋነኛ ምክንያት የግብርና ምርቶች በበቂ ሁኔታ መመረት አለመቻላቸው ፣ ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ እንዱሁም የማዕድን ምርት መቀነሱ ነው።በተለይ ኢትዮጵያ ትልቅ የውጭ ምንዛሬ ገቢ የምታገኝበት የማዕድን ንግድን በአግባቡ መምራት ባለመቻሉ እንደ አገር ትልቅ ገቢ እያሳጣ ይገኛል።
በተጨማሪ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በአግባቡ አለማስተዋወቅ ለገቢው መቀነስ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው የተናገሩት ወይዘሮ ፈትለወርቅ፣ በቀጣይ በአግባቡ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ተጨማሪ በቀጣዩ ዓመት የግብርና ምርት በብዛት ተመርቶ እና ስርዓት ባለው መልኩ በንግድ ሂደቱ እንዲያልፍ ለማድረግ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
ስለቀጣዩ ዓመት ዕቅድ የተናገሩት ወይዘሮ ፈትለወርቅ እንደገለጹት፤ ዘርፉን ለማሻሻል ከአደረጃጀት ጀምሮ የሚስተካከሉ ስራዎች መኖራቸውን እና ይህም በመንግስት ደረጃ እንዲታወቅ መደረጉን ጠቁመዋል።በሌላ በኩል ምርት በሚፈለገው ደረጃ እንዳይመረት የሚያደርጉ እክሎችን ለመቀነስ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።እንደ ንግድ ሚኒስቴር መረጃ የወጪ ንግዱ በተለይ በማዕድን ዘርፍ አሽቆልቁሏል።በተለይ በ2006 ዓ.ም. 430 ሚሊዮን ዶላር የነበረው የወርቅ ማዕድን ገቢ በ2011 ዓ.ም ወደ 32 ሚሊዮን ዶላር አሽቆልቁሏል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011
እፀገነት አክሊሉ