– በ526 ሚሊዮን ብር የራሱንና ህንፃና ላብራቶሪ እያስገነባ ነው
አዲስ አበባ፡– የአገሪቱን አንኳር የጤና ችግሮች ሳይንሳዊ እልባት እንዲሰጣቸውና አገሪቱ በጤና የተሻለ እምርታ እንድታስመዘግብ ትኩረት ማድረጉን የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ። 526 ሚሊዮን ብር የተበጀተለትና በሦስት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የተቋሙ ላብራቶሪ በቀጣይ ለሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች የላቀ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጿል።
በአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ደጅይጥኑ ሙላው በተለይም ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለፁት፤ ተቋሙ ለግማሽ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ ጉልህ የጤና ችግሮች በምርምር ላይ በመመስረት መፍትሄ እንዲያገኙ በርካታ ሥራዎች ሲያከናውን ቆይቷል።
በተለይም የህክምና ሥርዓትና ሥራዎችን ማሻሻልና ምርምሮችን በተሻለ መንገድ ማከናወን፣ አዳዲስ የምርምር ሥራዎችን ማስተዋወቅ፣ አዳዲስ ምርምሮችን መከወን እንዲሁም የኢትዮጵውያን ጤና ባለሙያዎች ብቃትና ክህሎት እንዲያድግ ድጋፍ ማድረግ ነው።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ 526 ሚሊዮን ብር የተበጀተለትና በሦስት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ህንፃ ግንባታ እየተከናወነ ነው።ይህም ተቋሙ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው የምርምር ሥራዎች የላቀ ድርሻ ይኖረዋል።
በአሁኑ ወቅት በአዳማ ከተማ የወባ ምርምር ማዕከል ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ አያሌ የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን በአገሪቱ አራቱም ማዕዘናት በስፋት የመንቀሳቀስ ውጥን አለው። ምንም እንኳን ኢንስቲትዩት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ቢሆንም ችግሮችም መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ለአብነትም የምርምር ሥራዎች ረጅም ጊዜ መውሰድና ለህብረተሰቡ በሰፊውና በወቅቱ አለመድረስ፣ የቴክኖሎጂ እጥረት፣ በሚፈለገው ደረጃ የምርምር ሥራዎችን አለማካሄድ ብሎም ተቋሙ የሚያከናውናቸው ሥራዎችን በሰፊው አለመታወቃቸው መሆናቸውን ገልፀዋል።
የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት እ.ኤ.አ 1970 የተመሰረተ የምርምር ተቋም ሲሆን፤ በኢትዮጵያ መንግስት ብሎም በሲውዲን እና ኖርዌይ መንግስታት የተራድኦ ድርጅቶች የፋይናንስ ድጋፍ ይደረግለታል። ኢንስቲትዩቱ በርካታ ኢትዮጵውያን በጤናው ዘርፍ በውጭ ሃገር የትምህርት ዕድል እንዲገኙ እና በዘርፉ የሚሰሩ ምርምሮችን በመደገፍና በማስተዋወቅ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር