አዲስ አበባ፡- ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ለማቅረብ ሊውል የሚችል አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ከመንግስት እንዳልተከፈለው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አስታወቀ።የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ ድርጅቱ በቅድሚያ በቂ የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ እና መጠየቅ እንዳለበት ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት የግዥ ዘርፍ ተወካይ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ እንደሻው ለገሰ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ሲቋቋም ለድርጅቱ በጥሬ ገንዘብ ሊከፈል ከሚገባው ሶስት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ውስጥ 792 ሚሊዮን ብር እስከአሁን አልተከፈለም።
በተጨማሪ በ2006 እስከ 2007 ድረስ ዓ.ም በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረው የገበያ ችግር በመመርኮዝ ገበያ ለማረጋጋት ታስቦ በመንግስት ትዕዛዝ ፓልም ዘይት እንዲገዛ ተብሎ ነበር።በወቅቱ ድርጅቱ በቀድሞው ስሙ ጅንአድ እየተባለ በሚጠራበት ጊዜ ከእራሱ ካዝና ያወጣው 597 ሚሊዮን ብር እስከአሁን አልተከፈለውም።በመሆኑም በአጠቃላይ መንግስት ላይ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ክፍያ ለድርጅቱ መክፈል ይጠበቅበታል።
ገንዘቡ እንዲከፈል ለመንግስት በተደጋጋሚ ጊዜ ጥያቄ መቅረቡን የተናገሩት ምክትል ኃላፊው፤ እስከአሁን ድረስ ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘቱ በተቋሙ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።ድርጅቱ ገንዘቡን ከመንግስት ባለማግኘቱ የተነሳ በኢንዱስትሪ ግብአት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጉድለት እያደረሰበት መሆኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ ከተሰጠው ግብአትን ለኢንዱስትሪዎች የማቅረብ እና የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለተጠቃሚዎች ከማድረስ አኳያ ድክመት ታይቷል።በተለይ ከፍተኛ አቅም የሚጠይቀውን ጠገራ ብር/የብረት ማዕድን/ በኢንዱስትሪዎች ፍላጎት ልክ ማድረስ አልተቻለም።
በተመሳሳይ ኬሚካሎችን ጨምሮ የተለያዩ ግብአቶች ለኢንዱስተሪዎች አቅርቦ የግብአት ችግሩን ለማቃለል ገንዘቡ ወሳኝነት አለው።እስከአሁን ከባንክ በመበደር እና የድርጅቱን ገንዘብ በማብቃቃት የኢንዱስትሪዎች ግብአት ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ እመቤት ሙሉ መኮንን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ድርጅቱ ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍ ሲቋቋም ዋና ዓላማው የገበያውን ክፍተት መነሻ በማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ምርቶችን ገዝቶ በመጋዘን ማከማቸትና ገበያውን የማረጋጋት ሥራዎች ማከናወን ነው።በመሆኑን ተቋሙ ገንዘቡን ቢያገኝ የሚያውለው ለኢንዱስትሪዎች ጥቅም በመሆኑ ሊለቀቅለት ይገባል፡፡
እንደ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት መረጃ፤ ተቋሙ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በአዲስ መልክ ተደራጅቶ የግብዓት አቅርቦት ስራ ከጀመረበት ጥር 2008 ጀምሮ እስከ 2010 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ድረስ ከብር 1ነጥብ3 ቢሊዮን በላይ ዋጋ ያላቸው የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በዱቤ ሽያጭ ውል አቅርቧል።ድርጅቱ በተለይ የተዳመጠ ጥጥ፣ ኬሚካል፣ ብረት፣ ስንዴ እና የቆዳ ግብአቶችን እንዲሁም የኢንዱስትሪ ጨው እያቀረበ ይገኛል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ ለኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ጥያቄ በጻፈው ደብዳቤ መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ103 ሺ የአሜሪካን ዶላር በላይ ፈቅዶ እና የዘይት በጀት እጥረት በሌለበት ሁኔታ ከድርጅቱ አካውንት ገንዘብ መወሰዱ ግልጽ አይደለም ብሏል።
በመሆኑም የዘይት ሽያጭ ላለመሆኑና ወጪው የታዘዘበትና ላለመተካቱ በመረጃ ስላልተደገፈ ውሳኔ መስጠት ያስቸግራል የሚል ምላሽ ሰጥቷል።በመሆኑም ድርጅቱ የተሟላ ኦዲት ሪፖርትና መረጃ እንዲያቀርብ አሳስቧል።በተጨማሪ ድርጅቱ እንደ አዲስ ሲቋቋም የነበረው የትርፍ ድርሻ እና ለመንግስት የተከፈለ ሂሳብ በተመሳሳይ በቂ የኦዲት ሪፖርት ያስፈልጋቸዋል ብሏል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011
ጌትነት ተስፋማርያም