– በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ ለወጣቶች ገቢ የሚሆኑ ችግኞች ይተከላሉ
– 20 ሚሊዮን የአፕል፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ጌሾ እና ሌሎችም ችግኞች ተዘጋጅተዋል
አዲስ አበባ፡– በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ 20 ሚሊዮን ዘለቄታዊ የኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ መቀመጫውን ባህርዳር ያደረገው የአባይ ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
የአባይ ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ የወንድወሰን መንግስቱ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል በሚገኙ የዓባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተተክለው እንዲጸድቁ ጥረት ይደረጋል።ለዚህም 20 ሚሊዮን የተለያዩ አይነት ፍራፍሬዎች እና ወደ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን የሚያፈሩ እጽዋት ችግኞች ተዘጋጅተዋል፡፡
እንደ አቶ የወንድወሰን ገለጻ፤ ለወጣቶች የምርት ተጠቃሚነት ብሎም ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ታቅደው የተዘጋጁት ችግኞች በኦሮሚያ ክልል እና በአማራ ክልል 20 ወረዳዎች ላይ ይተከላሉ። በአባይ ወንዝ ተፋሰስ በሆኑት በርብ፣ መገጭ፣ በርሲና፣ አርጆ- ዴዴሳ እንዲሁም ፊንጫ ወንዝ እና ግድቦች አካባቢ በክረምት ወቅት ከፍተኛ የተፋሰስ ልማት ስራ ይከናወናል።
በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን፣ ጅማ ዞን እና ቡኖ-በደሌ ምስራቅ ወለጋ ዞን ዋነኛ የኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ችግኝ ተከላ የሚካሄድባቸው ቦታዎች ናቸው።በአማራ ክልል ደግሞ በደቡብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር እና ሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ቋሚ የፍራፍሬ ተክሎችን ጨምሮ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸው የሚያይሉ እጽዋት ለተከላ መዘጋጀታቸውን አቶ የወንድወሰን ተናግረዋል፡፡
በእያንዳንዱ አካባቢ የሚተከሉ ችግኞች የነዋሪዎችን እና ወጣቶቹን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ የወንድወሰን፣ አንዱ አካባቢ የአፕል እና ማንጎ ችግኞችን ሲፈልግ ሌላው ደግሞ የጌሾ እና ሌሎች ገቢ የሚያስገኙ ችግኞች መጠየቃቸውን አስረድተዋል። ችግኞቹ መትከል ብቻ ሳይሆን ተከልለው አስፈላጊው ጥበቃ የሚደረግባቸው በመሆኑ በቀጣይ ተጓዳኝ ስራዎች ለማከናወን እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።
እንደ አቶ የወንደወሰን ከሆነ፣ እስከአሁን በተሰሩ የአባይ ተፋሰስ ልማት ስራዎች በተለያዩ አካባቢዎች 34ሺ 600 ሄክታር መሬት ከንክኪ ተከልሎ ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል።በተከለለው ስፍራም ከአራት ሺ በላይ የተለያዩ ክልል ወጣቶች በንብ ማርባት፣ ከብት ማደለብ እና ቋሚ ፍራፍሬዎችን ለገበያ በማቅረብ ስራ ተሰማርተዋል። አሁንም ችግኝ በሚተከልባቸው አካባቢዎች ተመሳሳይ የስራ እድሎች ለወጣቱ እንደሚፈጠር ከየአካባቢው አመራሮች ጋር ግንኙነት ይደረጋል።
እንደ የአባይ ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት መረጃ፤ የችግኝ ተከላው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ ያስጀ መሩት እና በአገር አቀፍ ደረጃ አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተያዘው እቅድ አንድ አካል ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011
ጌትነት ተስፋማርያም