አምቦ፡- የግብርና ሥራን ለማዘመን ተስፋ የተጣለበት የላይኛው ጉደር የመስኖ ፕሮጀክት በጉደርና ጥቁር እንጭኒ አካባቢ ተጀመረ።
ፕሮጀክቱን ለማስጀመር ትናንት በስፍራው ተገኝተው የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ 3ነጥብ4 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተያዘለት ገልፀዋል።ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 4ሺ926 ሔክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው ሲሆን ከ10ሺ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል።
በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዬ ወረዳ በሚገኘው ፋጦ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ ከመስኖ ፕሮጀክቱ ባሻገር የአካባቢውን የንፁህ ውሃ አቅርቦት ችግር እንደሚያቃልል የገለፁት ሚኒስትሩ፣ የግብርና ስራዎችን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ አርሶ አደሩን በዓመት ሦስት ጊዜ ለማምረት እንደሚረዳው ተናግረዋል።የላይኛው ጉደር መስኖ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ፤ ከአርባ ሜትር በላይ ጥልቀት፣ ከ273 ሜትር በላይ ስፋትና 57ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ይይዛል ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ በመርሐግብሩ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የፌዴራል እና የክልሉ መንግስት የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ መካከለኛና አነስተኛ ግድቦችን በተለያዩ አካባቢዎች ለመገንባት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።
የላይኛው ጉደር የመስኖ ፕሮጀክትም ከግብርና በተጨማሪ ለአሳ እርባታና ለቱሪዝም ምቹ በመሆኑ ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንደሚችል ተናግረዋል።የአካባቢው ህብረተሰብም የግድቡ ግንባታ እንዲፋጠን የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
ግንባታውን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን እንዲሁም የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ያከናውኑታል።በሦስት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011