አዲስ አበባ:- የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ባዘጋጀው የጸረ ጥላቻ ንግግርና የሃሰት መረጃ ረቂቅ አዋጅ ላይ በተደረገው ውይይት ረቂቅ አዋጁ የዜጎችን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ይገድባል በሚል የሚቀርቡ ስጋቶች ተገቢ እንዳልሆኑና የማንንም መብትና ነፃነት እንደማይገድብ ተገለፀ።
የጥላቻ ንግግር እና አደገኛ የሀሰት መረጃዎችን ማሰራጨትን ለመከላከል ያስችላል ተብሎ በተዘጋጀው በዚህ አዋጅ ላይ በትናንትናው እለት ኤሊሌ ሆቴል የሚዲያ ተቋማት፣ የህግ ባለሙዎች፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ አክቲቪስቶች እና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን የተለያዩ የድጋፍና የተቃውሞ ሀሳቦች ተንጸባርቀዋል፡፡
የቀድሞ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ አቶ ታምራት ነገራ እንደገለጹት፣ አሁን ለተከሰተው የጥላቻ ንግግር ዋና መደላድሉ ህገ-መንግስቱ የፈጠረው የብሄር ጉዳይ ነውና መጀመሪያ እሱ ነው ለውይይት መቅረብና መሻሻል አለበት።ይሄኛው አዋጅ ከዛ ቀጥሎ ነው ሊታይ የሚገባው።በዚህ አገር መናገር በሚያስፈልግበት በዚህ ሰአት ይህን አዋጅ ማውጣት ተገቢ ያልሆነ እርምጃ ነው፡፡
አክቲቪስት አቶ ስዩም ተሾመ በበኩሉ፣ ፍፁም እውነትና ፍፁም ውሸት የሚባል ነገር የለም።በመሆኑም ይህ አዋጅ የተዘጋጀው ሰዎችን ስጋት ውስጥ ለመክተት ነው ብለዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ አስተያየታቸውን ከሰጡት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መካከል አቶ ካሳ ዘገየ እንዳሉት ደግሞ፣ ተቋም እየወደመ፣ የሰው ህይወት እየጠፋ፣ ንብረት እየተዘረፈና አገር እየፈረሰ ይህ ረቂቅ አዋጅ አያስፈልግም ማለት ስህተት ነው።በመሆኑም ቶሎ ፀድቆ ወደ ስራ ሊገባ ይገባል፡፡
በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት አቃቢ ህግ የሆኑት ወይዘሮ አመልማል በቀለ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ስጋቱ ተገቢ ያልሆነ ስጋት ነው።ከሁሉም በፊት መጀመሪያ ረቂቅ አዋጁ ለምን አስፈለገ የሚለውን ማየት ይገባል ።ረቂቅ አዋጁ ያስፈለገበት አብይ ምክንያት አሁን እየታዩ ያሉትን የጥላቻና ጥላቻ አዘል ንግግሮችን፣ የሀሰት መረጃ ስርጭቶችንና የመሳሰሉትን ከመቆጣጠር አኳያ የህግ ክፍተት በመኖሩ ነው፡፡
እንደ ወይዘሮ አመልማል ገለጻ፣ ረቂቅ አዋጁ የጋዜጠኞችንም ሆነ የሌሎችን ሀሳብን የመግለፅ ነፃነትንም ሆነ መረጃ የማሰራጨት መብትን በፍፁም አይገድብም።ለዚህም “ልዩ ሁኔታዎች” አለው።አፋኝም አይደለም፣ በህገ- መንግስት የተደነገጉትን መብቶችንም የሚፃረር አይደለም።
ረቂቅ አዋጁ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል ለሚላቸው ከማህበራዊ አገልግሎት መስጠትና ቀላል እስራት ጀምሮ እስከ አምስት አመት ፅኑ አስራት፤ ከብር ሶስት ሺህ ጀምሮ እስከ አስር ሺህ ብር ድረስ ቅጣት የሚያስከትል፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ህግ አንቀጽ 486 አዋጅንም የሚሽር መሆኑም ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011
ግርማ መንግሥቴ