መቐለ:- በአክሱም ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ የጉብኝት ቆይታ ጊዜን እስከ አምስት ቀን ከፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂና ቱሪዝም ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአርኪ ዮሎጂና ቱሪዝም ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ተክለብርሀን ለገሠ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ የቱሪዝም ገቢ የሚገኘው በቱሪስት የቆይታ ጊዜና በቱሪስት ብዛት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የቱሪስት ብዛትም ሆነ የጉብኝት የቆይታ ጊዜ ጥቂት ነው።
እንደ አገር ያለውን ችግር ለመፍታት ጭምር በአክሱምና አካባቢዋ ያሉትንና እስካሁን ያልተዋወቁትን የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች በማስተዋወቅ የቱሪስቱን የጉብኝት የቆይታ ጊዜ ከፍ ለማድረግ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ እየሰራ ይገኛል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርስነት ተመዝግቦ ካለው የአክሱም ሀውልት በተጨማሪ ሌሎች የመዳረሻ ስፍራዎች በአክሱም በብዛት
ቢገኙም በቱሪስቶች የመጎብኘት እድል የላቸውም። በመሆኑም ቱሪስቶች የአክሱምን ሀውልት ለመጎብኘት የሁለት ቀናት ብቻ የጊዜ ቆይታ ይኖራቸዋል። ይህ የጉብኝት ጊዜ ቆይታ ማነስ ደግሞ ከቱሪዝም በሚገኘው ገቢላይ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡
በአካባቢው ያለው ሀብት ከሁለት ቀናት በላይ የሚያስቆይ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመውሰድ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ማስፋት በሚያስችል ሁኔታ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን፤ ሌሎች የመዳረሻ ስፍራዎችን በማስተዋወቅ የቱሪስት የጉብኝት የቆይታ ጊዜን ከሁለት ቀናት በአማካኝ ወደ አምስት ቀናት ለማሳደግ ከክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ቱሪስቶችን እስከ አምስት ቀን ድረስ ማቆየት የሚችለው የቱሪዝም መስህብ አገ ልግሎት ላይ ከዋለ የአገርን ገጽታ ይበልጥ ለማስተዋወቅም ሆነ ኢኮኖሚውን ለማሳለጥ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል። ለዚህም የሌሎች ባለ ድርሻ አካላት እገዛ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። አክሱም፣ የሓና አድዋን ሳይጨምር ወደ 60 የሚጠጉ የቱሪስት መዳረሻዎች በአካባቢው መኖራቸውንም ዳይሬክተሩ አክለዋል::
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011
አዲሱ ገረመው