የታላቁ ዓድዋ ድል ምስጢር

(ክፍል አንድ)

“የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም፣ ለድንቅ ታሪካችን የሚመጥን ውብ ሥራ!”በሚል ርዕስ ጋዜጠኛ ኤልያስ መሠረት በቴሌግራም ገጹ ባጋራው መልዕክት፤ብዙ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ሲፃፍ እና ሲነገር በቅኝ ግዛት ያልተገዛን እና ነፃነታችንን ጠብቀን የኖርን ሕዝቦች መሆናችን ጎላ ብሎ ይጠቀሳል። ይህን አኩሪ ታሪካችንን ለራሳችን ለማየትም ይሁን ለጎብኚዎች ለማሳየት ግን አለ ተብሎ የሚጠራ የታሪክ መዘክር አልነበረንም። የዛሬ 6 ዓመት ገደማ ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩ ጋዜጠኞች የዓድዋ ድልን የሚያሳይ ነገር እንዳሳያቸው ጠይቀውኝ ግራ ቢገባኝ ብሔራዊ ሙዚየም ይዣቸው ስሄድ አስታውሳለሁ። በወቅቱ ይህን ትልቅ ታሪክ የሚዘክር ሙዝየም ሀገራችን ውስጥ ባለመኖሩ ሲገረሙ ታዝቤ ነበር ይለናል።እኔም ለዚህ ክብር የበቃው የዓድዋ ድል የተገኘበትን ምስጢር ከበይነ መረብ ቀራርሜ እንዲህ ምንጭ ጠቅሼ ላጋራችሁ ወደድሁ።

የጦርነት ታሪክ ፀሐፍት በአንድ ነገር ይስማማሉ። አንዲት ሀገር በጦር ሜዳ አሸናፊ የምትሆነው በፍትሐዊ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ከሆነች ብቻ ነው። ጦርነቱ ፍትሐዊ ካልሆነ ግን መቼም ቢሆን አሸናፊ አትሆንም። ይህን እሳቤ ይዘን ወደ ዓድዋ ጦርነት ገፊ ምክንያቶች ስናመራ ኢትዮጵያ በዚያ ዘመን የገባችበት ጦርነት ፍትሃዊ ሆኖ እናገኘዋለን ይሉናል ጥበቡ ከበደና ስለአባት ማናዬ የተባሉ ጸሐፍት ባስነበቡን ማለፊያ መጣጥፍ።

እንግሊዝ ምሥራቅ አፍሪካን በተለይም የዓባይ ወንዝ ተፋሰስን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ካላት ፍላጎት የመነጨ በመሆኑ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን በተደረገው የቅኝ ግዛት መስፋፋት እንግሊዝ፣ፈረንሳይ ፣ ቤልጂየም እና ኢጣሊያ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። በእርግጥ የኢጣሊያ አመጣጥ የሀገር ውስጥ ፖለቲካዊ ገና የውህደት ዑደቱን ባለማጠናቀቁ ዘግየት ብላ ነው የተቀላቀለችው።

እንግሊዞች እና ግብፆች በሱዳኖች የደረሰባቸውን ከበባ ለመቋቋም ከኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ጋር ተፈራረሙ፤ የሒዎቴ ወይም የዓድዋ ስምምነትን። በሱዳን ከበባ የተፈፀመባቸው የግብፅ እና የእንግሊዝ ወታደሮች በኢትዮጵያ በኩል አድርገው በሰላም መውጣት እንዲችሉ ማድረግን ታሳቢ በማድረግ። በዚህ ስምምነት እንግሊዝ ለኢትዮጵያ ወደቦችን ክፍት ለማድረግ ተስማምታለች።

ምሥራቅ አካባቢ ግብፅ ተቆጣጥራው የነበረውን ወደብም ለቃ ለመውጣት እንዲሁ። እንግሊዝ ግን ለኢትዮጵያ የገባችውን ቃል አጥፋ በተቃራኒው ምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ተገዳዳሪ ሆና የመጣችባትን ፈረንሳይን ለመግታት ኢጣሊያን ጋበዘቻት። ኢጣሊያን በእንግሊዝ ግብዣ የምገባባት የወዲያው ምክንያት ፈረንሳይን መግታት የሚል ቢሆንም የሮም ቄሳር ኃይላት ግን የራሳቸውን ቀመር ስሌት እያሰሉ ነበር። በእንግሊዝ ጋባዥነት ወደ ኢትዮጵያ ሰሜናዊ ግዛት የገባችው ኢጣሊያ ከአፄ ምኒልክ ጋር በውጫሌ ስምምነት ፈረመች።

ያ ስምምነት ግን በመርዝ የተለወሰ ሀረግ እና አንቀጾችን ይዞ ነበር። አንቀፅ 17 የኢጣሊያንኛ ቋንቋ ይዘቱ ፍፁም የተለየ ነበር። ኢትዮጵያን በተዘዋዋሪ የኢጣሊያ የቅኝ ተገዥ ያደረገ ፍሬ ሀሳብ የያዘ ነበር። ኢትዮጵያ ነገሩን ውድቅ አደረገች ። አሁን ሁሉ ነገር ወደ ጦር አውድማ እየዞረ ነው። የቄሳር ኃይላት በዚያ ታላቂቱን ሀገር በቅኝ ግዛት መዳፋቸው ለማስገባት ከቋመጡ ከራርመዋል። ታላቁ አርበኛ ራስ አሉላ አባ ነጋ በዶጋሊ ያደረሰባቸውን ከባድ ኪሳራ እና ውርደት ለመበቀል አሰፍስፈው ተሰልፈዋል።

ታላቂቷ አፍሪካዊት ሀገር የምሥራቅ አፍሪቃዋ ኮከብ ደግሞ በታላቁ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ በኩል አዋጭ ያለችውን ዝግጅት ለአይቀሬው ጦርነት እያዘጋጀች ነው። ሀገራዊ ዝግጅቱ በንጉሠ ነገሥቱ በአፄ ምኒልክ የዘመቻና የጦርነት አዋጅ ይጀምራል።የአዋጁ ይዘት የዘመቻ ጥሪን ለኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎችና ለሹማምንቶች ኢትዮጵያ በጠላት ጥርስ ውስጥ መግባቷንና የቅኝ ተገዥነት ዕጣፋንታዋ መቃረቡን፣በሕዝቦች የተባበረ ክንድ ግን ጠላትን መመከት እና በቅኝ መገዛት እንደማይቻል የተገነዘቡት ንጉሠ ነገሥት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይህን ታላቅ የጦር ክተት አዋጅ አወጁ።

ከታሪክ መረጃ ምንጮች የምንገነዘበው የምንረዳውም የሩቁንም ሆነ የቅርቡን የዘማች ሠራዊት ኃይል በማደራጀት ከሸዋና ከአካባቢው የተነሳው ዘማች ኃይል ወሎ ወረ ኢሉ ላይ እንዲከት፣ ከጎጃም፣ ከደምቢያ፣ ከቋራ፣ ከበጌምድር እና ከጨጨሆ በላይ ያለውን ሀገር ሁሉ አሸንጌ ላይ እንዲከት፣ የሰሜኑንና የወልቃይት ጠገዴንም ሰው መቀሌ ላይ እንዲከት፣ የሐረር ዘማች በአዲስ አበባ በኩል ገና የጥቅምቱ ዘመቻ ሳይጀምር አዲስ አበባ ገብቶ ወረ ኢሉ እንዲከት፣ የወለጋው ሠራዊት መግባት የቻለው ገብቶ በክረምቱ በመስከረም ስለሚበረታ በውሃ ሙላት እንዲቆይ ተደርጓል።

ዋናው ቁም ነገር ግን አዋጁ ሀገራዊ ንቅናቄን መፍጠሩና መተግበሩ ስለነበር በትክክል ተተግብሯል ለማለት ይቻላል። ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ሃይማኖትህን እና ሚስትህን የሚሉ ግዝፈት የሚነሱ ጉዳዮችን ማካተታቸውን ስንመረምር ምን ያህል አርቆ አሳቢ መሆናቸውን እንረዳለን። ሰው በሚስቱ እና በሃይማኖቱ ከመጡበት ቀናኢ ነውና ! የዘመተው ሠራዊት ፍጹም ሕብረ ብሔራዊ ነበር። እገሌ እና እገሌ ሳይባባሉ ፈቃደኝነት ላይ በተመሠረተ የንጉሠ ነገሥቱን አዋጅ ተቀብለው በሀገራዊ፣ በወገናዊና በባህላዊ ጉዳዮች የጋራ ትስስር፣ የጋራ መግባባትና በኢትዮጵያዊነት ወኔ ተሞልተው ታሪክ ለመሥራት የተሰባሰቡ ዜጎች እንጂ ግዴታ፣ ኃይልና በወቅቱ ሕግ አስገዳጅነት የዘመቱ አልነበሩም።

ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውንና የሀገራቸውን የነፃነትና የሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ ያተኮሩ እንጂ በትናንሽ ቁርሾዎች ልዩነት ፈጥረው ከዋናው ሀገር የመጠበቅ ተልዕኮ ያፈነገጡም አልነበሩም። በዘመቻው ሂደት የታየው የጋራ ክተት ጥሪ፣የታየው የጋራ ዓላማ ፅናት የተሞላበት ረዥሙ የዘመቻ ጉዞ፣ ሣይቸኩሉ ሁሉንም በልባቸው አድርገው የጋራ ድል ማስመዝገቡ የዚያ የዓድዋ ዘመቻ የጦር አመራር የጥበብ የምክክር ብስለትና ብቃት ነበር። ይህ ባይሆን ኖሮ የዓድዋን ድል ማስመዝገቡ አስችጋሪ በሆነ ነበር።

የዘመቻ ስንቅ ሁኔታ፦ ከንጉሠ ነገሥቱ ወረገኑ፣ ከእቴጌይቱ ወረገኑ፣በግብር መልክ እንዲገባ በየደረሱበት አካባቢ ከተሰበሰበው የተለያየ የአቅርቦት አይነት ሌላ፣ ዋናው የስንቅ የጀርባ አጥንት ሆኖ ጦርነቱን በብቃት ለማሸነፍ የተቻለው ከዘመቻ ጉዞ ደርሦ መልስን በማካተት በተጨማሪም በውጊያዎችም ወቅቶችም ቢሆን የሕዝቦችን አስተዋፅኦ ይህ ነበር ብሎ መገመቱ ይከብዳል። በተለይ የትግራይ የጦር አውድማዎች አካባቢዎች የነዋሪዎችን ያላሰለሰ ድጋፍ መገመቱ አይከብድም። ወደርየለሽ የአቅርቦት መረባረብ ተደርጓል (ገብረ ሥላሴ ገፅ 227 _268)።

በዓድዋ ጦርነት የተሰለፈው ዘመቻ ሠራዊት የጦር ኃይሉና መሣሪያ አቅም፦ ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ሕዝቦች ተዋፅኦ የነበረ ሲሆን፤ እንደ ዘመኑ አሠራር በተዋረድ የዘመቻ ጥሪ ደርሷቸው የዘመቱ ነበሩ። ባሳለፉበት የውጊያ አውድማዎችና በተሳተፉበት የዓድዋ ግንባር ላይ በታሪክ ውስጥ ሊደመሰስ የማይቻለውን የዓለም፣ የአፍሪካ እና የኢትዮጵያን ጥቁር ሕዝቦች ድል እውን እንዲሆን አድርገዋል። የተለያዩ የዚያ ሠራዊት አመራርና አባላት በተለያዩ የጦር ሜዳዎች ውስጥ ወርቅ በእሳት ግሎ እንደሚፈተን በጦርነት የተፈተኑና የጦርነትን ምንነት አብጠርጥረው የሚያውቁ ነበሩ። በኢትዮጵያ ይሁን በኢጣሊያኑ ወገን የተለያዩ ካሊበር አቅም የነበራቸው መድፎች፣መትረየሶችና ሌሎች ነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች በሥራ ላይ ውለዋል።

የኢትዮጵያው ዘማች ሠራዊት የተወሰኑ ከባድ መሣሪያዎች ነበሯቸው። የመሣሪያዎችን ዝርዝርና አቅማቸውን፣ እንዲሁም በሁለቱም ጎን የነበረውን የጦር ኃይሉን አቅም በደንብ ማየት ይቻላል። የኢጣሊያኑ ተዋጊ 56 መድፎችን አሰልፏል። (በርክሌ) ሁለት የኢጣሊያን ባትሪዎች ከባድና ፈጣን ተወንጫፊዎችን እንደተጠቀሙ ዕይታውን ፅፏል። ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ላይ ያሰለፉት 42 መድፎች ነበሯቸው። የወቅቱ ወታደራዊ ጠበብቶች ግን ለዓድዋው ድል ዋነኛ ምክንያት የከባድ መሣሪያው መታጠቅ አልነበረም። የደነደነው ኢትዮጵያዊ የጀግኖች ወኔ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዘማች ሠራዊት መድፎች ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ ነበሩ። በግዥ፣ በስጦታ፣ አፄ ዮሐንስ ከጉንዳት ና ከጉራዕ ጦርነት ወቅት ከግብፆች የማረኳቸው መትረየሶችና ሌሎች ጠመንጃዎች ሁሉ ተደራጅተው ለውጊያ አገልግሎት ውለዋል። ዋናው ቁም ነገር ኢትዮጵያ የአውሮፓ ሠራሽ ከባድ መሣሪያዎችን ዓድዋ ጦርነት ላይ መጠቀሟን መገንዘብ ነው። የኢትዮጵያዊያኑ የመድፍና የማሽን ጦር መሣሪያዎች በብቃት የመጠቀሙ ሁኔታ በወቅቱ ወታደራዊ ጠበብቶች ተገምግመው፣ የግምገማው ውጤት ሲገለፅ የዓድዋ ውጊያዎች የአፍሪካ ኃይል የሆነው የኢትዮጵያ ዘማች ሠራዊት በቅኝ ገዥዎች ሠራሽ መሣሪያዎች ቅኝ ገዥውን ኢጣሊያንን አንበረከከ እንጂ የቅኝ ግዛት ናፋቂዋ ኢጣሊያ በቅኝ ገዥዎች ሠራሽም ይሁን በራሷ በሠራችው መሣሪያ ባለውጤት እንዳልነበረች የዓድዋ ተራሮች ገሃድ አድርገውታል።

በኢትዮጵያ በኩል በፈረንሣይ ገበያዎች በኩል የገቡትን ከባድ መሣሪያዎችን መጠቀም መቻሉን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ተዋጊዎች መሣሪያዎች የኢጣሊያን ኃይል ፀጥ ማሰኘታቸው የኢጣሊያኑ ኃይል ከአላጄና ከመቀሌ የወጊያዎች ሽንፈትና ውድቀት ያለመማራቸውን የሚያረጋግጥ ነበር። በኢትዮጵያ በኩል ከዘመናዊ ጦር መሣሪያዎች በተጨማሪ ጦርነቱ እየተጋጋለ ሲሄድ ጎራዴና በለበን ነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎችን በመጠቀም ያደረጉት ወሳኝ ውጊያ የዓድዋን ጦርነት ድል እንዲያጠናቅቁ ረድቷቸዋል።

የዓድዋ የጦር አውድማ እና ሦስቱ የውጊያ ቀጣ ናዎች፦ ቀዳሚው ፈጠን ብሎ ወደ ዓድዋው ውጊያ ቀጣና የገባው በጀኔራል አልቤርቶኒ ሥር ቀዳሚውን የኢጣሊያን ባታሊዮን መርቶ የነበረው ማጆር ዴሚኒኮ ትሩኢቶ አስቸጋሪውን የ10 ማይል ጉዞ በመጓዝ እኩለ ሌሊት ላይ ገንደብታ ገባ። የዚህ ኃይል እንቅስቃሴ በየትኛውም ደረጃ ከጀኔራል አልቤርቶኒ ሀሳብ ጋር ስለልተናበበ ሌሊቱን በጨረቃ እየገፋ ሊነጋጋ ሲል በኢትዮጵያ ጦር ካምፕ ውስጥ መሆናቸውን ብቻ ተገነዘቡ።ኢትዮጵያዊያን በዕሩምታ ተኩስ ጀመሩ። ጠዋት 12 ሰዓት ላይ የተወሰኑ ደቂቃዎች ሲጨምሩ የዓድዋው ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ላይ ተጀመረ።

ከኢትዮጵያውያኑ 1 ሺህ የሚሆኑት የማጆር ቱሪቶ የመጀመሪያው አስካሪ ባታሊዮን 950 ሰው ብቻ ስለ ነበር ለቁጥር አለመቀራረባቸውን ወዲያኑ በቅፅበት ስለተረዱ፣ ከበባን እንደ አንድ ጥሩ ስልት ወሰዱ። ከወገኑ የራቀው የቱሪቶ ሠራዊት ከጥቅም ውጭ ሆነ። ሠፊ ርቅት በመከሰቱ ጀኔራል አልቤርቶኒ ለማጆር ቱሪቶ መድረስ ከፈለገ ብዙ ሠራዊቱን ለመስዋእትነት ይዳርጋል። የኢትዮጵያውያኑ ከበባ ቱሪቶ ወደ ኋላ እንዳያፈገፍግ፣ ጄኔራል አልቤርቶኒም ወደ ፊት እንዳይገሰግስ አስገደዳቸው።

በሁለት ኮረብታዎች (አምባ ምድር) በየሥፍራው የመጠቀም ስልት፦ የግራው ኮረብታ ጠላትን ከግራ በኩል እንዳያጠቃ የተፈጥሮ መከላከያ ሆኗል።የቀኙ ኮረብታም በቀኝ በኩል ያለው ጠላት እንዳያጠቃ ይከላከላል። ሁለቱን ኮረብታዎች ያገናኘው መሬት ኢትዮጵያውያን መድፎችን ጠምደውበታል። ከዚህ ገዥ መሬት ላይ የአልቤርቶኒ ኃይል ሲንቀሳቀስ በግልፅ ይታያል።

ስለዚህ ሠራዊት ከሠራዊት ጋር በግላጭ መሬት ላይ መዋጋት፣ በከባድ መሣሪያ ሽፋን መስጠት ሆነ። ኢትዮጵያውያኑ የፈለጉትና ያሰቡት ያ ዓይነት አሰላለፍ እንዲሆን ነበር። ሆነላቸው። ከዚህ የቅንጅትና የስልት ሕይወት ውስጥ መድፈኞች፣ባትሪዎች መቀሌ ላይ ከነበራቸው አሰላለፎች ጋር በተመሳሰለ መልኩ ዓድዋም ላይ ውጤታማነታቸውን አሳዩ።የሥራ ክፍፍል ተደርጎ መድፈኞችን ማበረታታት፣ እቴጌ ጣይቱ 5 መድፎችን ሥራዬ ብለው በአስተኳሽነት በመሳተፍ ውጊያ ላይ ነበሩ። የራስ መኮንንና የራስ ሚካኤል 15 ሺህ ሠራዊት አልቤርቶኒን በቀኝ በኩል ከበቡት፣ በተመሳሳይ ሰዓት የንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ የዋግሹም ጓንጉልና የእቴጌ ጣይቱ ኃይል አልቤርቶኒን በግራ በኩል ከበቡና የኢጣሊያን ሠራዊት በከበባ አጣብቂኝ ውስጥ በማስገባት ወቀጡት።

ይህ የጦር ታክቲክ የኢትዮጵያ የረዥም ዘመን የውጊያ ስልት ስትራቴጂና ስልትን መጠቀም በትክክል የተተገበረ ነበር። ይህም ኢጣሊያኖች እንዲበታተኑ፣አቅማቸው እንዲዳከም ያደረገ ስልትና ቅንጅት በመሆኑ የተቀረው ብዙኃኑ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጊዜና እስትንፋስ አግኝቶ ወደ ውጊያው እምብርት ለመንቀሳቀስ ቻለ። 2ኛው ጄኔራል ዳቦርሜዳ ለአልቤርቶኒ እርዳታ በመስጠት ወደ ውጊያ በቀኝ በኩል ሲገባ በማርያም ሻዊት በኩል ወደ ዓድዋ ፈጥኖ ሲንቀሳቀስ ሌላው ጄኔራል አርሞንዲ ከገንደብታ በፍጥነት ዳቦርሜዳ የለቀቀውን ሥፍራ በመዝጋት ላይ እያለ ዳቦርሜዳ ራሱ አቅጣጫ በመሳት ወደ ግራ ማጥቃት ሲገባው ወደ ቀኝ ተንቀሳቀሰ። የኢትዮጵያውያን ቅንጅት እና ታክቲክ፡ ቶሎ በፍጥነት የኢጣሊያን የአሰላለፍ ምስቅልቅልነትን ተረዱ።

ጊዜ ሳይባክን ስህተቱን ተጠቀሙበት። የዳቦርሜዳ ኃይል ከአልቤርቶኒ ጋር አለመቀናጀቱ ግልፅ ሆነላቸው ማለት ነው። ዳቦርሜዳ ምንም ጥቃት እንደማያደርስ የተረዱት ኢትዮጵያውያን 15 ሺህ እግረኛ ተዋጊዎችን በማስገባት አልቤርቶኒንና ዳቦርሜዳን እንዲነጣጠሉ አደረጉ። ይህ 15 ሺህ ኃይል አደገኛ ኃይል በመሆኑ የዳቦርሜዳን በ3 ሰዓት ከ30 ደቂቃ አካባቢ ለባራቴሪ ባደረገው ሪፖርት ገልጿል። እነዚያ 15 ሺህ ወታደሮች የራስ መኮንን እና የራስ መንገሻ ሠራዊት ነበሩ። ከ3 ሰአት 30 በኋላ ይህ የሁለትዮሽ ኃይል የኢጣሊያንን የአልቤርቶኒን ተዋጊ ኃይል ወደ ሦስት ስፍራ ተነጣጥለው ዋጋ ቢስ እንዲሆኑ አደረጋቸው።

የእቴጌ ጣይቱ ሠራዊት በራስ መንገሻና በራስ መኮንን ሠራዊት የተቆራረጡትን ኃይሎች ማውደም ጀመረ።እንደ እውነቱ ከሆነ በሁለቱም ባላንጣዎች ላይ ኃይለኛ ዕልቂትን ያሳየ የተጋጋለው የዓድዋ ጦርነት ኢጣሊያኑ ከጧቱ 12 ሰዓት ተኩል ላይ የጀመሩት ማጥቃት ወደ 3 ሰዓት ከ30 ደቂቃ አካባቢ ተፍረከረኩ። መረጃዎች የሚያስቀምጡት በቅንጅት ማፍረክረክ የተባለው ኢትዮጵያዊው የዚያ ዘመን ታክቲክ ይህ ነበር። በመጨረሻ ክፍል መጣጥፍ ደግሞ ቀሪ የጦርነቱን ስትራቴጂና የዓድዋን ድል አንድምታ እጋራለሁ። ምንጫችን ስለአባት ማናዬን ፋና ቴሌቪዥን አመሠግናለሁ።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን የካቲት 13/2016

Recommended For You