. በአክሱም ሀዉልት ስር ዉሀ እየመነጨ በመሆኑ ቅርሱ የመውደቅ አደጋ ተጋርጦበታል።
የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ በማሳደግ ረገድ ትልቅ ድርሻ ላላቸው ቅርሶች መንግስት ተገቢውን ትኩረት እየሰጠ አለመሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።
በመቀሌ እየተካሄደ ባለው ሶስተኛው አገር አቀፍ የባህል ቱሪዝምና ስፖርት አመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባዔ ላይ በአክሱም ዩኒቨርስቲ የአርኪዎሎጂና ቱሪዝም ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት መምህር ተክለብርሀን ለገሰ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ መንግስት ለቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ትኩረት ባለመስጠቱ ቅርሶች ለጉዳትና ብልሽት እየተጋለጡ በዚህም ታሪክ እየጠፋና ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ እያደረገ ነው።
ቱሪስቶች ወደሀገር ከገቡ በኋላ ያላቸው የቆይታ ጊዜ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ ለዚህም በቱሪስት ቦታዎች የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የአስጎብኚ ድርጅቶች ደካማ መሆንና በባለሙያዎች አለመመራት፣ የጉብኝት ካርታና መረጃዎች በአግባቡ አለመዘጋጀት በምክንያትነት ከተጠቀሱት መካከል ናቸው።
በቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ ማነስ ምክንያት ቅርሶቹ በሚገኙበት አካባቢ የሚኖረው የህብረተሰብ ክፍልም ተጠቃሚ መሆን አልቻለም ያለው ጥናቱ ጎብኝዎቹ ለጥቂት ሰአታት ቅርሶችን ከተመለከቱ በኋላ እንደሚወጡም ተመላክቷል።
እንደ መምህር ተክለብርሀን ጥናት ቅርሶችን ለመጠገን እጅግ አነስተኛ ገንዘብ የሚያስፈልግ ቢሆንም ትኩረት በመነፈጋቸው ምክንያት ግን የጥገና ስራዎችን በጊዜው መስራት አዳጋች ሆኗል፤ ይህ ደግሞ ቱሪዝሙን ክፉኛ እየጎዳውና ዕድገቱ ቁልቁል እንዲሆን እያደረገው ነው።
የላሊበላ እና አክሱም ሀውልቶችን እንደ አብነት ያነሱት መምህሩ ቅርሶቹ ከሚያስገቡት ገቢ አንፃር ሲታይ ለጥገና የሚያስፈልገው ወጪ አነስተኛ ነው ነገር ግን ትኩረት በመነፈጉ የተነሳ ተገቢው ጥገና አልተደረገላቸውም ብለዋል።
መምህር ተክለብርሀን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት ደግሞ በአክሱም ሀውልት ስር ውሀ እየመነጨ በመሆኑ ቅርሱ የመውደቅ አደጋ ተጋርጦበታል፤ ክረምቱ ሳይገባ ለመጠገንም አልተቻለም ነው ያሉት።
ለጊዜያዊ መፍትሄ ይሆን ዘንድ ከሀውልቱ ስር የደረቅ አፈር ሙሌት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በኩል እየተከናወነ መሆኑን መምህሩ ተናግረዋል።
ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና የቱሪዝሙን እድገት ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማዳበርና ለቅርሶች ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ በጥናቱ ተጠቁሟል።
በድልነሳ ምንውየለት