የታላቁ ዓድዋ ድል ምስጢር

(የመጨረሻ ክፍል)

በመጀመሪያ ክፍል መጣጥፍ የጦርነቱን አነሳስና የጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን የውጊያ ስትራቴጂ አጋርቻለሁ። በዛሬው መጣጥፍ ደግሞ የቀሩ የውጊያ ስልቶችንና የዓድዋን ግዙፍ አንድምታ አወሳለሁ።

3ኛ የውጊያውን እምብርት የማፍረስ የመጨረሻው ታክቲክና ቅንጅት፦ የኢትዮጵያ ሠራዊት የአልቤርቶኒንና የዳቦርሜዳን የክፍተት ስህተት ተገንዝቦ በየስፍራው ጠላትን የመምታት አቅሙን በተግባር ባዋለበት በዚያች ሰዓት በወታደራዊ ጠበብቶች እይታ የኢትዮጵያ ሠራዊት ለሀገራቸው የዓድዋን ድል ማስመዝገባቸው የታወቀ ጉዳይ ሆኖ ነበር። የበርሃው መብረቅ የበጋው ብራቅ የዶጋሊው አራስ ነበር ራስ አሉላ አባ ነጋ በፍጥነት ይህ አጋጣሚ ሳይቆይ እንዲተገበር ወሳኝ የጦር መሪ ሆነዋል። ይህንን ጉዳይ ሲተገብሩ ራስ አሉላ ለንጉሠ ነገሥቱ ያስተላለፉት መልዕክት በመድፍ፣በመትረየስ፣በጠመንጃ ስለወጠርናቸው በአስቸኳይ የኦሮሞ ፈረሰኞች ከራስ ሚካኤል ጦር ውስጥ በብዛትና በፍጥነት አካባቢውን እንዲያጥለቀልቁትና ከምሥራቅ አቅጣጫ መንገድ ዘግተው በጨበጣ የኢጣሊያኑን ኃይል እንዲለቅሙ ብለው ስለተመካከሩ ውጊያዎቹ ድልን በድል ላይ ጨመሩ።ጦርነቱ አልቋል ውጊያዎች ግን ቀኑን ሙሉ ተካሄዱ።

ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተኩል ጀምሮ በሌላ አቅጣጫ ወደ ወጊያው የገባው የአርሞንዲ ሠራዊት በተራው ተመታ። በሁሉም አቅጣጫ በጥልቅት የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል በቀለበት ውስጥ በማስገባት ሙት፣ቁስለኛ፣ምርኮኛ ማድረጉን አረጋገጠ። ይህንን የመሰለ የውጊያ አቅም ተጠቅመው በጄኔራል ዳቦር ሜዳ ፣በጄኔራል አርሞንዲ፣በጄኔራል ኤሌና ተዋናይነት በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የሮማ ቄሳር ጦርነት ፣የቅኝ ግዛት ዓላማው አልቤርቶኒና ዓድዋ የሕልም እንጀራ ሆነ። የዓድዋ የድል የሕልም እንጀራ እንዲሆን አደረገው!!

ስለላ እና የዓድዋ ድል፦ በራስ አሉላ አባ ነጋ እና በራስ መንገሻ በኩል በቂ አቅም የነበራቸው እና ግሩም ሥራ የሠሩ የመረጃ ሰዎች ነበሩ። በሚስጥር የተዘረጋው የመረጃ መረብ ዕርዳታና ድጋፍ የኢትዮጵያ ዘማች ሠራዊት በኢጣሊያ የጠላት ሠራዊት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና እንዲያሳድር ረድቷል። በሻይ አውዓሎምና በራስ አሉላ እና በራስ መንገሻ ሥር የነበሩት ሌሎች ሰዎች የመሬትና የባህል እውቅት፣የቋንቋ ችሎታና ከኢጣሊያኑም ጋር በነበራቸው የውስጥ ለውስጥ የመረጃ ሥራ ብዙ ዘዴ በማካበት የሰጡት መረጃ ኢጣሊያኑን ሠራዊት በሚጎዳና የውጊያውን አጀማመር ኢትዮጵያውያኑን ዘማች ሠራዊት በሚጠቅም መልኩ በማድረጋቸው አስተዋፅኦአቸው እጅግ የጎላ ነበር።

የራስ ስብሀትና የደጃዝማች ሐጎስ ከኢጣሊያን ወገን ከድተው ወደ ኢትዮጵያ ሠራዊት መቀላቀል ብዙ መረጃዎችንም ይዞ ስለመጣ ሁኔታዎች ሁሉ ለኢጣሊያ ወራሪ ኃይል እንዳይመቻች አድርጎታል።የዘማቹ ሠራዊት ቆራጥነትና ብርታትም ሌላው ጀብዷዊ የታሪክ አንጓ ነው። ሠራዊቱ አልጋውን ለማቆም እንጂ ለመሸሽ አይፈልግም።አንዱ ወደ ፊት አንዱ ወደ ኋላ አይልም(መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፡የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ) ላይ እንደ ዘገቡት። ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ተስተውሏል።ኢትዮጵያዊ ፅናት በእጅጉ ተንፀባርቋል። በመላው ዓለምም አብርቷል።

የዓድዋ ድል ለእኛ ትውልድ የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድን ነው? ኢትዮጵያ አሁን ላይ በርካታ የውጭም የውስጥም ድጋቶች ተደቅነውባታል። የመፍትሔ መንገዶችን እያማተረች ፣የቢሆን መላምቶችን እያፍታታች ባለበት ወቅት በእርግጥ የዓድዋ ድል እና የዚያ ዘመን የነፃነት አርበኞች ምን መልዕክት ያስተላልፉልናል ብሎ መጠየቅ ብልህነት ይመስለኛል። እስኪ የእነርሱን አስደማሚ ጀብድ ጅማሮ እና ፍፃሜ ሰዓታት ላይ የነበሩ እልሆችን ከታሪክ ድርሳናት እንግለጥ።

ከዘመቻው ጉዞ ሂደት ጀምሮ እስከ ጦርነቱ መጨረሻ ድረስ ዝግመት፣ክፍተት፣ ቅፅበት መመካከርና መከባበር በስፋት የነበሩ ክስተቶች ናቸው። በጦርነቱ ወቅት አልጋ በአልጋ የሚሆን ነገር ስለማይኖር በእነዚያ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ታልፎ የዓድዋ ድል እውን ሆኗል። የእንጢጮን ተራራ በ27 ቀን በፀሐይ በሌሊት በመብራት የተገነባውን፣የተደለደለውን ትቶ እንደ ተመረዘ ጉሬዛ ከሜዳ ላይ ተዘርግፎ እንደ እህል ተወቃ። ስፍራውን ቢያበጁ፣መሣሪያ ቢያደራጁ ጉልበትና ብልሀት የእግዚያብሔር መሆኑ በዚህ ተገለጠ (ፀሐፊ ገብረ ሥላሴ ገፅ 257) አስፍረውታል።

ከጦርነት ድል በኋላ የተመላሹ ቁጥር ሳስቷል። ዘምተውና በውጊያው ከነበሩት ጀግኖች ውስጥ እነ ፊታውራሪ ገበየሁ ጎራው፣ደጃዝማች ጫጫ፣ደጃች ባሻህ አቦዬ፣ፊታውራሪ ተክሌ፣ቀኝ አዝማች ታፈሰና ሌሎች ያልተጠቀሱት ቁጥራቸው የበዛ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የዓድዋ ጦርነት ወኪል ዋልታና ማገር በነበሩበት ብዙኃን ውስጥ ወደ ቄያቸው አልተመለሱም። የድሉን ጎዳና አፋጥነው በዚያው በእነዚያ የጥቁር ሕዝቦች መመኪያ የዓድዋ ተራሮች ህያው ሆነዋል። ይህ ትውልድ ከቅድመ አያቶቹ እና አባቶቹ የሰነቁለትን አስተምህሮት በተራው ለወቅታዊው ችግሮች መፍትሄ ሊጠቀምበት ይገባል።

ትናንት ለዓድዋ ጦርነት መነሻ የሆነው የውሃ ጦርነት ዛሬም ለሌላ ጦርነት እያዘጋጀን ይሆን? ግብፅ እንደ እንግሊዝ ሱዳን እንደ ኢጣሊያ ጊዜው 19ኛው ክፍለ ዘመን አይደለም። 21ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ቴክኖሎጂ መር 4ኛው የኢንዱስትሪ አብዮት የተቀጣጠለበት። ምሥራቅ አፍሪካ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ ደግሞ ዛሬም እንደ ትናንቱ ተፈላጊነቱ እጅግ ያሻቀበበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ይህ ቀጣና ከግሪክ እስከ ሮማኖች፣ከኦቶማኖች እስከ ፈርኦኖች፣የቅኝ ግዛት እስከ ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ፣ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች እስከ ቀዝቃዛው ጦርነት ገፈት ቀማሽ ሆኗል። አሁን ደግሞ በአዲሱ የእጅ አዙር ጦርነት መዳፍ ውስጥ ለመግባት በወደብ እና ጦር ሰፈር ግንባታ ከኃያላን እስከ ህዳጣን ከነዳጅ ከበርቴዎች እስከ ኒዩክሌር አረር ባለቤቶች ከፍተኛ ርኩቻ እየተካሄደበት ነው።

በመጀመሪያ ክፍል መጣጥፍ የዓድዋ ጦርነት ስረ መሰረት መነሻ እንግሊዝ በኢጣሊያን በኩል የዓባይ ወንዝን የመቆጣጠር ህልም ነበር። የዓድዋ ጦርነት ዋና ግብ ጣሊያን የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት መመዝበር በተለይም የዓባይ ወንዝን ነበር። ለፋብሪካዎቿ ጥሬ እቃ ፍለጋ እና በቀጣናው ያላትን ተስፋፊነት እና ተሰሚነት ማጎልበቻ ነበር።ያኔ ጀግኖች አርበኞቻችን የኢትዮጵያ የነፃነት ንስሮች ከሁሉም የሀገራችን ክፍል ነጋሪት ጎስመው ወደ ዓድዋ ተመሙ። የቄራስ ኃይላት በጥሬ እቃ ምዝበራ የታወሩ ግን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያን በሚገባ ያላወቁት ሰላቶዎች በዓድዋ ተራሮች የኢትዮጵያን ጀግኖች ጎራዴ ፉጨት መቋቋም ተሳናቸው። የዓድዋ ተራሮችም ለእነዚያ ቄሳር ኃይላት ተላላኪዎች የጎን ውጋት ሆኑባቸው። ምዕራባዊያን ለረዥም ዘመን የዘሩት የሀሰት ተረክ በዓድዋ ባዶ ሆነ። ነጮች በጥቁሮች አይሸነፉም የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ለፈፋ በዓድዋ ባዶ ሆነ።

አፍሪካዊያን እና መላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ብሎም በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር የነበሩት ሌሎች ሀገራት ፓን ኢትዮጵያኒዝምን እየሰበኩ የቅኝ ግዛት ቀንበርን እስከ ወዲያኛው ጠረማመሱት። የጣሊያን የጥሬ እቃ እና የተፈጥሮ ሀብት ምዝበራ የባህል ክለሳ በዓድዋ ተደመሰሰ። የዓባይ ፖለቲካ ዛሬም ድረስ በቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች ተሸብቦ በአዲሱ የቅኝ ግዛት እሳቤ የተሸበቡት ፈርዖኖች። ዛሬም በ1929 እና 1959 ስምምነት የመሟገቻ እና የአሳሳች ዲፕሎማሲያቸው መጋመጃ አድርገው እየባዘኑ ነው። የግብፆች ግብ እንደ ጣሊያኖች የቅኝ ግዛት መንፈስ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት መመዝበር ነው።

ዓባይ ለኢትዮጵያ ወንዝ ብቻ አይደለም ባህል፣ሃይማኖት ፣ እምነት፣ፍልስፍና፣ ቅኔ እና አፈር ነው። ካይሮዎች ይህን በበላይነት ያለ ማንም ከልካይነት መዝረፍ ይፈልጋሉ። እርግጥ ሲዘርፉም ከርመዋል። ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጀመር ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አቋሟ ከኢትዮጵያ ጎን ነበር።ነገረ ኦማር ሀሰን አልበሽር በዳቦ አብዮት ከስልጣናቸው ሲፈነገሉ ውሃው ዲፕሎማሲም አብሮ የተቀለበሰ ይመስላል። ግብፅ እንደ ኢንግሊዝ ሱዳን እንደ ኢጣሊያ እየሆኑ መጥተዋል። በዚያኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዝ የዓባይን ወንዝ ሙሉ ለሙሉ በመቆጣጠር ሱዳን እና ግብፅ የሚገኙ የጥጥር እርሻ ልማቶቿን በማጎልበት ማችስተር እና ላንክሻየር ለሚገኙ የአልባሳት እና ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎቿ ጥሬ እቃነት በአስተማማኝ ሁኔታ የማቅረብ ህልም ነበራት። ይህን አካሄዷን ለመግታት ሌላኛው የዚያ ዘመን ተፎካካሪ ፈረንሳይ ጂቡቲ ላይ ሆና መስፋፋት ጀመረች።የፓሪስን መንገድ በኢጣሊያ የመዝጋት የእንግሊዝ ሴራ በኢትዮጵያ እውን ሆነ።

ኢጣሊያ ወደ ኢትዮጵያ ገባች ። ኢትዮጵያ እና ኢጣሊያ ጦርነት ውስጥ ገቡ በጦርነቱ አዳክሞ ዓባይን መቆጣጠር የእንግሊዝ ከመጋረጃው በስተጀርባ የነበረ እቅድ ነው። ዛሬ ደግሞ ግብፅ ሱዳንን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመላክ ሁለቱን ሀገራት ጦር ለማማዘዝ እያሰፈሰፈች ነው። መገናኛ ብዙኃኖቻቸው 24 ሰዓታት ስለ ሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብ በርዕሰ አንቀጽነት እየዘገቡት ነው።ሱዳንም ኢጣሊያንነቷን አጠናክራ የቀጠለች ይመስላል። ያ ኔ ኢጣሊያ የኢትዮጵያን ግዛት ወራ የእኔ ይዞታ ነው በሚል አፍራሽ አካሄድ ስትከተል ነበር። አሁን ደግሞ ሱዳን የኢትዮጵያን ግዛት ወራ እኔ ተወጋሁ እያለች የሴራ አቀነባባሪ ወኪሎቿን ከመጋረጃው በስተጀርባ ሆነው አይዞሽ የሚሏትን ወገኖች ድምፅ እና ድጋፍ ለማግኘት የአዞ እንባ እያባች ነው።

የሱዳን እና ኢጣሊያ ተመሳስሎ፦

ኢጣሊያ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የውሃ ፖለቲካ እና የስትራቴጂክ ቅርምት አፍሪካ ቀንድ ውስጥ የገባችው ገና ሀገረ መንግሥቷ የውህደት ጭቃውን ሳያደርቅ ነበር።ሱዳንም አሁን ላይ እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ ገና የሽግግር የፖለቲካ ትኩሳቷ እና የአልበሽር ዘመን ውልቃቶች ጥሩ ወጌሻ አግኝተው የሱዳናዊያን የምጣኔ ሀብት እድገት ጥያቄ በውል ምላሽ ሳያገኝ ነው። ያኔ እንግሊዝ ኢጣሊያንን ግፊበት እያለች የዲፕሎማሲ ሽፋን ሰጥታታለች። ዛሬም ግብፅ ሱዳንን ግፊበት እያለቻት ነው። የካይሮ ሰዎች ለካርቱም መለዮ ለባሾች በተለይም በአረቡ ዓለም የዲፕሎማሲ ድጋፍ እየሰጧቸው ነው።

የዓድዋ ድል ካርድ እዚህ ላይ መሳብ አለበት።እንዴት እና በምን መንገድ የሚለው ጉዳይ ግን ገና ብዙ ተንታኞችን ፡ምሁራን እና ፖሊሲ አውጪዎችን የሚያነጋግር ቢሆንም የእኔ የምላቸውን የሃሳብ ፍንጣቂዎች በተወሰነ ደረጃ ላቅርብ ።ዋናው ጉዳይ ለውሃ ዲፕሎማሲው መፍትሄ ስትራቴጂ መንደፍ ነው። ማርክ ዜቶን እና ዬሮን ዋረን (2006 _Hydro-hegemony – a framework for analysis of trans –boundary water conflicts) በሚለው ጥናታዊ ስራቸው የውሃ የበላይነት ዲፕሎማሲን ማጠናከር የሚቻለው በሦስት ጉዳዮች ላይ ጠንክሮ በመስራት ነው።አንድም የተፋሰሱን ውሃ ሀብት በብዛት መቆጣጠር፣ሁለትም ከተፋሰሱ አባል ሀገራት ጋር የይስሙላ ትብብር እያደረጉ ታሪካዊ መብትን ማስጠበቅ ሲሰልስ ደግሞ የተፋሰሱ አባል ሀገራት እንዳይጠቀሙ የተለያዩ ዘዴዎችን ገቢር ማድረግ የሚል ነው። ካይሮ አሁን እነዚህን ሦስት ስትራቴጂዎች ገቢር አድርጋለች። ውሃውን በብዛት እየተጠቀመችበት ትገኛለች። ፍትሐዊ በሚል ግን ኢፍትሐዊ አካሄድ ለማንበር ድርድር እያለች በተቃራኒው በወታደራዊ ኃይል ለማስፈራራት እየሞከረች ነው።አዲሱን የጦርነት ስልት የውክልና እና የእጅ አዙር ጦርነትም በሱዳን በኩል እየሞከረች ነው።

የውሃውን እሳት በውሃ የማጥፋት ድህረ ዓድዋ ወታደራዊ ስትራቴጂ፦ በዓለም ላይ ከ286 በላይ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ይገኛሉ። በእነዚህ ወንዞች በርካታ ሀገራት የላይኛው እና የታችኛው ተፋሰስ አባል ሆነው እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። ብዙ ጊዜ በላይኛው ተፋሰስ አባል ሀገራት ግድብ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች ሲጀመሩ የታችኞች ተፋሰስ አባል ሀገራት እሮሮ እና እየዬ ዲፕሎማሲያዊ ጩኸታቸውን ያሰማሉ። ሁል ጊዜም መፍትሔ የሚሆነው ግን የተጀመረው ግድብ በድል ሲጠናቀቅ እና ውሃው መፍሰሱን ሲቀጥል ነው። ኢትዮጵያስ ?ኢትዮጵያው ከእነዚያ እንደ አንድ ናት።

የታላቁ ህዳሴ የህዳሴ ግድብን በፍጥነት ማጠናቀቅ አዲሱን የግብፅ ቅኝ ግዛት መንፈስ ለዘለቄታው መስበር ነው። ጥቅሙም ለኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደለም። ለሌሎች አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ጭምር እንጂ። ለምን?የዓድዋ ድል ለመላው ጥቁር ሕዝቦች እና አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን አይቻል የሚመስለውን የቅኝ ግዛት ቀንበር መስበሪያ ርዕዮት ዓለም ነበር ፓን ኢትዮጵያኒዝም ወደ በኋላ ላይ ፓን አፍሪካኒዝም የተሸጋገረው።

አሁንም የህዳሴው ግድብ ከተጠናቀቀ በሁሉም የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት ግብፅን እንዴት ተቋቁመን እንችላለን ለሚለው የዘመን ግርጃ መቀልበሻ ጥቁር ማቅ ማውለቂያ ሞዴል ነው። ግድቡ ለአፍሪካዊያን ሌላም የምጣኔ ሀብት ሞዴል ይዞ የሚመጣ ነው። እስካሁን በአፍሪካ ግዙፍ ግድቦች በራስ ሀብት ያለ ማንም የውጭ እርዳታ የተገነባ የለም።’ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ይህን የክፍለ ዘመን ግርዶሽ የሚገልጥ ነው። የታላቁ የህዳሴ ግድብ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የዓድዋ ድል ብስራት የፓን ኢትዮጵያኒዝም ርዕዮት ዓለም ግማድ ነው።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን  የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You