ሴት ልጅ በትምህርት ባትገፋ፣ በሥራም ከፍተኛ በሚባለው የአመራርነት ደረጃ ላይ ባትገኝ የወንዱን ያህል ለምን የሚል ጥያቄ አይነሳም። ይልቁንም ትዳር እስክትይዝ ቤተሰቧን በቤት ውስጥ እንድታግዝ፣ ትዳር ከያዘችም በኋላ ቤተሰቧን እንድትመራ ነው የምትበረታታው። ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ ሃይማኖት፣ ባህል እነዚህ ሁሉ ተቋማት ሴት ልጅን በዚህ መንገድ ነው የሚቀርጹት። ብዙዎችም በዚህ ተጽእኖ አልፈዋል።
እንዲህ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በመሆኑ ነገሮችን ለመለወጥ ጊዜ ይወስዳል። ሴት ልጅ ጠንካራ እንድትሆን ጥረት በማድረግ የሚመሰገኑ ቤተሰቦች መኖራቸውና በግላቸውም ተጣጥረው ከወንዶች እኩል አደባባይ የዋሉ በአርአያነት የሚጠቀሱ ሴቶችም እንዳሉ አይዘነጋም ።
ወይዘሮ ዘይነብ ሃጂ አደን ከእነዚህ መካከል ይጠቀሳሉ። ወይዘሮ ዘይነብ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ነው ተወልደው ያደጉት። በአሁኑ ጊዜም በክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። አሁን የሚገኙበት የኃላፊነት ደረጃ ላይ ለመድረስ የበቁት እናትና አባታቸው ለትምህርት ልዩ ቦታ የሚሰጡና የሚያበረታቱ በመሆናቸው፤ እርሳቸውም በመማራቸውና በሥራም ከታች ጀምሮ ጠንክረው በመሥራታቸው እንደሆነ ይገልጻሉ። እንዲማሩ የሚያበረታታ ቤተሰብ ስላላቸውም ያመሰግኗቸዋል። እድለኛ እንደሆኑም ይናገራሉ።
‹‹ሴት ልጅ ተምራ ከወንዱ እኩል በኃላፊነት ቦታ ላይ እንዳትሆን ከፈጣሪ አይደለም የተሰጣት። ሴት ልጅ ወደ ማጀት የሚለው በማህበረሰብ ውስጥ የተፈጠረ ነገር ነው። ›› የሚሉት ወይዘሮ ዘይነብ፤ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ብዙዎችን እንደጎዳ ይናገራሉ። እንደርሳቸው የቤተሰብ ድጋፍ አግኝተውና በግላቸው ጥረት ማድረግ የቻሉት እጅግ ጥቂት ናቸው ይላሉ። አሁን ላይ ደግሞ ቀደም ካለው በተሻለ ለሴት ልጅ ትኩረት መሰጠቱና በትምህርትም ሆነ በተለያየ የሙያ መስክ ተሰማርተው ባለሙያ በመሆንና በኃላፊነት ደረጃም በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ወይዘሮ ዘይነብ እንደነገሩን፤ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በጅግጅጋ የተለያዩ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው። በርቀት ትምህርት ሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ በአስተዳደር ትምህርት ተምረው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመቀጠልም በአግሪካልቸር ኢኮኖሚክስ የትምህርት ዘርፍ ተመርቀዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ ሆነው በወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ውስጥ በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ ይሰሩ ነበር። በወቅቱም ቢሮው ለወጣቶች በተለያየ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ሲሰራ ነበር እርሳቸውም አብረው በበጎ ፈቃድ ሲንቀሳቀሱ ነው የነበረው።
የበጎፈቃድ አገልግሎት ወደ ሥራ ዓለም እንዲገቡም ምክንያት ሆኗቸዋል። እዛው የበጎፈቃድ አገልግሎት በሚሰጡበት ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ውስጥ ባለሙያ ሆነው ተቀጠሩ። ለጥቂት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ደግሞ በሴቶችና ሕፃናት ዘርፍ ውስጥ ተጠባባቂ ኃላፊ ሆነው ተመደቡ። የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ዳይሬክተር ሆነው እንዲሰሩ ኃላፊነት ሲሰጣቸውም ብዙ ጊዜ አልተቆጠረም።
ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ እያሉ ነበር ሀገራዊ ለውጥ የተደረገው። በክልላቸውም አዲስ የአመራርና የሥራ ለውጥ ሲደረግ እየሰሩ በሚገኙበት የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሾሙ። ለሶስት ዓመታት ካገለገሉ በኃላ ደግሞ አሁን የሚገኙበት ኃላፊነት ላይ መጡ። ሴት የካቢኔ አባል በመሆንም ብቸኛ ነበሩ።
በካቢኔው ውስጥ ብቸኛ መሆናቸው በአንድ በኩል ለሌሎች አርአያ መሆናቸው ሲያስደስታቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከእርሳቸው ጋር ሌሎች አለመኖራቸው ቁጭት ውስጥ ከቷቸው እንደነበር ይናገራሉ።
በጊዜ ሂደት ግን ለውጥ መጥቶ አሁን ላይ ሴት የካቢኔ አባላት አራት መድረሳቸውን፣ በክልሉ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ በምክትል የአመራር ደረጃም የሴቶች ቁጥር ከሁለት የበለጠ እንዳልነበርና አሁን በቁጥር ከ15 በላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። የክልሉ አስተዳደር ለሴቶች ያለው ከበሬታም ልዩ ቦታ እንደሚሰጠውና በማህረሰብ አመለካከት ላይም ለውጥ እንዲመጣ መንገድ የከፈተ መሆኑን አስረድተዋል።
ለውጡ የሚበረታታ ቢሆንም በቂ ነው ብለው አያምኑም። እዚህ ላይ የክልሉ አስተዳደር ሴቶች እንዲበረታቱ፣ ቅድሚያም ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነም አመልክተዋል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጡም ሴቶች ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ እንደሚበረታቱና ሃምሳ ሃምሳ ለማድረስም እንደሚሰራ የተናገሩትንም አስታውሰዋል።
ወይዘሮ ዘይነብ ሴቷ የችሎታ ማነስ ኖሯት ነው ብለው አያምኑም። ‹‹ ወንዱ ሴት ልጁ ትልቅ ቦታ እንድትደርስ ፍላጎትና ምኞት አለው። በጎሳም እንዲሁ ሴት ልጅ መበረታታት አለባት ይባላል። ተግባር ላይ ግን አያውሉም›› ነው ያሉት። ሕገመንግሥቱም ለሴቶች መብቱን ቢሰጥም ተግባራዊነቱ ላይ ክፍተት መኖሩን ነው የገለጹት።
ወይዘሮ ዘይነብ እንዳሉት፤ የሴት ልጅ የመሪነት ሚና የሚጀምረው ከቤቷ ነው። በሥነ ምግባር የታነጹ፣ ሀገርን የሚጠቅሙ ጥሩ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ትልቁን ድርሻ የምትወስደው ሴት ናት። ቤት የማስተዳደሩም ሚና ከወንዱ ድርሻ ከፍ ያለ ነው። በቤት ውስጥ የምትወጣው ኃላፊነት ለሥራ ዓለምም ትልቅ ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ። የራሳቸውን ተሞክሮም ለአብነት ያነሳሉ።
‹‹ትዳር መሥርቻለሁ። ልጆችም አሉኝ። በቤት ውስጥ የሚጠበቅብኝንና የእናትነት ድርሻዬን እየተወጣሁ ትዳሬን ሳላጎድል በሥራ ኃላፊነቴም ክፍተት ሳልፈጥር እየተወጣሁ ነው›› ሲሉ አስረድተዋል። ሴት ልጅ በሥራ ላይ ኃላፊነቷን በታማኝነት ለመወጣትም ትጉህ እንደሆነች፣ በሀብት አጠቃቀምም ቢሆንም ጠንቃቃና ብክነትን እንደምትከላከል ይገልጻሉ።
ወይዘሮ ዘይነብ በአንድ ወቅት ለሥልጠና ኔዘርላንድ ሄደው በነበረበት ወቅት የታዘቡትንና ተሞክሮም ይሆናል ብለው ያመኑበትንም እንዲህ አካፍለዋል። እርሳቸው እንዳሉት፤ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ሲጎበኙ ሴቶች በተለያየ የሥራ ዘርፍ ውስጥ ይገኛሉ። በአመራርነት ደረጃም ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት ሴቶች ናቸው። የፓርላማ አፈ ጉባኤዋም ሴት ናት። ሴቶች በኃላፊነት ደረጃም ሆነ በተለያየ የሥራ ዘርፍ ውስጥ እንዲገኙ የተደረገው በብቃታቸው እንደሆነም በቆይታቸው ለመገንዘብ ችለዋል።
ወይዘሮ ዘይነብ ሀገሪቱ የደረሰችበትን የእድገት ደረጃም ነበር ያደነቁት። እርሳቸው እንዳሉት ሀገሪቱ ውሃ ላይ ነው የተመሰረተችው ማለት ይቻላል። ቤቶች የተገነቡት በውሃ ላይ ነው። በግንባታ ሥራውም የሴቶች ተሳትፎ እጅግ ከፍተኛ እንደነበር ተነግሯቸዋል። በርግጥ ሴቶቹ ጠንክረው ለመውጣታቸው ምክንያት ነበር። በጦርነት ምክንያት የወንዱን ድርሻ ተክተው የሚሰሩት ሴቶች ነበሩ። ‹‹ሀገራችንን ሴቶች ናቸው የገነቡልን›› የሚል እውቅናና አክብሮትም እንደተሰጣቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ዘይነብ መንፈሳዊ ቅናትም አድሮባቸዋል።
ኔዘርላድን እንዲህ በማሳያ ለመግለጽ ቢሞክሩም፤ ብዙ በጥንካሬያቸው የሚጠቀሱ ኢትዮጵያውያን ሴቶች መኖራቸውን ይገልጻሉ። ወንዶች ይህን እንደሚያምኑም ይጠቅሳሉ። ሆኖም ግን ሴት ወደ አመራርነት እንድትመጣ ፍላጎት ያለው ወንድ አነስተኛ እንደሆነ ይናገራሉ።
ወይዘሮ ዘይነብ እንደሚሉት እርሳቸውም በግላቸው ሴቶች የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ከፍተኛ ፍላጎት ስላላቸው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በምክርም ሆነ በሚችሉት ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ ናቸው። ይህንን የሚገነዘቡ አንዳንዶችም ‹‹ ሌላ ተቋም እየመራሽ አሁንም ስለሴቶች ታወሪያለሽ ›› ይሏቸዋል። እርሳቸውም መልሳቸው አንድና አንድ ‹‹ያገባኛል›› ነው። ሥራቸው በሴቶች ዘርፍ ውስጥ ባይሆንም እንደሚመለከታቸው ያምናሉ።
ወይዘሮ ዘይነብ እንዳሉት ዛሬ ወደ ከተማ የመምጣት እድል በመኖሩ በገጠር የሚኖሩ ሴቶች የከተማውን አኗኗር በማየት እራሳቸውን በኑሮ ለመለወጥ በተለያየ ነገር ላይ ሲሳተፉና ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል። በተለይ ደግሞ የተንቀሳቃሽ ስልክ ለገጠሩ የህብረተሰብ ክፍልም ተደራሽ መሆኑ ለሴቶች ንቃተ ህሊና ከፍ ማለት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በዚህም ለውጦች እየታዩ ቢሆንም ለውጥ አለ ብለን መዘናጋት የለብንም።
ከከተማ በጣም ርቀው የሚገኙ ከመረጃ በመራቃቸውና ለውጥ ለማድረግም ዕድሉን ባለማግኘታቸው ዛሬም ለጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ከመጋለጥ አልዳኑም። እዚህ አካባቢ መድረስ አለብን። ለውጥ መጣ ማለት የሚቻለውም ለውጡ ሀገራዊ መሆን ሲችል ነው።
ወይዘሮ ዘይነብ በአመራርነት ላይ የገጠማቸው ነገር ይኖር እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ሰውንና ሥራን መምራት ከባድ ነው። ለትልቁም ለትንሹም ነገር መቆጣት ሳይሆን፤ በትእግስትና በጥበብ ነገሮችን ለመፍታት መሞከር የሚል መርህ ስላላቸው በዚህ መንገድ ነው የሚጠቀሙት።
ከእናትነት ጋርም ያያይዙታል። እናት በባህሪ ወጣ ያለውንም፣ ጥሩ ሥነምግባር ያለውንም ልጆችዋን እኩል እንደምትወድና በባህሪ ወጣ ያለውን ለመመለስ የተለያየ ጥረት እንደምታደርግም በመግለጽ፤ በሥራ ኃላፊነታቸው ላይም እንዲህ ያለው ነገር ሲገጥማቸው በሥራቸው ያሉትንም ሰራተኞች እንደልጆቻቸው አይተው ነገሮችን ለማስተካከል ጥረት እንደሚያደርጉ ነው ያስረዱት።
ነገሮች ከአቅም በላይ ሆነው ሲያገኗቸውም በችኮላ ከመወሰን ይልቅ ጊዜ ሰጥቶ ማጤንን ይመርጣሉ። በተፈጥሮአቸውም ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች ቶሎ ውሳኔ ለመስጠት የመቸኮል ባህሪ እንደሌላቸውና በሥራ ላይ መቆየታቸውም ነገሮችን ለማመዛዘን አስችሏቸዋል። ኃላፊነታቸውን ሲወጡም ቢሮ በር ዘግተው ፀሐፊ እያዘዙ የሚሰሩ ሳይሆኑ፤ በሥራቸው ያሉ ሰራተኞች ቢሮ በመሄድና እርሳቸው ጋርም በማስጠራት ስለ ሥራቸው ከእነርሱም ሃሳብ በመውሰድ አሳታፊ በሆነ ሁኔታ ሰርተው ለማሰራት ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የነገሩን።
ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር በእርሳቸው በኩል ተቀባይነት የለውም። ‹‹ተስፋ ከቆረጥኩ እስከዛሬ የሰራሁት ሁሉ ዋጋ አጣ ማለት ነው። ዜሮ ሆነ። ይሄ ሽንፈት ነው። የበለጠ ጠንክሬ ኃላፊነቴን መወጣት እንጂ መሸነፍ የለብኝም›› ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።
ወይዘሮ ዘይነብ ወደ ኃላፊነት የመጡት ሥራን ከታች ተለማምደው ነው። ከታችኛው እርከን ጀምሮ ወደላይ መውጣት ስላለው ጠቀሜታም እንደገለጹት፤ ሥራን ከታች መጀመር በተለያየ ነገር ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመያዝ እንደሚያግዝና ወደ ኃላፊነት ከተመጣ በኋላም ኃላፊነትን በቀላሉ ለመወጣት እንደሚጠቅም ነው ያስረዱት።
ሴት አመራሮችን እንደብርቅ የምናይበት ጊዜ እየተለወጠና ከቀደሙት ዓመታትም ለውጦች ቢታዩም፤ በከፍተኛ አመራርነት ላይ የሚገኙት ሴቶች ቁጥር አሁንም የሚፈለገውን ያህል ነው ለማለት አያስደፍርም።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም