የካቲት ወር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ

የየካቲት ወር ‹‹የጥቁር ሕዝቦች ወር›› እየተባለም ይጠራል። የጥቁር ሕዝቦች የመብት ማስከበር ታሪኮች የሚነገሩበት ነው። በተለይ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ደግሞ በብዙ ታሪካዊ ክስተቶች የታጨቀ ወር ነው። ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ያሉ የኢትዮጵያ ታሪኮች የተመዘገቡበት ነው።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ይህን ወር ገናና የሚያደርገው የዓድዋ ታሪክ ነው። ስለዓድዋ ጊዜው ሲደርስ የምናወራ ይሆናል። ከዚያ በፊት የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያም የየካቲት ወር ሌላው መለያ ነው። የካቲት 26 የካራማራ የድል ታሪክም አለ። ጊዜው ሲደርስ በዝርዝር እናያቸዋለን።

ወደ አገር ውስጥ ጉዳዮች ብቻ ስንመጣ ደግሞ የካቲት 11 የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ምሥረታ ታሪክ አለ። በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ንጉሣዊ ሥርዓቱን ለመጣል የተቀጣጠለው የደርግ አብዮት የተጀመረውም በዚሁ በወርሃ የካቲት ነው፡፡

ከእነዚህ የየካቲት ታሪካዊ ክስተቶች የወሩን ስም የያዘው ‹‹የየካቲት አብዮት›› የሚባለው ነው። ይህ አብዮት በወርሃ የካቲት ስለተቀጣጠለ በ1፣ በ2፣ በ3፣ ወይም በ20 ምናምን ተብሎ ሳይሆን የሚገለጸው በጥቅሉ የየካቲት አብዮት ተብሎ ነው።

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ50 ዓመታት በፊት በወርሃ የካቲት 1966 ዓ.ም የነበረውን የየካቲት አብዮት እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን እናስታውስ፡፡

ከ106 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 4 ቀን 1910 ዓ.ም የነበረው ክስተት የእቴጌ ጣይቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ነው።

‹‹ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ›› በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት እቴጌ ጣይቱ ከአባታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም እና ከእናታቸው ወይዘሮ የውብዳር ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም በጌምድር ውስጥ ደብረታቦር ከተማ ተወለዱ።

ወደ ፖለቲካዊ ታሪካቸው እንሂድና፤ የፋሲካ ዕለት ሚያዝያ 25 ቀን 1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ከአጼ ምኒልክ ጋር ቅዱስ ቁርባን ተቀብለው ተጋቡ። ንጉሡ ‹‹አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› የሚለውን ስም በተቀዳጁ በማግሥቱ ጥቅምት 27 ቀን 1882 ዓ.ም ወይዘሮ ጣይቱ ብጡል እቴጌ ተብለው ተሰየሙ።

ከእቴጌ ጣይቱ የፖለቲካ ተሳትፎዎች ጎልቶ የሚታየው፤ ኢትዮጵያ ሚያዝያ 25 ቀን 1981 ዓ.ም በውጫሌ ላይ ከኢጣሊያ ጋር በተፈራረመችው ውል ውስጥ በኢጣሊያንኛው ትርጉም ሀገሪቷን ነፃነት እንደሌላት ጥገኛ በማስመሰል ዓላማ ላይ የተመረኮዘ ውንብድና መኖሩ ሲታወቅ በተናገሩት ነው።

የጣሊያንን ሴራ ከተረዱ በኋላ «እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም። ሆኖም ይህን ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ» የሚል አቋማቸው በታሪክ ሰነድ በደማቁ ተጽፏል።

እቴጌ ጣይቱ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች መረጋጋት የሚያረጋግጥ የሀገር ግንባታ ተግባሮች በማከናወን ረገድና የአዲስ አበባ ከተማ መቆርቆር በእቴጌ ጣይቱ ከተጠናቀቁት የግንባታ ተግባሮች አንዱ ነው። ከሚታወሱባቸው አንዱ ደግሞ ፒያሳ ያለው ጣይቱ ሆቴል ነው።

በልጅ እያሱ አስተዳደር ዘመን እቴጌ ጣይቱ ከቤተ መንግሥት ተወግደው በግዞት ላይ ለአንድ ዓመት በላይ እንደተቀመጡ ይነገራል። ሆኖም ታማኝ አሽከሮቻቸውና መላው ሠራዊት የእቴጌነታቸውን ልዕልና አላጐደለባቸውም። መሳፍንቱ መኳንንቱና ወይዛዝርቱም ቢሆኑ ተገቢውን አክብሮት ሳይነፍጓቸው ዕለት በዕለት ይጠይቋቸው ነበር።

የልጅ እያሱ ሥልጣን ብዙም ሳይቆይ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም የሚኒስትሮች ካቢኔ ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥተ ነገሥታት ተብለው መንግሥቱን በመምራት እንዲተኳቸው መደረጉ ለእቴጌ ጣይቱ ታላቅ ድል ሆነ። በመሆኑም የእቴጌም የእስራት ቀንበር ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ሊወድቅላቸው ቻለ። ንግሥት ዘውዲቱ ሥልጣናቸው ተዳክሞ ትዕዛዛቸው እንዳይዛባ በማለት ከተጓዙበት ከእንጦጦ ሳይቀር ምክር መለገሳቸውን አላቋረጡም ነበር።

እቴጌ ጣይቱ የደረሰባቸውን ፈተና ሁሉ በትዕግስት ተቀብለው ጥቂት እፎይ ካሉ በኋላ ከአፄ ምኒልክ ጐን ሆነው የኢትዮጵያን አንድነትና ጥንካሬ ለማረጋገጥ ሲታገሉ ያለፉት ዘመን ከዕለታት አንድ ቀን ትዝ ስላላቸው ከሰገነት ላይ ብቅ ብለው «ያ ቤት የትኛው ነው?» ብለው ሲጠይቁ ከደንገጡሮቹ አንዷ «የእመቤቴ እልፍኝ ግምጃ ቤት ነበር» አለች። እሳቸውም ትንሽ ተከዝ ብለው ከቆዩ በኋላ ቀበል በማድረግ «ነበር ለካስ እንዲህ ቅርብ ኖሯል» አሉ ይባላል። ይህም እንደ አባባል ሆኖ ይነገርላቸዋል፡፡

ከ87 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 7 ቀን 1929 ዓ.ም ሆሎታ ገነት የጦር ትምህርት ቤት ተመሰረተ። የሆለታ ገነት ጦር አካዳሚ በ1928 ዓ.ም በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ስም በአምስት የስዊድን መኮንን አሰልጣኞች እገዛ ስራውን ጀመረ። ሆኖም ግን ፋሽስት ጣልያን ኢትዮጵያን በመውረሩ የጦር ማሰልጠኛው በአግባቡ ስራውን ማከናወን አልቻለም። በወቅቱ ሥልጠና ይከታተሉ የነበሩ ሠልጣኞች የመጀመሪያ ዘመናዊ ጦር ሰልጣኝ ስለነበሩ ብርቅ ተዋጊዎች ነበሩ። ከማሰልጠኛው ውስጥ የነበሩ ሰልጣኞችም ሆኑ ስልጠናውን ያጠናቀቁ ‹‹የጥቁር አንበሳ ጦር›› በሚል አዲስ የአርበኞች እንቅስቃሴ በተለይ በምዕራብ ኢትዮጵያ ጀመሩ።

የጥቁር አንበሳ ጦር በፋሽስት ጣልያን ወረራ ወቅት በአርበኝነት የተሳተፉ የሆለታ ገነት ጦር ምሩቃን እና በውጭ የተማሩ ጥቂት ኢትዮጵያውያን የመሰረቱት ፀረ ፋሽስት እንቅስቃሴ ነው። በጣልያን ላይ ዘመናዊ የጦር ውጊያ በማሳየት ብቻ ሳይሆን በጥንታዊ መንገድ ለሚዋጋው የኢትዮጵያ ገበሬ አርበኛ ዘመናዊ የውጊያ ስልትን በማስተማር የጥቁር አንበሳ ጦር ያደረገው አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም።

የሆሎታ ገነት ጦር አካዳሚ ተመልሶ የተመሰረተው ጣልያን ከተባረረ በኋላ ንጉሰ ነገሥቱ ተመልሰው ከመጡ በኋላ በ1935 ዓ.ም ነበር። የጥቁር አንበሳ የጦር አካዳሚ ‹‹ሆለታ ገነት ጦር አካዳሚ›› የሚል ስያሜ ያገኘውም ደርግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ነበር።

የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በአፍሪካ አንጋፋው በዓለማችንም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊት ከተመሰረቱ ጥቂት የጦር ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ ነው። ይህ የጦር ትምህርት ቤት በዘመነ ኢህአዴግ (1990 ዓ.ም) ለግማሽ ክፍለ ዘመን የቆየው ‹‹ሆለታ ገነት ጦር›› ስያሜ ወደ ሐየሎም አርአያ የጦር ማሰልጠኛ ተቀይሮ እንደነበር ይታወሳል።

በዚሁ ወደ ‹‹የየካቲት አብዮት›› ታሪክ እንሂድ።

ከዛሬ 50 ዓመት በፊት በወርሃ የካቲት 1966 ዓ.ም አዲስ አበባ በታክሲ አሽከርካሪዎች፣ በመምህራን፣ በሠራተኞች፣ በወጣቶች፣ በተማሪዎች፣ በወታደሮች በጥቅሉ በሕዝባዊ አብዮት ተናወጠች። መሬት ለአራሹ፣ የዴሞክራሲ መብት፣ የሃይማኖት እኩልነት፣ የብሔሮች እኩልነት፣ የሴቶች እኩልነት ከፍ ተደርገው ተጮኸላቸው፣ ተዘመረላቸው።

የካቲት 1966 ዓ.ም የፈነዳው እሳተ ገሞራ አድማሱን አስፍቶ ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት የተዳደረችበትን የዘውድና የአፄ ሥርዓት የገረሰሰበት አብዮት ተወለደ።

የካቲት አዝሎት የነበረው ሕዝባዊ ተስፋ መጠነ ሰፊ ነበር። በረሃብ ዘወትር የሚጠቃው ሕዝብ በቀን ሦስት ጊዜ የሚመገበው የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ፣ ጤናው እንዲሟላ፣ ትምህርት ያልደረሰው ወገን ትምህርት እንዲያገኝ፣ የነበረው የትምህርት ሥርዓትም የተሟላና ከምርትና ከዕድገት ጋር የተያያዘ እንዲሆን፣ ንጹህ ውሃ፣ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን ተስፋና ምኞትን ተሸክሞ ነበር።

እነዚህ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተስፋዎች ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ደግሞ የካቲት ፖለቲካዊ ተስፋም አንግቦ ነበር። ማን እቅዱን ያወጣል? ማን እቅዱን ይተቻል? ማን እቅዱን ያስፈጽማል? ማንስ ተፈጻሚነቱን ይከታተላል? ለሚሉትና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ሁሉ የካቲት ተስፋዊ መልስ ሰጥቶ ነበር።

ሥልጣን የሕዝብ እንዲሆን፣ አገሪቱ በሕዝብ በተመረጡ ዜጎች እንድትተዳደርና ሕዝባዊ መንግሥት እንዲመሠረት፣ ዳኝነት ፍትሃዊ በሆነና ነፃ በሆነ መልኩ እንዲስፋፋ፣ ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች፤ ማለትም በፖለቲካ ድርጅትም ሆነ በሠራተኛ ማኅበር የመደራጀት መብት እንዲከበር፣ በነፃነት የመጻፍ፣ የመወያየት … ወዘተ መብቶች ያለገደብ እንዲከበሩ የካቲት ተስፋውን ሰንቆ ነበር።

የካቲት 1966 ዓ.ም ኢትዮጵያውን ለመለወጥ የትግል ችቦ የተለኮሰበት፤ አርሶ አደሮች ከባላባታዊ የጭሰኝነት ሕይወት ለመላቀቅ ያመጹበት፣ ለተመጣጣኝ ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያ የተጠየቀበት፣ መምህራን አዲሱን የትምህርት ፖሊሲ «ሴክተር ሪቪው»ን የተቃወሙበትና በማኅበራቸው ደህንነት የሞገቱበት፣ ታክሲ ነጂዎች በነዳጅ ጭማሪ ምክንያት ሥራ ያቆሙበት፣ ሙስሊሞች የሃይማኖት እኩልነት ብለው በአደባባይ ሰልፍ የወጡበት፣ ተማሪዎችና ተራማጅ ኃይሎች ‹‹መሬት ለአራሹ›› መፈክርን ከፍ አድርገው ሥር ነቀል ለውጥ የጠየቁበት ነበር።

የየካቲቱ 1966 ዓ.ም ሕዝባዊ አብዮት ወደ ወታደራዊ አብዮት ተሸጋገረ። በሦስት ወር ጉዞውም የንጉሱን 60 ሹማምንት ያለፍርድ ገድሎ በርካታ እርምጃዎችን ወሰደ። ንጉሱን ከስልጣን በማውረድ እራሱን ደርግ ብሎ በመሰየም ብቸኛው የኢትዮጵያ መንግስት ሆነ።

አማካሪዎቹም በዚሁ ሹም ሽር ከስልጣን ተካፋይነት ወደ ሁለተኛ ደረጃ አማካሪነት ወረዱ። በዚህ ሁኔታ የመጣው ደርግ 17 ዓመት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር መጀመሪያ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› በኋላ ‹‹ሶሻሊስት ሪፑብሊክ›› እየፈጠረ ቢሄድም እየቆየ ግን እሱም በተራው ተቃዋሚዎች ተፈጠሩበት።

በዋና ተቃዋሚነት ኢሕአፓ በደርጉ ስርም እነ መኢሶን፣ ወዝ ሊግና ሌሎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጨምሮ በኢትዮጵያ የአብዮት ተውኔት መድረክ ላይ ያዋጣል ያሉትን የትግል ስልትና ዘዴ ቢከተሉም የደርግ መንግስት ወታደራዊ ባህሪው አይሎበት ሲጨፋጨፉ ቆይተዋል።

የደርግ መንግስት በተራው በስልጣን ዘመኑ የተነሱትን አበይት ጥያቄዎች ለመመለስ ከሰላም ውይይት ይልቅ ጦር ሰባቂ ጎራዴ ታጣቂ በመሆኑ ዘመኑን ሙሉ አገሪቱን ያላባራ ጦርነት ውስጥ ከተታት።

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንደሚሉት፤ ከ1966 እስከ 1968 ዓ.ም ድረስ ባሉት ሁለት ዓመታት ደርግ ከያዘው ርዕዮት ጋር ለመተዋወቅ ብቻ ሳይሆን ከማንም ያላነሰ ክህሎት አለኝ ለማለት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ሁልጊዜ አንድ እርምጃ ወደፊት ቀድሞ ከሚገኘው የግራ ክንፍ ኃይል ጋር ለመስተካከልና ብሎም የግራ ክንፉን ለማለፍ የነበረው ትግልና ጥረት ቀላል አልነበረም፤ ጥረቱም ተሳክቶ በሚያዝያ 1968 ዓ.ም ደርግ የመጨረሻውን ርዕዮተ ዓለማዊ እመርታ በማድረግ፣ የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮትን በመመሪያነት አወጀ። በዚህ ድርጊቱም እየቀደመ ሲያስቸግረው ከነበረው የግራ ክንፍ የፖለቲካ ቡድን ጋር ተስተካከለ ማለት ይቻላል። ከዚያ የሚቀጥለው እርምጃ ራሱን የሠፊውንና የጭቁኑን ሕዝብ ትግል በግንባር ቀደምነት ለመምራት በታሪክ የታጨ ብቸኛ የፖለቲካ ኃይል አድርጎ ማየቱ ነው፡፡

ይህን አስደናቂ የደርግ የርዕዮተ ዓለም ጉዞ ካሰመረለት አንዱ፤ የግራ ክንፉ ተከፋፍሎ ወደ አብዮቱ መድረክ መውጣት ነው። በተለይም ከሀገር ውጭ የሚገኘው የተማሪው ንቅናቄ አካል አብዮቱ ሲፈነዳ በሁለት አክራሪ ጎራዎች ተሰልፎ ነበር። ኋላ ገሀድ እንደ ወጣው እነዚህ ሁለት ጎራዎች የኢሕአፓና የመኢሶን ድርጅቶች ተከታዮች ነበሩ። እነዚህ ሁለት አንጋፋ የግራ ክንፍ ኅቡዕ ድርጅቶች በተማሪ ድርጅቶች ሽፋን ደጋፊዎቻቸውን ማብዛትና ማጠናከር ተያይዘው ነበር። በአብዮቱ ዋዜማ ሁለቱ ጎራዎች በዓለም አቀፉ የተማሪዎች ድርጅት አወቃቀር ላይ ሳንጃ ቀረሽ ክርክር እያደረጉ ነበር። የኢሕአፓ ወገኖች በአዲስ መልክ የተዋቀረውን ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ፌዴሬሽን ሲደግፉ፣ የመኢሶን ተከታዮች ደግሞ በቁጥጥራቸው ስር የነበረው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር እንዲቀጥል ይሟገቱ ነበር።

በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ያለው ደርግ ‹‹ሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ›› ዘመቻውን በተለያዩ ዘርፎች ማጧጧፍ ቀጥሏል፡፡

እንዲህ እንዲህ እያሉ ነጭና ቀይ ሽብር የሚባሉ የሽብር ድርጊቶች ተፈጥረው የደርግን ታሪክ የጦርነት ታሪክ አደረጉት። በመጨረሻም ደርግ በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይና አጋሮቹ በመሰረቱት ኢህአዴግ ተወግዶ መሪው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከሀገር ተሰደዱ። እነሆ የየካቲት አብዮትም የዚያ ታሪክ አካል ሆነ።

ጆሮ ገብ የታሪክ ክስተት የማያጣው የየካቲት ወር ከ6 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ አሁን ላለው ለውጥ ምክንያት የሆኑት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ለቀቁ። የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም የተነገረው ሰበር ዜና የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ቀጥሎ ምን ይፈጠራል፣ ማን ይሆናል ሲባል ቆይቶ፤ በዚሁ በየካቲት ወር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኦህዴድ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ። ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ሊሆን እንደሚችል ሰፊ ግምት ማግኘት ተቻለ። በኋላም በመጋቢት ወር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸው ይፋ ሆነ።

የየካቲት ወር እነሆ ከጥንት እስከ ዛሬ የታሪክና ፖለቲካ ክስተቶች ወር ሆኖ ይታወሳል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን  የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You