ሌላኛው የመሰረተ ልማት ስኬት- የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም

በመሀል አዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ የተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ግንባታው ተጠናቆ ከሰሞኑ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል። ሙዚየሙ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አገልግሎቶች እንዲኖሩት ተደርጎ የተገነባ ነው። ጀግኖች አርበኞች የሰሩትን ታላቅ ጀብድ፣ የሀገር አንድነትን የማስጠበቅ ወርቃማ ታሪክ የሚተርክ፤ ለዘመኑና ለመጪው ትውልድም በአግባቡ ለመዘከር የሚያስችል ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው።

የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝብ ብሎም ለሰው ዘር ሁሉ እኩልነት ፈር ቀዳጅ ነው። ድሉ በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩ የአፍሪካና ሌሎች የዓለም ሀገራትም ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ። ይሁንና ላለፉት 128 ዓመታት የሚገባውን ያህል ትኩረት አላገኘም፤ በሚገባው መልኩም መታሰቢያ አልነበረውም፡፡ የዚህ ሙዚየም ግንባታ በየቦታው ተበታትኖ የነበሩ የአድዋ ድልን የሚተርኩ ታሪካዊ ቅርሶችን ከያሉበት በማሰባሰብ በሙዚየሙ እየተደራጀና ይበልጥ እየተሟላ የሚሄድበት ሁኔታ መኖሩም በሙዚየሙ ጉብኝት ወቅት ተመላክቷል።

በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ፕሮጀክት ግንባታ ጋር ተያይዞም በፕሮጀክቱ ዙሪያና አካባቢውን ውብ እና ለቱሪዝም ሳቢ ያደረጉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችም ተገንብተዋል። የአራዳ ሕንጻ እድሳትን ጨምሮ፣ የአስፓልት መንገድ እድሳት እና የእግረኛ መሄጃዎች ተሰርተዋል።

ከሰሞኑ በመዲናዋ መካሄድ የጀመረውን 37ኛው የአፍሪካ መሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት እየጎበኙት ይገኛሉ። ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የተለያዩ የመሰብሰቢያ አዳራሾችንም ባካተተ መልኩ አምሮና ተውቦ ተገንብቷል። በሙዚየሙ የሚገኙ አዳራሾች የሚይዙት ሰው መጠን ሲታይ፤ ትልቁ አዳራሽ የሚባለውና 2ሺ 500 ሰው የሚይዘው ፓን አፍሪካን ሆል፤ አራት ሺ ሰው የሚይዝ ሁለገብ አዳራሽ፤ 300 ሰዎች የሚይዝ የምክር ቤት አዳራሽ፤ 300 መቶ ሰዎች የሚይዝ አድዋ አዳራሽ፤ 160 ሰዎች ሚይዝ መካከለኛ አዳራሽ ይገኛሉ። እንዲሁም በሙዚየሙ 250 ሰዎች መያዝ ሚችሉ ሁለት ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶች፤ ሶስት ሺ ሰዎች በአንድ ጊዜ የሚያስተናግዱበት ሬስቶራንቶች፣ ሁለት ካፍቴሪያዎች፤ የሕጻናት መዚየም በውስጡ ይገኛሉ። በተጨማሪም በአንድ ጊዜ አንድ ሺ ተሽከርካሪዎችን መያዝ የሚችል ፓርኪንግ፤ ዘመናዊ ጂምናዚየም እንዲሁም ጊቢውን የሚያደምቁ ስድስት ፏፏቴዎች ያሉት ሲሆን የሙዚየሙ ሕንፃ አናት ላይ ደግሞ በአረንጎዴ አሻራ የተዋበ ስፋራ ይገኝበታል።

አካባቢው ለቱሪስት ሳቢ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያግዙ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችም ተገንብቷል። በሙዚየሙ ዙሪያም የሚታየው የገጽታ ለውጥ ምናልባትም በቅርብ ወራት ወደ አካባቢው ያልሄደ ሰው በሚደመምበት መልኩ ለውጦችን መመልከት ያስችለዋል። ቀደም ሲል የምናውቀው ፒያሳ ዛሬ ሌላ ሆኗል፡፡ በተለምዶ መኔር ተራ ተብሎ የሚጠራው አካባ ዛሬ ላይ ሌላ አዲስ ውብ ገፅታ ተላብሷል። አራዳ ሕንፃ በዙሪያው የነበሩና ከደቡብ አቅጣጫ ከለገሐር መስመር ወደ ማዘጋጃ ሲታይ ከአራዳ ሕንፃ ጋር ተያይዞ ተገንብቶ የነበረው በአዲስ መልኩ ማስተካከያዎች ተደርጎባቸዋል፤ የእይታና ገፅታ ለውጥም ተደርጎበት ይታያል።

እንዲሁም በቸርችል ቪው ከአራዳ ሕንጻ ሻገር ብሎ ቀጥታ ወደ ማዘጋጃ ቤትና የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አቅራቢያ ባለው አደባባይ በመዲናዋ ያልነበረ አዲስ ሀውልት ተገንብቷል። ይህ አዲስ ሀውልትም የአድዋ ድል አፍሪካ ከጭቆና ነፃ እንድትሆንና ፓን አፍሪካኒዝም እንዲወለድ ጉልህ ድርሻ የነበረው በመሆኑም ይህንኑም የተመለከተ ሀውልቱ ዙሪያው ባማረ አደባባይ ላይ ሳቢ በሆነ መልኩ ተሰርቶ ይገኛል። ሀውልቱ በአድዋ ድል ወቅት የነበሩ ጀግኖች አባቶችንና እናቶችን ጀብዱ እንቅስቃሴዎች የሚያሳዩ፣ ጋሻና ጦር የያዙ፣ በወቅቱ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ፈረሰኞችንና የተለያዩ የጦርነቱ ሁነቶችን የሚያሳዩ ቅርጻቅርፆች ተካተውበታል። በሀውልቱ አናት ላይ ለመላው አፍሪካ አንድነት ተምሳሌት የሆነው የአፍሪካ ሕብረት ዓርማ ተቀርፆበት ይታያል። ታሪካዊው የአራዳ ሕንፃም ወርቃማነቱን በጠበቀ መልኩ ይበልጥ ወብ ሆኖና በተለያዩ የሚያማምሩ መብራቶች ታጅቦ ታድሷል።

በየአቅጣጫው ያሉና በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ዙሪያ ብሎም አቅራቢያው የሚገኙ ከፒያሳ መብራት ኃይል አጠገብ የነበረው አደባባይ ወደ ጊዮርጊስ ምኒሊክ ሀውልት ድረስ ያለውን አስፓልት መንገድ ጨምሮ በሙዚየሙ ዙሪያ የመንገድ ስፋት በጨመረና አላስፈላጊ አደባባዮችም ላይ ማስተካከያዎችን በማድረግ ለተሽከርካሪና እግረኛ እንቅስቃሴ በሚያመች መልኩም አድሳት ተደርጎባቸው ይታያል። ቀደም ሲል የአራት ኪሎ ታክሲ ማቆሚያ በነበረው አካባቢም የታክሲ ማቆሚያ ተርሚናል የተሰራበት ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። ቢዘህ ተርሚናል በመዞርም በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየሙ በምድር በኩል ወደ ተገነባው የተሽከርካሪዎች ማቆሚያ ፓርኪንግ መግቢያም ይገኛል።

የአድዋ ሙዚየም የኢትዮጵያውያን የድል ብስራት፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ኩራት፤ ታሪክ ከነወዙ የሚዘከርበት የዓድዋ ድል መታሰቢያ ኪነ-ሕንጻዊ ውበትን ተላብሶ፤ ስምንት የመግቢያ በሮችን ክፍት አድርጎ፤ ለከተማዋ ተጨማሪ ሞገስና ውበት አጎናፅፎ፤ በከተማችን እምብርት ላይ በኩራት ተሞሽሮ ይገኛል። በዋናው መግቢያ ሲገባ የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካ ነፃነት ድል መገለጫ የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሀውልት እና የሁሉም ከተሞቻችንን ርቀት ልኬት መነሻ የዓድዋ ዐ-0 ኪሎ ሜትርም ይገኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ስለፕሮጀክቱ እንደሚገልፁት የፕሮጀክቱ አጠቃላይ 11 ብሎኮች ፤ አምስት ወለሎች ያሉት ሲሆን ሙዚየሙ የተሰራበት አጠቃላይ ስፍራው አምስት ሄክታር ቦታ ላይ የተንጣለለ ነው። ግንባታውም አምስቱ ወለል የያዘው ስፍራ ሲዘረጋም ወደ 12 ሄክታር አካባቢ ይሆናል ሲሉ ይገልጻሉ። የወቅቱ መሪ የነበሩት አፄ ምኒሊክ በአድዋ ድል ደማቅ ታሪክ መጻፋቸውን ጠቅሰው፤ ከሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች ኢትዮጵያውያን ተምመው መጥተው፤ አድዋ ላይ ተዋድቀው፤ ሕይወታቸውን ሰጥተው ሉዓላዊነታችንን ያስከበሩበት ታሪክ፤ ያስተባበሩና የመሩ ናቸው። በመሆኑም በታሪካቸው ልክ በሚገባ የሚዘከር ቅርፅ በሙዚየሙ የተቀመጠ መሆኑንም ያስረዳሉ።

ሙዚየሙ ያረፈበት ስፍራም ለበርካታ ዓመታት ምንም አገልግሎት ሳይሰጥ፤ ታጥሮ መቆየቱንና በቆሻሻ የተሞላ አካባቢ እንደነበር ያስታውሳሉ። ሀሳብን ወደ እቅድና ወደ መሬት በተግባር መቀየር በመቻሉ፤ በተከታታይም ያንን ውጤታማ ማድረግ በመቻሉ፤ በብቃትና በፅናት መጀመር፤ መከወን፤ በተባለው ጊዜም ለአገልግሎት ለማድረስ የተቻለበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይሄንን ሀሳብ ያመነጩትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ያንን ሀሳብ ተቀብሎ ትልቅና ጉልህ ታሪክ፤ የኩራታችን ምንጭ መማሪያ ቤታችን አድርጎ የገነባው መሆኑንም ይገልፃሉ።

የከንቲባ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ፕሮጀክት በተያዘለት በጀትና ጊዜ ለመጠናቀቁ የበላይ አመራሩ ከአማካሪውና ኮንትራክተሩ ጋር በመገናኘት በተደጋጋሚ ምልከታና ክትትል የተደረገለት በመሆኑ ነው ይላሉ። በቴክኖሎጂ ድጋፍና የፋይናንስ አቅርቦት በማድረግ የግብዓት ችግሮችን የበላይ አመራሩ እየፈታው በመሄዱ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ መቻሉን ያስረዳሉ።

የአድዋ ሙዚየም ፕሮጀክት ትላንትን ከነገውና ከመጪው ትውልድ ድልድይ ሆኖ የሚያገናኝ የአድዋን ድል ታላቅነት የሚመጥን ትልቅ ፋይዳ ያለው ፕሮጀከት ነው። የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያውያንን የሚያሰባስብ፣ አልበገርነታችንንና ለትውልድ ግንባታ በሚሆን ደረጃ ለመገንባቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪዎችና በአድዋ ድል ዙሪያ የፃፉ አካላት ጋር በመሆን ታሪኩን በበለጠ የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ይጠቁማሉ። በአድዋ ድል መታሰቢያ ጎንም የፓን አፍሪካኒዝም መነሻ የሆነ ሁለት ሕንፃዎች ፕሮጀከትን ጨምሮ አካባቢው ትልቅ የቱሪዝም መስህብ ሆኖ እንዲቀጠል በውበቱና በግዝፈቱ ከሕዳሴ ግደብ በመቀጠል በከተማ አስተዳደሩ ከተገነቡት መካከል ግዙፉ ፕሮጀክት መሆኑንም ይናገራሉ።

የአድዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ፕሮጀክት አማካሪ እንዲሁም የዲዛይን ቁጥጥርና የሱፐርቪዥን ስራዎች የሕንጻ ዘርፍ ተጠሪ መሀንዲስ ኢንጂነር አስራት ሰለሞን መገናኛ ብዙሃን ባስጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት፤ አስራ አንድ ዋና ዋና ሕንፃዎች ያሉት ፕሮጀክቱ፤ የመጀመሪያውና ዋነኛው ሶስት ብሎኮችን የያዘውም አድዋን መሰረት ያደረገው የሙዚየሙ ክፍል ነው። ይህ የሙዚየሙ ክፍል 1888 ዓ.ም ላይ ለነፃነታቸው ቀናኢ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የከፈሉትን መስዋዕትነት ለአፍሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝብ አርአያ የሆኑባቸውን የሚዘከርበት ለአሁኑ ትውልድ ደግሞ ታሪክ የሚሸጋገርበት ክፍሎች ተለይተውለት የተገነባ ነው።

በክፍሎቹ የወቅቱ የጦር መሪዎች የሚዘከሩባቸው ሀውልቶች ይገኛሉ። ለሀገራቸው፣ ለነፃነታቸው፣ ለሃይማኖታቸው ሲሉ የተዋደቁ ኢትዮጵያውያንም የሚታሰቡበት ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የስነ-ስዕል ውጤቶች ተካተዋል። ከዚህም ባሻገር ጦርነቱ አድዋ ላይ ቢሆንም ከዚያ በፊት ኢትዮጵያውያን አምባላጌና መቀሌ ላይ ተዋግተዋል። በተለይም መቀሌ ላይ የሴቶች ኢትዮጵያውያን መለኝነት የሚገለፅባቸው ሁነቶች አሉ። በስፍራው የሚታየው የውሃ ኩሬ የሴቶችን ብልህነት በጦርነት ድል እንዲገኝ ያደረጉትን አስተዋፅኦ መዘከሪያ የእቴጌ ጣይቱ ሀውልት ይገኛል። እንዲሁም ከጎኑ የንጉስ ምኒሊክ ሀውልት ተሰርቷል። በአቅራቢያውም የፈረሰኞች ሚና የሚዘክርበት የጥበብ ስራዎች፤ ከአድዋ ጋር ተያይዘው የተሰሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንዲሁም ለአድዋ ጦርነት ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል በአማርኛና በጣሊያንኛ ያለውን የሚዘከርባቸው ብሎኮችም ይገኙበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶከተር ዐቢይ አሕመድ በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ምርቃቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ይህንን አስደማሚ መታሰቢያ ሌሎች የጥቁር ሕዝቦች ሀገራት ሊሰሩቶ ይችላሉ፤ ይሁንና የምኒሊክ ልጅ፣ የባልቻ ልጅ፣ የገበያው ልጅ፣ የአሉላ አባነጋ ልጅ መሆን አይችሉም። ኢትዮጵያዊነት የታደልነው ነው፤ ይህ መታሰቢያ ግን ታግለን ጥረን ሰርተን ያሳካነው ነው። ኢትዮጵያዊ በመሆን ታድለን የመሥራት ልቦናና ጥረት ታክሎበት ይህ መታሰቢያ ከ128 ዓመታት በኋላ ዛሬ በዚህ ስፍራ እውን ሆኖ ለልጆች መተላለፍ በሚችልበት ከነግርማ ሞገሱ ኢትዮጵያን መሥሎ ኢትዮጵያን አክሎ የታየበት ነው።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን  የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You