አዲስ አበባ፡- ከተለያዩ ክልሎች የተፈናቀሉና በአሁኑ ወቅት ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ያሉ ዜጎችን ወደ ግብርና ስራ የመመለስ ተግባር መጀመሩን የእርሻ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን ተከትሎ ወደ ግብርና ስራ በመግባት ምርታማ እንዲሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የግብርና መሳሪያዎችን፣ የዘር ግብዓት፣ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር የማቅረብ ስራውን ከመስራቱም በላይ ለተፈናቃዮቹ የሚያስፈልጉ የሎጂስቲክ ስራዎችን ከየክልሉና በየደረጃው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በዘላቂነት ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ የመደገፍና የማብቃት ስራም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም የ 2011/12 የክረምት ወቅት የግብርና ስራ ዝግጀት ምዕራፍ መጀመሩን የተናገሩት ሃላፊው የግብርናው የአመራረት ተሞክሮዎችን ማስቀጠልና በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የተያዙ እቅዶችን ማሳካት ግቡ መሆኑን አብራርተዋል።
ባለፉት ጊዜያት በ 188 ወረዳዎች ላይ የተጀመረውን በክላስተር የማሰራት ሙከራ በማጠናከር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደ 300 ወረዳዎች ለማስፋት ማቀዱን የሚናገሩት ሃላፊው፤ በዚህም ወደ 150 ወረዳዎች ከፍ እንዲል ማስቻል የዓመቱ ትልቁ ዕቅድ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም መሰረት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በቤንሻኒጉል፣ በጋምቤላ በ 150 ወረዳዎች ላይ የክላስተር ስራና የማሰልጠን ተግባር ለመጀመር የዝግጅት ምዕራፉ መጠናቀቁን የተናገሩት ሃላፊው በሌላ በኩልም የፍራፍሬና አትክልት ልማት ስራዎችን በሁሉም ክልሎች ላይ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ለመስራት የቅድመ ዝግጀት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
በአፋር፣ በሶማሌና በደቡብ ክልሎች በመስኖ ስንዴ የሚለማባቸውን አካባቢዎች የመለየት ስራ ከመሰራቱም በላይ በስኳር ኮርፖሬሽንና በማህበራት ተይዘው የነበሩ መሬቶች ለማልማት የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ሃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የ 2011/12 የምርት ዘመንን በአግባቡ ውጤታማ ለማድረግ ባለፉት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመታት ያልተሳኩ እቅዶችን በማሳካት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅዱ ማብቂያ ላይ 406 ሚሊዮን ኩንታል ለመድረስ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ላይም ኮምባይነርና ትራክተርን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ስለ አጠቃቀሙና አጠጋገኑ ስልጠናዎችን በልማት ጣቢያ ሰራተኞች አማካይነት እየተሰጠ ሲሆን፤ በእንስሳት ሀብት ዘርፉ ዙሪያም በተለይ የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሊሰሩ የሚገቡ ስራዎችም ትኩረት አግኝተዋል፤ በዚህም ዓለም አቀፉን የወተት ቀን ከማክበር ጀምሮ የተለያዩ የንቅናቄ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ያብራራሉ።
እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚረዱ ነገሮች አንዱ የግብዓት አቅርቦት ነው፤ እስከ አሁን የአፈርና የኬሚካል ማዳበሪያዎችን እንዲሁም ጸረ ተባይ ኬሚካሎችን የማቅረብ ስራም እየተከናወነ ሲሆን ፤ ለዓመቱ ከ 1 ነጥብ 2 መቶ ሺ በላይ የአፈር ኬሚካል ሙሉ በሙሉ ተገዝቷል፤ ወደ አርሶ አደሩም እየተጓጓዘ ይገኛል። 40 ሺ ኩንታል የዱቄት ጸረ ተባይ (አረም) ማጥፊያ ኬሚካሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ተገዝተዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011
እፀገነት አክሊሉ