«የሰቆጣ ቃልኪዳን» በቀጣይ የተጠናከረ ድጋፍ ይሻል

ኢትዮጵያ የምግብና የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ለማሻሻል ጠንካራ ሥራዎችን ስትሠራ ቆይታለች፡፡ በዚህም የማይናቅ ለውጥ ማምጣት ችላለች፡፡ ያም ሆኖ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በኢትዮጵያ አሁንም ትልቅ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የማኅበረሰብ ጤና ችግር ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት ነው እንግዲህ የሰቆጣ ቃልኪዳን እ.ኤ.አ በ2015 ይፋ የተደረገው፡፡ በዚህ ቃልኪዳን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2030 ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን የመቀንጨር ችግር ለማስቆም ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች፡፡

ይህንኑ መነሻ በማድረግ መንግሥት ከፍተኛ ተፅእኖ ያላቸውን በጤናና በሌሎች ሴክተሮች የሚተገበሩ የሥርዓተ ምግብ ተኮር ተግባራትንና የአየር ንብረት የሚቋቋሙ ሥነ- ምግብ ተኮር የመሠረተ ልማት ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ የብሔራዊ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂንም አያይዞ ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡

የሰቆጣ ቃልኪዳን በመጀመሪያ ዙር በ40 ወረዳዎች የተሳካ የሙከራ ትግበራ ምዕራፍ ከተጠናቀቀ በኋላ የማስፋት ምዕራፍ ትግበራው በ240 ለመቀንጨር ችግር ተጋላጭ በሆኑ ወረዳዎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡ አሁን ደግሞ በሁለተኛው ዙር ወደ 700 ወረዳዎች ለማስፋት ሥራ ተጀምሯል፡፡ ለዚህ ሥራም የሀብት ማሰባሰብ እቅድ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ይፋ ተደርጓል፡፡

የሰቆጣ ቃልኪዳን ፍኖተ ካርታ እንደሚያሳየው በአስር አመታት ጊዜ ውስጥ ስምንት የስትራቴጂክ ዓላማዎችን ለማሳካት ፕሮግራሞችን በማስፋፋት በድምሩ 146 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡ ይህም የማስፋፋትና የማሳደግ የበጀት ፍላጎትን ያጠቃልላል።

የሰቆጣ ቃልኪዳንን ተፅእኖ ለማሳደግ በታኅሣሥ 22 ቀን 2016 የማስፋፋት ምዕራፍ ትግበራ ከ240 ወደ 700 ወረዳዎች ለማስፋት ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን ይህም ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚጠይቅ መሆኑ ታውቋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደሚናገሩት፣ ኢትዮጵያ በምግብና በምግብ ሥርዓት ራሷ ለመቻልና ጤናማ የሕፃናት አስተዳደግ እንዲኖር በምግብና በሥርዓተ- ምግብ ላይ ከፍተኛ ሥራ ስትሠራ ቆይታለች፡፡

ለዚህ ትልቁን አስቻይ ሁኔታ የፈጠረው ደግሞ የሰቆጣ ቃልኪዳን ነው፡፡ ይህ ቃልኪዳን ይፋ የሆነው በ2007 ዓ.ም በሰቆጣ አካባቢ ከምግብ ጋር በተያያዘ ካለው ችግር በመነሳት ሲሆን ለአስራ አምስት አመታት ይቆያል፡፡

ኢትዮጵያ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር የፈረመችው የሰቆጣ ቃልኪዳን በሦስት ዙር በየአምስት አመት ወደ ሥራ የሚገባ ነው። የመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያዎቹን አምስት አመታት የሚያጠቃል ሲሆን 240 ወረዳዎች ላይ ይተገበራል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 40 ወረዳዎች በሙከራ የተሠራባቸው ነው፡፡ 200 ወረዳዎች በመጨመር በድምሩ በ240 ወረዳዎች ቃልኪዳኑ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

ከሁለት አመት በፊት በተጀመረውና በሁለተኛው አምስት አመት ደግሞ ተጨማሪ ወረዳዎችን በመጨመር ከ240 ወደ 700 ወረዳዎች እንዲሰፋ ተደርጎ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ በሦስተኛውና በመጨረሻው አምስት አመት ዙር ከ1 ሺ በላይ በሚሆኑ በሁሉም ወረዳዎች ላይ የማስፋት ሥራ እንደሚሠራ ይጠበቃል፡፡

ሥራው ከፍተኛ ፋይናንስና ርብርብ ይጠይቃል። ከተወሰኑ አመታት በፊት ምግብና ሥርዓተ ምግብ ላይ ከሚሠሩ ከሁሉም አጋር ድርጅቶች ጋር ጤና ሚኒስቴር ውይይት አካሂዷል፡፡ የውይይቱ ዋነኛ አጀንዳም አጋር ድርጅቶች አስፈላጊውን ሁሉ ግብአትና ፋይናንስ እንዲያቀርቡና በመንግሥትም ደግሞ የራሱን ኃላፊነት እንዲወጣ ነበር፡፡

በዚህም መንግሥት በየአመቱ 3 ቢሊዮን ብር በፌዴራል ደረጃ እንዲመድብ፣ ክልሎችም እንዲሁ በክልል ደረጃ 3 ቢሊዮን ብር እንዲመድቡ እንዲሁም አጋር ድርጅቶች 6 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር እንዲያመጡ በማድረግ በአጠቃላይ በየአመቱ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ለሥርዓተ- ምግብ ወጪ እንዲደረግ ታስቦ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ገንዘቡ ሥራ ላይ ሲውል ዋናው ትኩረት የሚደረግበት ጉዳይ ዜጎች በቂ የሆነ የተመጣጠነና በንጥረ ነገር የበለፀጉ ምግቦችን እንዲያገኙ ማስቻል ነው፡፡ ይህንንም በተለያዩ መንገዶች እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ለእናቶችና ለሕፃናት በተለይ አጥቢ እናቶች፣ ነፍሰ ጡር እናቶችና ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ሕፃናት በቂ የሆነ ምግብ እንዲያገኙ፣ ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣ በጓሯቸው የተለያዩ አትክልቶችን እንዲያለሙ ማስቻል፣ ትምህርት መስጠት፣ አቅም ለሌላቸውና ለምግብ አቅርቦት በቂ ገቢ የሌላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲደረግላቸው መደገፍ፣ ከሴፍቲ ኔት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግና ሌሎችም ሥራዎች በዚሁ ገንዘብ አማካኝነት ይከናወናል፡፡

እስከ 75 ከመቶ የሚገመተው ፋይናንስ ለዚሁ ሥራ በተለያየ መንገድ ይመጣል፡፡ መንግሥትም በቀጣይ የሚጨመረው እንዳለ ሆኖ ለምግብና ሥርዓተ ምግብ የሚፈለገውን የገንዘብ መጠን በማቅረብ የራሱን ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል፡፡ ነገር ግን አጋር ድርጅቶች ይህን ፋይናንስ ወደ መንግሥት እያመጡ አይደለም፡፡

በአብዛኛው በራሳቸው መንገድ ነው የሚሠሩት። ስለዚህ በራሳቸው መንገድ የሚሠሩት ሥራ እንዳለ ሆኖ የሚፈለገውን ፋይናንስ ወደ መንግሥት ካዝና የበለጠ እንዲያመጡና በቀጥታ በአንድ ሥርዓት ወደታች እንዲወርድ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፣ ባለፉት ሁለት አመታት ከሞላ ጎደል ለሥርዓተ -ምግብ የሀብት አሰባሰቡ ሂደት የተሳካ ነበር፡፡ በመንግሥት ደረጃ ለአብነት በ2016 ዓ.ም ለጤና ሚኒስቴር 697 ሚሊዮን ብር ለዚሁ ሥራ መድቧል፡፡ በክልል ደረጃም ለዚሁ ሥራ በርካታ ገንዘብ እየተመደበ ነው። በተመሳሳይ በቂ ባይሆኑም አጋር ድርጅቶችም ተሳትፏቸውን እያሳዩ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለሥርዓተ ምግብ ፋይናንስ በማምጣት በኩል ጥሩ ጅምር እንዳለ ታይቷል፡፡ በመንግሥት በኩልም በዚህ ጉዳይ አስራ አራት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በጋራ እየሠሩ ይገኛሉ።

ከግብአት ጋር በተለይም ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ ሁሉም አጋር ድርጅቶች ቃል በገቡት መሠረት ገንዘብ እንዲያቀርቡ፣ መንግሥት በፌዴራልም፤ በክልልም ደረጃ የበለጠ ገንዘብ እንዲያመጣ ፤ በተለይ ደግሞ ከግጭት፣ ድርቅና ሌሎችም የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር በተያያዘ አሁን ካሉትና መሬት ላይ ከሚታዩ ችግሮች አኳያ ተጨማሪ አቅም ስለሚያስፈልግ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ውይይት ከአጋር ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው የመንግሥትና የክልል አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡

በመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት የሰቆጣ ቃልኪዳን ትግበራ ምዕራፍ አበረታች ውጤት መጥቷል፡፡ በተለይ በትግራይና በአማራ ክልል በሚገኙ 40 ወረዳዎች ላይ በተደረገ የሙከራ ትግበራ ጥሩ ውጤቶች መጥተዋል፡፡ ትግበራው በተጨማሪ 200 ወረዳዎች ላይ ሰፍቶ ተጨማሪ ጥቅምች እየተገኙ እንደሆነ ለማየት ተችሏል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ በክልልና በፌዴራል ደረጃ ያሉ 14 ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የሥርዓተ- ምግብ ጉዳይን የራሳቸው አድርገው በጋራ መሥራታቸው ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ በየደረጃው በጥናት የተረጋገጠ ውጤት መምጣቱ ሲሆን በተለይ እ.ኤ.አ በ2022 በዚህ ዘርፍ በሚሠራ ተቋም በተጠና ጥናት መሠረት በ240 ወረዳዎች ላይ ከ99 ሺ በላይ የሚሆኑ ሕፃናትን ከመቀንጨር ነፃ ማድረግ ተችሏል፡፡ ከ3 ሺ በላይ የሚሆኑ ሕፃናትንም ከሞት መታደግ ተችሏል፡፡ ስለዚህ ውጤቱ ተጨባጭ እየሆነ መምጣቱን ያሳያል። በርካታ አጋር ድርጅቶችም ገንዘብ በማሰባሰብ በሥርዓተ ምግብ ላይ ሰፊ ሥራ መሠራታቸው በግልፅ ታይቷል፡፡

ከዚህ ውጪ በነባራዊ ሁኔታ የመቀንጨርና አጣዳፊ የምግብ እጥረት በኢትዮጵያ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይህንን ለመቅረፍ የሰቆጣ ቃልኪዳን አብዛኛዎቹን አጋር ድርጅቶች ያሰባሰበና በይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ ያደረገ ስለሆነ ይህን ውጤት ለሁሉም ወረዳዎች ማስፋት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለዚህ ከ240 ወደ 700 ወረዳ እንዲሰፋ ተደርጓል፡፡ ከክልል ክልል፤ ከወረዳ ወረዳ ልዩነቶች ቢኖሩም በሁሉም አካባቢዎች ላይ ጥሩ ንቅናቄዎች አሉ።

በተጀመረበት ቦታ ላይ ሁሉም አመራር በሥርዓተ -ምግብ ዙሪያ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ አጋር ድርጅቶችም ተጨማሪ ገንዘብ እያቀረቡ ነው። ይህን በሁሉም ወረዳዎች ማድረስ ከተቻለ ደግሞ እ.ኤ.አ በ2030 መቀንጨርን ዜሮ ማድረግ ይቻላል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፣ የሰቆጣ ቃልኪዳን ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የተጀመረ ቢሆንም አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሠራበት ይገኛል። ከተወሰኑ ወራት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰቆጣ ቃልኪዳን ላይ ውይይት አድርጓል። ከኢትዮጵያም አልፎ ለአፍሪካውያን፤ ለዓለምም መቀንጨር ዜሮ የሚደረግበት ትልቅ ኢንሺዬቲቭ ሆኗል፡፡ ሴክተሮችን የሚያሰባስብ፣ ማኅበረሰቡን ዋነኛ አካል የሚያደርግ፣ የተለያዩ አጋር ድርጅቶችንና የግል ተቋማትን ብሎም ሲቪክ ማኅበራትን የሚያሰባስብ ትልቅ ኢንሺዬቲቭ እንደሆነ ተወስዷል፡፡ ለዚህም ነው በተጨማሪ ወረዳዎች ማስፋፋት የተፈለገው፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው እንደሚሉት፣ የሰቆጣ ቃልኪዳን ትግበራን በሚመለከት በርካታ ውጤቶች አሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተሞክሮው ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ የተጀመረበት ቦታም በመቀንጨርና በሌሎችም የሥርዓተ ምግብ መዛነፍ የሚታይበት ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ከሰቆጣ ቃልኪዳን ትግበራ በኋላ መቀንጨር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ታይቷል። ለአብነትም ከዛሬ ሃያ አመት በፊት በኢትዮጵያ የመቀንጨር ምጣኔ ከነበረበት 58 ከመቶ ከተወሰኑ አመታት በፊት ወደ 39 ከመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ይህ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

ይሁንና ባለፉት አምስት አመታት በኢትዮጵያ በነበሩ የፀጥታ ችግሮች፣ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የመቀንጨር ምጣኔው ተመልሶ የመጨመር አዝማሚያ አሳይቷል፡፡ በቅርቡ በተሠራ ጥናትም ቀደም ሲል የነበረው 37 ከመቶ የመቀንጨር ምጣኔ ወደ 39 ከመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ሆኖም ይህ ከክልል ክልል በእጅጉ ልዩነት አለው፡፡ ስለዚህ በቀጣዮቹ አመታት ተጨማሪ ጥናቶች በተለያዩ አጋር አካላት ተደግፈው ስለሚሠሩ ከክልል ክልል ያለው ለውጥ በግልፅ የሚታይ ይሆናል፡፡

በድርቅ፣ በግጭትና በተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የመጡ ችግሮችን ለመቅረፍ ከአጋር አካላት ጋርና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል አመራሮች ጋር የሚደረገው ውይይት ወሳኝ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሥራው ተጨማሪ አቅምና ግብአት የሚጠይቅ እንደመሆኑ ማኅበረሰቡን ማሰልጠን፣ የአመጋገብ ሥርዓት ላይ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ፣ እንደመንግሥት በግብርና ላይ የተጀመሩ በርካታ ሥራዎች በሁሉም ቦታዎች ላይ ማድረስ ይጠበቃል፡፡

በሰቆጣ ቃልኪዳን በአንድ አጀንዳ ላይ ሴክተሮች በጋራ ተረባርበው መሥራት እንደሚችሉ ትልቅ ትምህርት መውሰድ ተችሏል፡፡ የመቀንጨርና የሞት ምጣኔ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ እንደትልቅ ተሞክሮ የሚወሰድ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም ባለበት አካባቢ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በተለይ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው የሚመገቧቸው ኃይል ሰጪ ምግቦች የነበሩ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በዚህ የሰቆጣ ቃልኪዳን መሠረት የፕሮቲን ይዘት ያላቸውንና የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን መመገብ መቻል እየታየ ነው፡፡

እናቶችም በተሰጣቸው ግንዛቤ መሠረት ለሕፃናቶች የሚያዘጋጇቸውን ምግቦች የበለጠ የተለያዩና በንጥረ ነገር የበለፀጉ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ በዚህም በሕፃናት ጤና ላይ በርካታ ለውጦችን ማየት ተችሏል፡፡ በዚህም የሰቆጣ ቃልኪዳን ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ማግኘት ችሏል፡፡ ሆኖም ከዚህ የተገኙ ትምህርቶችን ወደ ሥራ ለመቀየር ተጨማሪ አቅም ይጠይቃል፡፡ በተለይ ደግሞ ከአጋር ድርጅቶች የተለያዩ ድጋፎች ያስፈልጋል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You