መቐለ፡- በኢትዮጵያ በየዓመቱ የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም እያስገኘ አለመሆኑን በመቐለ እየተካሄደ ባለው ሦስተኛው ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባዔ ተጠቆመ፡፡
ሦስተኛው ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባዔ ‹‹ባህላዊ እሴቶቻችን ለአገራዊ አንድነታችን እና ለዘላቂ ቱሪዝም ልማት›› በሚልመሪ ሃሳብ በመቐለ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በመድረኩ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የ13 ወራት ጸጋ ያላትና የብዝኃ ባህል ባለቤትና ውብ የተፈጥሮ መስህብ ያሏት አገር ብትሆንም በቱሪዝም መስክ የሚገባትን ያህል አልተጠቀመችም፡፡ በቱሪዝሙ በየዓመቱ የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም የሚጠበቀውን ያህል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አላስገኘም፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በዘመናት ጠንካራና የቱሪዝም እድገት ተመዝግቧል፡፡ ከውጭ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ቱሪስቶች ጨምረዋል፡፡ ነገር ግን የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ፈጣን በሆነ መልኩ እያደገ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሊያበረክት የሚገባውን አስተዋፅኦ አላበረከተም፡፡ በመሆኑም የቱሪስት መዳረሻዎችን በመለየት የማልማትና ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ የማስተዋወቅና ተዛማጅ ሥራዎች ማከናወን ይገባል፡፡
እንደ አገር የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማዘመንና የሆቴሎችን ቁጥር ለማብዛት በዓለም ላይ ተወዳዳሪ በመሆን ገበያ ለመፍጠር ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ገበያ የማጥናት፣ አዳዲስ ሆቴሎችን መገንባትና የተገነቡትን ማስፋፋትና ደረጃቸውን የማስጠበቅ ተግባር እንደሚያስፈልግ፤ ለዚህም ተግባራዊ ሥራው በአግባቡ ከተከናወነ የማህበረሰቡን ህይወት ትርጉም ባለው መንገድ መቀየር እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ምክትል የቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዘነቡ ሐለፎም በበኩላቸው፤ ሴክተሩን የኢኮኖሚ ሴክተር ነው ብሎ አለማየትና ከግብርናው ጎን ለጎን ማስኬድ አለመቻል፤ ከዘርፉ መገኘት የነበረበት ጥቅም እንዳይገኝ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ ዘርፉን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውስንነት እንዳለበምት ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ ዘነቡ እንዳሉት ቱሪዝሙ በተነጻጻሪ ከአንዱ አካባቢ ሌላኛው አካባቢ የተሻለ መስሎ ቢሆንም እንደ አገር ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ አሁን ላይ ሴክተሩ በኤጀንሲ ደረጃ ተቋቁሞ ራሱን ችሎ መንቀሳቀሱ እና እስከ ወረዳ ድረስ ቅርንጫፍ እያሰፋ መሄዱ መጻኢውን የዘርፉ በጎ ተስፋ ያሳያል፡፡ ዘርፉን ለማሳደግና የአገሪቷን ኢኮኖሚ በሚደግፍ ቁመና ላይ ለማሳረፍም ከግምታዊ ሥራ ይልቅ በጥናትና ምርምር መደገፍ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011
አዲሱ ገረመው