አዲስ አበባ፡- የኢንደስትሪ ግብዓት አቅርቦት ድርጅት የግብዓት አቅርቦት ችግር የመፍታት ተልዕኮ ቢሰጠውም እያሳካ አለመሆኑን ዋናኦዲተር ጠቁሟል፡፡
ዋና ኦዲተር የኢንደስትሪ ግብዓት አቅርቦት ሥርዓት አፈፃፀም ውጤታማነትን በተመለከተ ባከናወነው የክዋኔ ኦዲት ድርጅቱ በተቋቋመበት ደንብ ቁጥር 328/2006 መሰረት የኢንዱስትሪውን የግብዓት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ ጥናቶችን በማጥናት እና ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ቅደም ተከተሎችን በማስቀመጥ የኢንዱስትሪ ግብአት አቅርቦቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ ድርጅቶችን መገንባት ፣ ማስተዳደር እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ማስተላለፍ ሲገባው ኦዲቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሰራው ስራ አለመኖሩን ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ አስታውቀዋል፡፡
ድርጅቱ ለኢንደስትሪዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በዓይነት፣ በጥራት እና በብዛት በመለየት በእስትራቴጂክ እና ዓመታዊ ዕቅዱን በማካተት የግብዓት ችግሮችን መፍታት ቢኖርበትም ከዓመታዊ ዕቅድ ውጪ የረጅም እና መካከለኛ ጊዜ አቅጣጫ የሚያሳይ የፀደቀ ስትራቴጂክ ዕቅድ የሌለው መሆኑንም አቶገ መቹተ ናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በ2008 በጀት ዓመት ለብረታብረት ኢንዱስትሪ ዘርፍ በብር 270 ሚሊዮን ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገር የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ገዝቶ ለማቅረብ ያቀደ ቢሆንም ግዢውን አለመፈፀሙ፤ በተመሳሳይ ለጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ማለትም የተዳመጠ ጥጥ፣ብትን ጨርቅ፣ ትሪም ቀለም እና የተለያዩ ኬሚካሎችን በብር 1ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገዝቶ ለማቅረብ አቅዶ የተዳመጠ ጥጥ ግዢ ብቻ የፈፀመ መሆኑን ዋና ኦዲተሩ አመልክተዋል፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011
ምህረት ሞገስ