ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብትና በምቹ አየር ንብረት የታደሉ ከሚባሉ የአፍሪካ ሃገራት አንዷ ናት። በአንፃሩ ደግሞ ይህንን ሃብቷን ዜጎቿ አውቀው ለራሳቸውም ሆነ ለሃገር ኢኮኖሚ እድገት እንዲያውሉ በማድረግ ረገድ እጅግ ወደኋላ ከቀሩትም መካከል ትጠቀሳለች፡፡ በተለይም ያሏትን የተፈጥሮ ፀጋዎች የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ማልማት ባለመቻሏ ብልፅግናዋ ርቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቢሆን የግብርናም ሆነ የኢንዱስትሪው ክፍለ-ኢኮኖሚ ኋላቀርና ባህላዊ የሆነ ስርዓት ነው የሚከተሉት። ያላትንና በውል የሚታወቁትን አንዳንድ የተፈጥሮ ሃብቶች ወደ ውጭ ብትልክም፤ እሴት የማይጨመርባቸው በመሆኑ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን አልቻለችም፤ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትንም ጥቅም በሚገባው ልክ እያገኘች አይደለም፡፡
ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በጥናት መርምሮ ማወቅና ማሳወቅ፤ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጥቅም ላይ እንዲውሉ፤ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ሁነኛ መጋቢ እንዲሆኑ የማድረጉ ሚናም ለተለያዩ ተቋማት የተሰጠ ኃላፊነት ነው፡፡ በዚህ ረገድም የሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዋነኞቹ ሲሆኑ፤ ተቋማቱ ከሚሰጣቸው ሦስት ዋና ዋና ተልዕኮች መካከል ያሉበትን አካባቢ የተፈጥሮ ሃብትና ማኅብረሰብ ማዕከል ያደረጉ፤ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ማካሄድ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይም ሀገሪቱ ለምታካሂደው የኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ አጋዥ የሆኑ የምርምርና ጥናት ሥራ በማከናወን ለኢኮኖሚ እድገት አለኝታ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ፤ ማላመድና ለኅብረተሰቡ (ለሃገር) ጥቅም እንዲውሉ ማድረግም ላይም ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡
የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመያዝ በተለይም በማዕድን ምርምርና ልማት ዘርፍ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ካሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከልም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋነኛው ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ማዕድናት ላይ ዘርፈ ብዙ ምርምሮችን እያካሄደ ይገኛል፡፡ በቅርቡም ለሀገሪቱ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የጀርባ አጥንት የሆነው የብረት ማዕድን በክልሉ በስፋት መኖሩን አጥንቶ ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህና በሌሎችም የማዕድን ምርምር ሥራዎቹ ዙሪያ `ዝግጅት ክፍላችን በዩኒቨርሲቲው የጥናት ቡድን መሪ ከሆኑትና በጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል ከመምህር አገኘሁ ቦርኮ ጋር የነበረው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
እሳቸው እንደሚናገሩት፤ ላለፉት አምስት ዓመታት ደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ጋሞ ዞን፤ ኮንሶና ጎፋ ስድስት የሚደርሱ የማዕድን ፍለጋ ምርምር ላይ ቆይተዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ዩኑቨርሲቲው ተለይተው ከተሰጡት ሥራዎች ውስጥ ለሀገር በሚጠቁሙ ዘርፎች ላይ ምርምር በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችሉ ምርምሮች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡
ከእነዚህም መካከል የማዕድን አለኝታ ጥናት ማድረግ አንዱ ሥራ ሲሆን በዚህም መሰረት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነትና ጌጣጌጥ ሥራ የሚውሉ በርካታ ማዕድናት በአካባቢ መኖራቸውን ለይቷል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን አንዳንድ የግል ድርጅቶች በሚፈልጉት መልክ ጥናትና የማማከር ሥራ በመስራት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ወደፊት ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሥልጣን ሲያገኝ ደግሞ የራሱን የገቢ ምንጭ መፍጠሪያ ለማድረግ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ ከዚህ ቀደም የተሰሩ ምርምሮችንና ልምዶችን በመቀመር ለሀገር የውጭ ምንዛሬ በማስገባትና ብልፅግናውን እውን ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ያለውን የተማረ ኃይል በመጠቀም ተጨማሪ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እስካሁን ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በተደረገው የማዕድን ልየታ ሥራ በርካታ ማዕድናቶች በምርምሩ የተገኘ ሲሆን ለአብነትም በ2012 ዓ.ም ቡርጂ ዞን ላይ እንደካኦሊን፤ ቤንቶናይት፤ ግራናይት የተሰኙ ማዕድናት በስፋት እንደሚገኙ ለማወቅ መቻሉን ነው ያመለከቱት፡፡
በተጨማሪም ኮንሶ ዞን ላይ ሁለት ጊዜ በተለያዩ አቅጣጫዎች ዩኒቨርሲቲው ጥናትና ምርምር ማድረጉ አስታውሰው፤ በዋናነት ላይምስቶንና በጣም ውድ የሆነው ቤርሊን የተሰኘ ማዕድን በመለየት አሁን ላይ የተለያዩ ኩባንያዎች በስፋት የሚያመርቱና ለማምረት ጥያቄ ያቀረቡ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡ እንዲሁም በጥራት ደረጃው ከፍ ያለ አማዞናይት የተሰኘው ማዕድን በዞኑ መኖሩን መታወቁን፤ ይህም ማዕድን ለጌጣጌጥና ለሴራሚክ ኢንደስትሪ ዋነኛ ግብዓት የሚሆን ሲሆን በተመሳሳይ በርካታ ኩባንያዎች ወደ ሥራ ለመግባት ፍቃድ መጠየቃቸውን ያስረዳሉ፡፡
እንደእሳቸው ገለፃ፤ ዩኒቨርሲቲው ከሁለት ዓመታት ወዲህ ወይጦ ድንበር ላይ ኤመራልድ የተሰኘውን አይነት በዓለም የማዕድን ገበያ ተወዳጅና ውድ የሆኑ ማዕድናትን ከመለየት አልፎ የተለያዩ የአካባቢው ነዋሪዎች ተደራጅተው በማምረት በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ መላክ ድረስ የደረሱ አሉ፡፡ ከእነዚህም ባሻገር በዚሁ አካባቢ ላይ እንደኳርቲዝና ግራናይት የመሳሰሉ ለሴራሚክና ለብርጭቆ ኢንዱስትሪ የሚውሉ ማዕድናት ይገኛሉ። በእነኚህ ሳይቶች በርካታ ድርጅቶችና ማህበራት ፍቃድ አውጥተው ለማምረት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ከእነዚህም ባሻገር ለጌጣጌጥ የሚውሉ እንደኮራንደም፤ አማዞናይት፤ ጋርኔት፤ አኳማሬዝ ያሉ ማዕድናትም ቡርጂ ዞን በከፍተኛ መጠን እንዳሉ መታወቁን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹የእነዚህ ማዕድናትን ልየታ ሥራ ተሰርቶ በርካታ የግል ኩባንያዎች ገብተው እያመረቱ ነው የሚገኙት፤ ለሴራሚክ ኢንደስትሪ የሚውለው ካዩሊን የተሰኘው ማዕድን አንድ ኩባንያ በዞኑ ለማምረት ዝግጅት እያረገ ነው›› ይላሉ፡፡
ተቋሙ በተመሳሳይም በጋሞ ዞንም በጌጣጌጥና የኢንዱስትሪ ግብዓት ማዕድናት ላይ ጥናት ምርምር የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ በምዕራብና ምስራቅ ደቡባዊ የዞኑ ክፍል ገሬሴ ወረዳ ላይ በስድስት ቀበሌዎች ላይ ጥናት ማድረጉን አመላክተዋል፡፡ በእነዚህ ቀበሌዎች ላይ በሁለት ዙር ጥናት በማድረግ የልየታ ሥራ መሰራቱን የሚናገሩት አቶ አገኘሁ፤ ይህ አካባቢ ትልቅ ሃብት ያለበት ነው፤ ‹‹በተለይ እንደ ቤሬል፤ አኳማሬዝ፤ ኤሜራልድ፤ አኳማሬዝና የመሳሰሉ የጌጣጌጥ ማዕድናት አለ›› ይላሉ፡፡
በአካባቢው በተደረገው ጥናት መጠነ ሰፊና ጥሩ የሚባል ክምችት መኖሩን እንደተረጋገጠ ያስረዳሉ፡፡ በደንብ ቢጠና እና ተጨማሪ ምርምር ቢደረግ ደግሞ እንደ ዚንክና ኮፐር ያሉ ማዕድናትን በማምረት የሀገሪቱን ኢንዱስትሪ አቅም ወደላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም አኳማሪንና (ፖታሺየም፤ ካልሺየም፤ ሶዲየም ኮንሰንትሬሽን የያዘ)፤ በተለይ ለእፅዋት እድገትና እንክብካቤ የላቀ አስተዋፅኦ ያለው ማዕድን ሰፊ ክምችት መኖሩን ያስረዳሉ፡፡ በዚሁ አካባቢ ሁለት ኩባንያዎች ገብተው ኳርቲዝ እያመረቱ ሲሆን የማዕድናቱን መገኘት ተከትሎም የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ይህም የአካባቢው የልማት እንቅስቃሴ እየጎለበተ መምጣቱን፤ ወጣቶች በማኅበር ተደራጅተው እያለሙ ለሌችም የሥራ እድል እየፈጠሩ እንደሆነ ሲያስረዱ፤ ‹‹የአርሶአደር ልጆች ሳይቀሩ ተደራጅተው አርቴፊሻል በሆነ መንገድ ቁፋሮ በማድረግ ለኩባንያዎች ያቀርባሉ ይላሉ፡፡ ይህም ቢሆን ካለው ሰፊ ሀብት አኳያ ብዙ ሊሰራ የሚገባበት ዘርፍ እንደሆነ ነው የጠቀሱት፡፡
እንደ አቶ አገኘሁ ማብራያ፤ ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በባህላዊ መንገድ የብረት ማዕድን እያወጡ በማቅለጥ እንደማረሻ ፤ ቢላዋ የመሳሰሉ መሳሪያዎችን ያመርታሉ፡፡ ይህ ጉዳይ በአካባቢው ማኅበረሰብ ቢታወቅም በተጨባጭ የብረት ማዕድን ስለመኖሩና ምን ያህል ክምችት እንዳለ አይታወቅም ነበር፡፡ ይህም የብዙዎች የረዥም ጊዜ ጥያቄ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲው ይህንን የሕብረተሰቡን መረጃ በመያዝ በመጀመሪያ ምሁራንን ያሳተፈ ኮሚቴ አቋቁሞ ባህላዊ ምርት የሚከናወንበት ቦታ ለመቃኘት ሙከራ አድርጓል፡፡
‹‹በመቀጠልም ከማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመተባበር ፕሮፖዛል አስገብቶ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ወደ ጥናት ውስጥ ገብቷል፡፡ አካባቢው አዲስ ስለነበር ለስድስት ጊዜ ያህል ጥልቅ ጥናት አድርጓል፡፡ በጥናቱ መሰረት በጣም ሰፊ ቦታ ላይ የብረት ማዕድን መኖሩ ተረጋግጧል›› ይላሉ፡፡ ከዚህ ውስጥም 146 ስኩዌር ኪሎ ሜትሩን ካርታ ሰርተን 42 ናሙናዎችን በመሰብሰብ ጆዮፉዚክሱን መስራታቸውን፤ አዲስ አበባ በመላክም የብረት ይዘቱን ለማጣራት መሞከሩን ያስረዳሉ፡፡ የተከለለውን ሥፍራ በአምስት ብሎክ ክምቹንና የኢኮኖሚ እሴቱን በማጥናት ለ950 ዓመት የሚሆን የብረት ክምችት መኖሩን በግምት ለማወቅ መቻሉን ያመለክታሉ፡፡
ይሁንና ሰፊና ጥልቅ ያለው ጥናት ከተደረገ ከዚያም በላይ ብዙ ዓመት ሊቆይ የሚችልበት እድል መኖሩን ገልጸው፤ የማዕድኑ በአካባቢው በስፋት መገኘት በተለይም በሀገሪቱ አሁን ካለው የብረት ፍላጎትና በዓለም ገበያ ከሚስተዋለው የብረት ዋጋ ንረት አኳያ ትልቅ አንድምታ ያለው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ አሁን ላይ እየተስፋፋ ካለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪን አኳያ በሀገሪቱ ያለው የብረት ፍላጎት ከፍተኛ ነው፤ ከዚህ ባሻገርም በዓለም ላይ የብረት ዋጋ ንረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው›› ይላሉ፡፡
ይህም የሀገሪቱን የብረት ፍላጎት ከማርካት በተጨማሪ ለብረት ግዢ እየወጣ ያለውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በመታደግ ረገድ የላቀ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ነው ያብራሩት፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲ በአቅሙ እያደረገ ካለው ጥናትና ምርምር ባሻገር በአካቢው ጥልቅ የሆነ ጥናት በማካሄድ ሀገሪቱን ከዘርፉ የላቀ ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ባይ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠርና ኢንቨስትመንትን በመሳብ ሀገሪቱ ለተያያዘች የብልፅግና የልማት መስመር ለማሳካት ማዕድን ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አገኘሁ ማብራሪያ፤ ከብረት ማዕድን በተጨማሪ የከሰል ድንጋይ በዚሁ ጎፋ ዞን በስፋት የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህ ላይም ዩኒቨርሲቲው ሰፊ ጥናት አድርጓል፡፡ በዚህ ጥናት መሰረትም ወደ 429 ሚሊዮን ቶን ያክል የከሰል ድንጋይ ክምችት በአካባቢው መኖሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ በጋሞ ዞን በቀን 150 መኪና የሚጫን የከሰል ሃብት ይገኛል፡፡ በተጨማሪም አካባቢው መሰረተ ልማት ዝርጋትና ካለው ምቹ የአየር ሁኔታ፤ ለከተማ ቅርብ ከመሆኑ አንፃር በዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ አካላት ጥሩ እድል አለ፡፡
‹‹አሁንም ቢሆን በአካባቢው ያለውን ሰፊ የማዕድን ሃብት የተገነዘቡ የተለያዩ ድርጅቶች መዋለንዋያቸውን በማፍሰስ የልማት ሥራ እያከናወኑ ነው፤ ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል›› ይላሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር ምርምር ከማድረግ በዘለለ የተገኙ የማዕድን ሃብቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችንም በማቅረብና ምክረ ሃሳብ በመስጠት ረገድ የበኩሉን ሚና እየተዋጫወተ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
ይሁንና የፌዴራል መንግሥት ትልቁን ኃላፊነት በመውሰድ በተጨባጭ ማዕድናቱ ለሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ዋነኛ ግብዓት እንዲሆኑ የማድረግና ብልፅግናን እውን የማድረግ ሥራ ይሰራል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ አገኘሁ ያመለክታሉ። የማዕድኑ ጥቅም ላይ መዋል ኢንዱስትሪውን ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ማህበረሰብንም ሕይወት እንዲለወጥ ማድረጉ ላይም ሰፊ ሥራ መስራት የሚጠበቅበት እንደሆነ አስገንዝበው፤ በየደረጃው ያለው የመንግሥት አመራር ቁርጠኛ በመሆኑ ለአካባቢው ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን የካቲት 8 /2016