ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከጠላት ወረራ በኋላ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም በድል አድራጊነት አዲስ አበባ ሲገቡ «ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ታሪክ ዘመን መክፈቻ ነው» ብለው ዕለቱን በይነውታል። ይህንን ንግግራቸውን ተከትሎ የዛሬዋ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሥያሜም «አዲስ ዘመን» መባሉን የታሪክ መዛግብት ከትበውታል። በዚህም መሰረት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም በይፋ ሥራ ጀመረ።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮም አዲስ ዘመን የተለያዩ የመንግሰት ሥርዓቶችን እያለፈ ታሪክን እየዘገበ፣ እየከተበና እየሰነደ የሀገር ሀብትና የመረጃ ቋት በመሆን እነሆ ዛሬ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም 78ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በመሆኑም አዲስ ዘመንን ከጥንት ጀምሮ የሚያውቁትና በስራ ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ‹‹ጋዜጣው በትውልዶች ቅብብሎሽ የህትመት ሚዲያው አባት በመሆን እዚህ ደርሷል›› ሲሉ ይናገሩለታል።
‹‹አዲስ ዘመን ማለት ሀብትና ቅርስ ነው፤ በመሆኑም አሉን እንደምንላቸው ቅርሶቻችን ልዩ ትኩረትና ጥበቃ ያስፈልገዋል›› ሲል አስተያየቱን የሰጠው የአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ ወንድወሰን መኮንን ነው። ጋዜጣው ሲቋቋም በአገሪቱ ላይ ሊነበቡ የሚችሉ የህትመት ውጤቶች አነስተኛ ከመሆናቸው ባለፈ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እጥረት በመኖሩ ስራው በቤተክህነት አገልጋዮች ይሰራ ነበር ሲል ያስታውሳል። ከዚያ በኋላ ግን በዘርፉ የሚያስደንቅ አቅም ያላቸው ጻህፍት እየተሳተፉ እዚህ እንዳደረሱት ይናገራል።
ጋዜጣው ለአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስራዎችን በመሰነድ ትልቅ አብነት ሆኖ ብዙ ታሪካዊ ክስተቶችን ከትቦ የያዘ ነው የሚለው ጋዜጠኛ ወንድወሰን ህትመቱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ አገራዊ ኩነቶችን ከነፎቶግራፋቸው ተሰንደው የሚገኙበት በመሆኑ ቅርስ ሆኖ ዛሬም ድረስ እያገለገለ ይገኛል ብሏል፡፡
አዲስ ዘመን ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በሚዛናዊ ዘገባዎቹ፣ ጽንፈኝነትና አክራሪነት በማይታይባቸው የአምድ ዘገባዎቹ አገርን ወደ አንድ አምጥቷል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት ያሉ የህትመትም ሆኖ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ልምዱን መውሰድና ለአገር ሰላምና አንድነት ሊጠቀሙበት ይገባል ሲል አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በጋዜጣው ላይ እየታየ ያለው ለውጥ የሚበረታታ ፤ በተለይ በዕለተ ቅዳሜ ዕትም የተጀመረው አሁን ደግሞ በረቡእ ጋዜጣ ላይ የሚቀጥለው የለውጥ ስራ በሁሉም ቀናት ሊስፋፋ ይገባል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ጋዜጠኛ ተሾመ ቀዲዳ እንደገለፀው አዲስ ዘመን ማለት አንጋፋና የአገሪቱ የህትመት ሚዲያ አባት ነው። ቀደም ሲልም በጋዜጣው ላይ የሚሳተፉ ፀሀፍት ብዙ እውቀት ያላቸው፤ በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚያስተምሩ ምሁራን አሉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ጋዜጣው ለበርካታ ጥናታዊ ስራዎች እንደ መነሻም ሆነ አጋዥ (ሪፈረንስ ) በመሆን ዛሬ ድረስ እያገለገለ ነው።
ጋዜጣው የተለያዩ ሥርዓቶችን ያለፈ በብዙ ውጣ ውረዶች መካከልም ህዝቡን ያስተማረና ያነቃ ነው የሚለው ጋዜጠኛ ተሾመ አሁን በዚህ የለውጥ ጊዜም እራሱን ከጊዜው ጋር ለማራመድ እየሞከረ መሆኑም የጋዜጣውን አቅም ይገልጻል። የተጀመረውን የለውጥ ስራ ማጠናከር፤ የስርጭት መጠኑን ማስፋትና በቀጥታ ህብረተሰቡ ጋር የሚደርስበትን መንገድ ማመቻቸቱ አዲስ ዘመንን ተፈላጊና ተነባቢ እንደሚያደርገው አመልክቷል።
«አዲስ ዘመን ከእኔ ጋር የተዋወቀው ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ነው፤ ንባብን በደንብ የተለማመድኩበት ጋዜጣም ነው። አዲስ ዘመን በወቅቱ ጠቅላላ እውቀት የሚባሉ ትምህርቶች የሚገኙበትና በህብረተሰቡ ዘንድም በጣም ተወዳጅ ጋዜጣ ነበር። ታላላቅ ባለሙያዎች ብዕራቸውን ያሳርፉበትና በአጠቃላይ እንደ አገር ታላቅ ጋዜጣ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሷል›› ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡት በተቋሙ የይዘት ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሄኖክ ስዩም ናቸው፡፡
እንደ ዶክተር ሄኖክ ገለጻ አዲስ ዘመን በእነዚህ ወርቃማ ዘመኑ በጣም ተወዳጅ የተለያዩ ፖለቲካዊ እሳቤዎች በነጻነት የሚንጸባረቁበት ሲሆን ፤ ከደርግ ዘመነ ሥልጣን አንድ ዓመት ጀምሮ ግን ጋዜጣው ፖለቲካን የማይነካ (የማይተች) ይልቁንም የሥነ ጽሁፍና የቋንቋ ጋዜጣ ለመሆን መገደዱን ያስታውሳሉ።
ደርግን አስወግዶ የመጣው የኢህአዴግ የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ምንም እንኳን ሳንሱር ቢቀርም ጋዜጠኛው ራሱን ሳንሱር ከማድረግ አልተላቀቀም፡፡ በዚህም በተለይ መንግስታዊ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ብቻ አተኩሮ መቆየቱን ጠቁመው አሁንም ቢሆን ጠንካራ የፖለቲካ ጉዳዮችን በማስተናገድ በኩል ሰፊ ክፍተቶች አሉበት ብለዋል።
ይህንን ሰፊ ክፍተት ለመሙላት ‹‹አዲስ ዘመን የማይነካው ጉዳይ እንዳይኖር፤ የህዝብ ጋዜጣ ሊሆን ይገባል›› በሚል መርህ ማንኛውንም አስተሳሰብ የሚራመድበት ነጻ መድረክ ሆኖ እንዲቀጥል አዲስ ዘመንም ሆነ ተቋሙ አዲስ የሪፎርም ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ ጋዜጣው የትውልድ ማመሳከሪያ (ሪፈረንስ) በመሆኑ የህትመት ውጤቶቹን ዘመናዊ በሆነ የዲጅታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ በሶስትና አራት ቅጂዎች (ኮፒዎች) የተለያዩ ቦታዎች ላይ እንዲቀመጡ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። አሁን ጋዜጣውም ሆነ ተቋሙ የራሱ ማተሚያ ቤት የሌለው መሆኑ ለስራው እንቅፋት ፈጥሯልና ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011
እፀገነት አክሊሉ