አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የ2 ነጥብ 76 ቢሊዮን ብር ብድር እና 488 ቢሊዮን ብር የድጋፍ ስምምነት ፊርማ ተካሄደ።
የብድር እና ድጋፍ ስምምነቱ ትናንትና በገንዘብ ሚኒስቴር አዳራሽ ተካሂዷል። በኢትዮጵያ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ አገራት መሪዎች በሁለቱም አገራት ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የመጣ ነው።
የፈረንሳይ እና የኢትዮጵያ መንግስት ለብድር እና ድጋፉ ስምምነት ካደረጉበት አጠቃላይ ገንዘብ ውስጥ 85 በመቶው የኢትዮጵያ መንግስት ለሚያካሂደው ሪፎርም በብድር መልክ ይቀርባል። ቀሪው ገንዘብ ደግሞ የህዝባዊ ተቋማት እና ኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማሳደግ የሚውል የቴክኒካል ድጋፍ ነው።
እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፤ በስምምነቱ የተካተቱት ብድር እና ድጋፍ የፈረንሳይ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ማሳያ ነው። በተጨማሪም ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ መንግስት የለውጥ አጀንዳዎች መሳካት ያላትን ድጋፍ የገለጸችበት አድርጎ መውሰድ ይቻላል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሚስተር ፍሬድሪክ ቦንተምስ በበኩላቸው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወርሃ ጥቅምት 2011 ዓ.ም ወደ ፈረንሳይ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በተመሳሳይ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። የአሁኑ ስምምነትም ሁለቱ መሪዎች በተገናኙባቸው ወቅቶች ያካሄዱትን አመርቂ ውይይት ተከትሎ የመጣ ድጋፍ እና ብድር ነው።
ሚስተር ፍሬድሪክ እንደገለጹት፤ ፈረንሳይ ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ለውጦች ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች። ገንዘቡ ለታለመለት አላማ እንዲውል የፈረንሳይ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል። ገንዘቡም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ቀጣይነት ማሳያ ይሆናል።
ፈረንሳይና ኢትዮጵያ ከ100 ዓመት በላይ የዘለቀ ግንኙነት ቢኖራቸውም የትብብር ስምምነት የጀመሩት ግን በ1960ዎቹ ውስጥ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በወቅቱም በባህል ሳይንሳዊ እና ቴክኒካል ትብብሮች ስምምነት ተደርጎ ነበር።
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011
ጌትነት ተስፋማርያም