አዲስ አበባ፡– አለመግባባቶችን በእውቀትና በመነጋገር ለመፍታት አንባቢ ትውልድ እንደሚያስፈለግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንትና ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲን ጎብኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት እንደተናገሩት “በኢትዮጵያ ውስጥ የምግብና የእውቀት ርሃብ አለ“ የእውቀት ችግሩ አርሰን እንዳንመገብ፤ እንዳንደማመጥና እንደ ህዝብ በጋራ እንዳንኖር እያደረገን ነው፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች ለፈተና ብቻ ሳይሆን ለማወቅ ቢያነቡ ፈተናውንም ያልፋሉ፤ ችግሩንም ይፈታሉ ብለዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በቅርቡ ተማሪዎች የሚወስዱት ፈተና ትንሹና የፈተናዎች ጅማሮ መሆኑን ተናግረው ጥረት የሚያደርጉ ሁሉ ያልፋሉ፡፡ ለዚህ ውጤት ለመብቃት ግን በተከታታይ ማንበብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡
“አንባቢ መሆን ልምምድ ይፈልጋል“ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንበብ ምንም እንኳ አድካሚ ቢሆንም በልምምድ ቀላል እየሆነ የሚሄድና ውጤታማ የሚያደርግ በመሆኑ ተማሪዎች የንባብ ልምዳቸውን እያዳበሩ እንዲሄዱ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ተማሪዎች በግል ከማንበብ ይልቅ በቡድን ማንበብን ቢለማመዱ አንዱ ከሌላው ጋር መደማመጥን ከማዳበራቸውም በላይ እርስ በእርስ የመረዳዳት ልምድም እንደሚያዳብሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
‹‹በርካታ ማንበቢያ ቦታ ያላቸው ሀገራት እውቀት ስላላቸው አለመግባባቶችን በውይይት ይፈታሉ፡፡ ማንበቢያ የሌላቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ደግሞ ችግሮችን በውይይት መፍታት አይችሉም›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማንበቢያ ቦታ ችግርን ለመፍታት ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲን መተካት የሚችልና በአንድ ጊዜ ለ 20ሺ ሰው አገልግሎት የሚሰጥ ቤተ መጻሀረፍት እየተገነባ ሲሆን ስራው ሲጠናቀቅም እውቀትን መገብየት የሚፈልጉ ሰዎች ሳይቸገሩ እንዲያነቡ፣ እንዲሰሩና እንዲመራመሩ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011
መላኩ ኤሮሴ