አዲስ አበባ፡- ለህግ የበላይነት መረጋገጥ የፍትህ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመላው አገሪቱ ከተውጣጡ ከ3 ሺህ በላይ ዳኞች፣ ዐቃብያነ ሕግ፣ ጠበቆችና የፍትሕ ዘርፍ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው በፍትህ ስራው ላይ እየተከናወነ ያለው የሪፎርም ስራ ውጤት የሚያመጣውና በአገሪቱ ላይ የህግ የበላይነት የሚረጋገጠው የፍትህ አካላት ቀጥተኛ ተሳትፎን ሲያደርጉ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ባለፈው አንድ ዓመት በዘርፉ የተካሄዱ የሕግ ማሻሻያዎች መሠረታቸው በተቋማት ላይ ትኩረት ያደረገና በተለይም አቅምን የመገንባትንና የመንግሥት ኃላፊዎችን ጨምሮ በሕግ የበላይነት የሚያምን ማኅበረሰብ የመፍጠር አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መደበኛ ያልሆኑ ማኅበራዊ ዕሴቶች ያላቸው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም ያሉት ዶክተር አብይ፤ በተለይም ሞራላዊ በሆነ መንገድ ኃላፊነትን መወጣት እና ሞራላዊ በሆነ መንገድ በማለም መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ከሁሉም የፍትህ አካላት የሚጠበቅ ወሳኝ ተግባር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከሞራላዊ ግዴታ በተጨማሪ ሞራላዊ መነሳሳትን ለማበልጸግና ለማሳደግ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ላይ በአገሪቱ ያሉ የፍትህ አካላት በሙሉ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸውም ነው የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም አስተዳደራቸው በፍትህ ሥራ ላይ ጣልቃ እንደማይገባ ለተሰብሳቢዎቹ ተናግረዋል።
ውይይቱ ከተጠናቀቀ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፍትሕ ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የዛፍ ችግኝ ተክለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011
እፀገነት አክሊሉ