አዲስ አበባ፡– አዲስ ዘመን ጋዜጣ ማንኛውም ሃሳብ የሚንሸራሸርበትና ወቅታዊ አጀንዳዎች በሳል በሆነ መንገድ የሚስተናገዱበት የህዝብ ጋዜጣ እንዲሆን የተለያዩ የሪፎረም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የይዘት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ተናገሩ። ጋዜጣው ዛሬ 78ኛ ዓመቱ ነው።
ዶክተር ሄኖክ ስዩም ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ጋዜጣው ባለፉት ዓመታት በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ የመጣ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ሁሉም ዜጋ በአገሪቱ የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ሃሳቡን በነጻነት የሚያንሸራሽርበት እንዲሁም ወቅታዊ ጉዳዮች የሚተነተኑበት ለማድረግ ሰፊ የሪፎርም ስራ እየተሰራ ነው።
እንደ ዶክተር ሄኖክ ገለጻ ጋዜጣውን ተነባቢ ለማድረግ በውስጥ ጋዜጠኞች ከሚጻፉ ጽሁፎች ባሻገር የውጭ ጻሀፍትን በመጋበዝና በኮንትራት በመቅጠር የተለያዩ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ የማድረግ ጅምርም መኖሩን ጠቁመዋል።
ከዚህ አንጻርም እንደ ሙከራ የዕለተ ቅዳሜ ጋዜጣን በአዲስ መልክ ወደ ስራ የማስገባት ሂደት ተከናውኖ ሰፊ ተነባቢነትና ተቀባይነት ተገኝቷል ፤ በቅርቡም የረቡዕ ጋዜጣን በአዲስ መልክ በማዘጋጀት ለንባብ ለማብቃት ዝግጅቱ መጀመሩን ጠቁመው፣ ከነዚህ ጋዜጦች የሚገኘውን ተሞክሮም በመቀመር ሁሉንም ጋዜጦች ወደ ከፍተኛ የተነባቢነት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ስራ እየተሰራም ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ጋዜጠኞችን በሙያው የበቁ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የተለያዩ ስልጠናዎችን የማመቻቸትና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ብቁ የሚሆኑባቸውን መንገዶች በመፈለግ ጋዜጣውን ወደ ቀድሞ ክብሩና ዝናው ብሎም ተነባቢነቱ ለመመለስ እየተሰራም መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ ልክ የሪፎረም ስራው ተጠናክሮ ቢቀጥልም የአንባቢው እይታ መቀየሩ ወሳኝ ነው ያሉት ዶክተር ሄኖክ፣ አንባቢው ከዚህ ቀደም ጋዜጣው የመንግስት አንደበት ብቻ አድርጎ ይመለከተው የነበረውንም አመለካከት ለመቀየር የምናነሳቸውን አጀንዳዎች በጥልቀትና እውነታውን በትክክል ባንጸባረቀ ሁኔታ በማቅረብ ተቀባይነትን ለማግኘትና
በህብረተሰቡ ውስጥ ለመግባትም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ከሞላ ጎደል ስኬቶች እየታዩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህ ማሳያው ደግሞ አዲሱ የቅዳሜ ጋዜጣ ነው ያሉት ዶክተር ሄኖክ፣ በአንባቢያን ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን እና ይህንን ይዞ ተጨማሪ ስራዎችን በማከል የአንባቢን ልብ ማሸነፍ እንደማይከብድ አስረድተዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚያሳትማቸው ጋዜጦች በይዘታቸው ተቀይረው በአንባቢያን ዘንድ ተወደውና ተፈልገው አልፈው ተርፈውም ገበያውን አሸንፈው እንዲወጡ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ሄኖክ፣ ከዚህ አንጻር ደግሞ ከሁለትና ሶስት ወር በፊት «ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ» ጋዜጣ የእሁድ ዕትምን በልዩ ሁኔታ በማዘጋጀት ለአንባቢ ቀርቧል ፤ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡና ጋዜጣውን ከሚያነቡ የህብረተሰብ ክፍሎችም አበረታች መልሶች ተገኝተዋል፤ ይህንንም በሌሎች ቀናት በሚታተሙ የሄራልድ ጋዜጦች ላይ ለማስፋት ታቅዷል።
በተመሳሳይ በኦሮሚኛ ቋንቋ የምትታተመውን በሪሳ ጋዜጣም ከሰኔ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ መልክ ወደ አንባቢያን ለማቅረብ እየተሰራ ከመሆኑም በላይ ጋዜጣዋን በሳምንት ሶስት ቀን እንድትታተምና የስርጭት አድማሷም እንዲሰፋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
«አዲስ ዘመን እንደ ስሙና እንደ አጀማመሩ የአዲስ ዘመን አብሳሪ ትክክለኛ የህዝብ ጋዜጣ እንዲሆን እየሰራን መሆኑን አንባቢዎቻችን ሊያውቁልን ይገባል። ጋዜጣው አሁን ምን እየሰራ ነው? ምን የተለየ ነገር አለው? ብለው ቢያዩም ብዙ መልካም ነገሮችን ያገኙበታል፤ የጎደለውን ደግሞ አብረን እናስተካክላለን» ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011
እፀገነት አክሊሉ