ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ጓደኞቻቸውን እንደ መልካም እድል በመጠቀም ልምድ መውሰድና የባህል ልውውጥ በማድረግ ግንኙነታቸውን ማጠናከርም አለባቸው።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፀጥታ ችግር ስጋት አለመኖሩንና የመማር ማስተማር ሂደቱ በአግባቡ እየተከናወነ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕ/ር ክንደያ ገብረህይወት ተናገሩ።
ፕ/ር ክንደያ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች እየተስተዋሉ ያሉ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዳይመጣ ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር በመሆን እየተሰራ ነው።
ትናንት በዩኒቨርሲቲው ከተማሪዎች ጋር ውይይት መደረጉን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ሰሞኑን በደብረ ማርቆስና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች በተፈጠረው ችግር በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ገልፀዋል፤ አግባብ አለመሆኑንና እያንዳንዱ ተማሪ ከእንደዚህ አይነት ድርጊት እንዲቆጠብ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
የፀጥታ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን አስቀድመን መለየት ላይ በትኩረት እየሰራን ነው ያሉት ፕ/ር ክንደያ ገብረህይወት ከአገልግሎት መጓደል ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችንም የአገሪቷ አቅም በሚፈቅደው መሰረት ለመፍታት እየሰራን ነውም ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዘርፎች፣ በቱሪዝም ዘርፉ ከአጎራባች ክልሎች ጋር በጋራ በመስራት፣ በግብርና እና ህክምና እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች ዙሪያ ጠንክሮ በመስራት ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚያገኟቸውን ጓደኞቻቸውን እንደ መልካም እድል በመጠቀም ልምድ መውሰድና የባህል ልውውጥ በማድረግ ግንኙነታቸውን ማጠናከር ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ፕ/ር ክንደያ ገብረህይወት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በድልነሳ ምንውየለት