በአዲስ አበባ ከተማ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቁስቋም በሚባለው አካባቢ በቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽ/ቤት አማካኝነት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለው የህፃናት አዳሪ ት/ቤት ፕሮጀክት ግንባታ 50 በመቶ ተጠናቀቀ።
ግንባታውን እያካሄደ የሚገኘው የአፍሮ ጺዮን ኮንስትራክሽን ድርጅት ማናጀር ኢንጂነር ዳንኤል ሃይሉ ዛሬ (ግንቦት 29) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ግንባታውን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
ፕሮጀክቱ እስከ ነሃሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ ጊዜ የተቆረጠለት ቢሆንም፤ አካባቢው ለግንባታ የተመቸ አለመሆን፣ ወደ ፕሮጀክቱ የሚያስገባው መንገድ አመቺ ባለመሆኑ የግንባታ ዕቃዎችን በቀላሉ ለማቅረብ ማዳጋቱ እና ክረምቱ መግባት መጀመሩ የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜውን ሊያራዝመው ይችለል የሚል ስጋት እንዳላቸው ኢንጂነሩ ገለጸዋል።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግንባታው 50 በመቶ ያህል መጠናቀቁን የገለጹት ኢንጂነሩ፤ ለዚህ ስኬት የአካባቢው ነዋሪዎች ለፕሮጀክቱ እያደረጉ ያለው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ (ፎርማን) ወጣት በለጠ ጸጋዬ በበኩሉ፤ ግንባታው በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝ ገልጾ፤ የሰራተኞች ተነሳሽነት ጥሩ በመሆኑ ግንባታውን በጥራትና በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ጥረት እየደረገ መሆኑን አስታውቋል።
እንደ ወጣት በለጠ ገለጻም፤ ፕሮጀክቱ እስካሁን ከ130 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል ፈጥሯል።
ፕሮጀክቱ የካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው አማካኝነት የመሰረተ ድንጋዩ መቀመጡ ይታወሳል።
በወይንሸት ካሳ
ፎቶ በሀዱሽ አብርሃ