ውልደቷ እና እድገቷ አዲስ አበባ ካሳንቺስ አካባቢ ነው:: አንዳንዶች ‹‹እማማ ሸክላ›› በሚለው ቅጽል ስሟ ያውቋታል – ወይዘሮ ብክርቲ ተወልደን:: ቅዳሜ እና እሁድ ለእማማ ሸክላ የእረፍት ቀናት ብቻ አይደሉም:: የሠፈሯን ሕፃናት ሰብስባ ከተፈጥሮ ጋር እንዲተዋወቁ እና እንዲጫወቱ የምትጠቀምባቸው ቀናቶች ናቸው:: እጆቻቸውን ከሞባይል እንዲያርቁ፤ አይኖቻቸውንም ከቴሌቪዥን ላይ እንዲያነሱ በማለት የሰፈር ልጆች ሰብስባ ጭቃ በማቡካት ታጫውት ነበር::
ሕፃናቱም ቅዳሜ እና እሁድ ለተወሰነ ሰዓት ተጫውተው ወደ የቤታቸው ይሄዳሉ:: በተደጋጋሚ መምጣታቸውን እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር መቆራኘታቸውን ወደዱት:: የሚገናኙበትን የወይዘሮ ብርክቲን ቤት ‹‹እማማ ጭቃ ቤት›› የሚል ስያሜ ሰጡት:: እርሷም በወጣላት ስም ደስ ተሰኘች:: የሸክላ ሙያ ማሰልጠኛዋን ስትከፍት ‹‹እማማ ሸክላ›› በሚል መጠነኛ ማስተካከያ ብቻ በማድረግ ስያሜውን አፀደቀችላቸው::
የወይዘሮ ብርክቲን ሕይወት መለስ ብለን በጥቂቱ እናስታውስ:: ከ16 ዓመታት በፊት ብርክቲ ሀገሯን ትታ ወደ አውሮፓ ተሰደደች:: የስደት ጥሩ የለውምና የስደት ሕይወቷ አስቸጋሪ ነበር:: ስደት እጇን ዘርግታ አልተቀበለቻትም ቢባል ይቀላል:: በተሰደደችበት ሀገር ጥሩ ሕይወት የሚኖረው ሰው እንኳን ስደቱን ወዶት አልተመለከተችውም:: ሁሉም ሀገሩን ይናፍቃል:: እርሷም ሀገሯን ናፈቀች:: ወደ ሀገሯ መመለስን አብልጣ ፈለገችው:: በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ምን ይዤ ልመለስ?›› ስትል አሰበች:: ዕድል እና ሃሳብ ተገጣጠሙ:: የሥዕል እና የሸክላ ሥራ የትምህርት ዕድል አገኘች::
ከዚህ ቀደም ሥዕል ስላ የማታውቀው ወይዘሮ ብርክቲ የሥዕል ሙከራዋ ጥሩ እንደሆነ እንደውም አንዳች የጥበብ ተሰጥኦ በውስጧ እንዳለ በመንገር እንድትቀጥልበት ቢነገራትም አሻፈረኝ አለች:: ተማሪ ያሏትን ለማስደሰት ግን በሳምንት አንድ ቀን ብቻ እየገባች ትማር ነበር:: ብቻ ልቧ ለሸክላ ሥራ አደላ::
የሸክላ ሥራው ምንም ዓይነት የተጋነነ ነገር አለመፈለጉ፣ ብዙ ወጪ አለማስወጣቱ፣ በትንሽ ወጪ ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻል ተረዳች:: ሥራው የትኛውንም አገር ግብአት አለመፈለጉን ተረድታ ወደ አገሯ ተመልሳ ብትሠራበት ውጤታም እንደምትሆንበት በማመን እርሷ ተጠቅማ ሌሎችንም ለመጥቀም በሚገባ ተምራ ከሰባት ዓመት የስደት ሕይወት በኋላ ወደ ናፈቀቻት ፊቷን ወደማታዞርባት እናት ሀገሯ ተመለሰች::
ወደ አገሯ ከተመለሰች በኋላም ከፌዴራል ጥቃቅን እና አነስተኛ ቢሮ ማሰልጠኛ የሸክላ ሥራን ድጋሚ ሰልጥና የምስክር ወረቀቷን ተቀበለች:: በተለያዩ ቦታዎች ልጆችን በማጫወት፣ የፌስቱላ ታማሚዎችን በማሰልጠን እና ትምህርት ቤቶች ላይ በማስተማር ሥራዋን ጀመረች:: እንዲሁም ኩልስማ፣ ብርክቲ እና ጓደኞቻቸው የተባለ የሽርክና ማህበርን ከሌሎች ባልደረቦቿ ጋር በማደራጀት የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን፣ ‹‹ላቀች››፣ ‹‹ምርጫ›› የተባሉ የሸከላ ምድጃዎችን በመሥራት እና ሴቶችን በመቅጠር ተጠቃሚ እንደሆኑ ማድረግ ቻሉ::
አብዛኞቹ በልምድ የሚሠሩ ሸክላ ሠሪዎች በአንድ ምርት ብቻ የተገደቡ ናቸው:: እርሷ ሙያውን የቀሰመችው በትምህርት ስለሆነ ሁሉንም የሸክላ ሥራዎች ትሞክራለች ብቻ ሳይሆን መሥራት ትችላለች:: የአበባ ዕቃ (ጌጣ ጌጥ)፣ ጀበና፣ ማንደጃ፣ እንሥራ፣ ድስት እና የመሳሰሉትን ትሠራለች::
አንዳንድ ጊዜ በአገራችን የሚሠሩ እጆች አይከበሩም:: ሸማኔው ‹‹ቁጢት በጣሽ››፤ ሸክላ ሠሪውም
‹‹አፈር ገፊ›› የሚል ስያሜ ወጥቶሎት ነበር:: በአውሮፓ በነበራት ቆይታ ግን ለሚሠሩ ጥበበኛ እጆች አልባሌ ስም ከማውጣት ወይም ከመስደብ ይልቅ ሲከበሩ እንዲሁም ሲወደሱ ተመልክታለች:: እርሷም ይህ ስድብ የሚቀየረው በእያንዳንዱ ሠው ሕይወት ገብቶ ሲዳስሰው እና ሲዳብሰው እንደሆነ ታምናለች:: ያን ጊዜ ሙያው ምን ያህል የተከበረ፣ ጥሩ ሥራ እና የተወደደ እንደሆነ ይገባዋል ትላለች::
የሸክላ ሙያ ላይ በመሠማራቷ እርሷ ላይ የደረሰባት ነገር የለም:: ከውጭ አገር ተምራ በመምጣቷ ነገሮች የቀለሉላት ይመስላል:: አንዳንድ ሰዎች ግን ‹‹ምን ሆነሽ ነው? ብር ይዘሽ ስላልመጣሽ ነው ሸክላ የምትሠረው? ተቸግረሽ ነው? ብለው ደፍረው ይጠይቋት ነበር:: አንዳንዶቹም ደግሞ ፊታቸው ላይ የሚነበብ ነገር ቢኖር እንኳን ሃሳባቸውን በቃላት ለመግለጽ ሲተናነቃቸው አስተውላለች:: ይሁንና እነዚህ ሁኔታዎች ስሜቷ ላይ የፈጠሩት አንዳችም ነገር የለም::
ነዳያን ቁጭ ብለው ሲለምኑ ገንዘብ ከመለመን ይልቅ ‹‹ ኑ ሸክላ ሥሩ›› ብትላቸው ‹‹ሸክላ ሠሪ ከዘሬም የለብኝም::›› የሚል ምላሽን ይሰጧታል:: ልመናን ልክ በዘር እንደተሰጣቸው አድርገው እየለመኑ ስትመለከት እጅጉን ታዝባለች:: ሌላ ደግሞ ከወረዳ ለሸክላ ሥራ ስልጠና ተብለው የሚላኩ አንዳንድ ሴቶች ደስተኛ እንደማይሆኑም ተመልክታለች:: ምክንያታቸው የአመለካከት ችግር ነው:: እንደነዚህ አይነት ያሉ ነገሮች ካልሆኑ በስተቀር የጎላ የሚባል ችግር አልገጠማትም::
እማማ ሸክላ ስለ ሸክላ ሥራ አውርታ አትጠግብም:: ከኬሚካል የጸዳ መሆኑ፤ በምርት ወቅትም ይሁን ምርቱ ግልጋሎት ላይ ሲውል ጤና ላይ ጉዳት የማያስከትል መሆኑን ትናገራለች:: ምንም አይነት ኪሳራ የለውም:: አዋጭ ቢዝነስ ነው:: እንደውም የሁላችንም የሆነችውን ጀበና በኤክስፖርት ደረጃ ለማድረስ ስልጠናዎች ቢሰጡ፤ ትምህርት ቤቶች እና ማሰልጠኛ ተቋማትን ማስፋፋት ቢቻል ሙያውን የበለጠ ለማሳደግ ይረዳል ባይ ናት::
በአገራችን የሸክላ ሥራ በብዛት የሚመረተው በባህላዊ መንገድ ነው:: ብዙ ሸክላ ሠሪዎች ይኑሩ እንጂ የማሰልጠኛ ተቋማት የሉንምና በሁሉም ወገን በኩል ትኩረት እንዲሰጠው ስትናገር ትደመጣለች:: በትምህርት ቤቶች አሁን አሁን ጥሩ ጅምሮች እየታየ ሲሆን፤ እርሷ እንድታስተምር አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በጠየቋት መሠረት እየሰራች መሆኗን ትገልጻለች::
በተለምዶ እስከከ ዛሬ ድረስ ሸክላ ሲሠራ የሚቃጠለው በኩበት እና በእንጨት ነው:: በዘመናዊ ከተባለ ደግሞ ኤሌክትሪክ፣ ጋዝ እና ሌሎች የተለዩ ማቃጠያዎች ናቸው:: ይህንን ችግር ለመቅረፍ የከሰል ተረፈ ምርቱን (ደቃቅ ከሰል) እንደ ጥፍጥፍ በመሥራት በዛ በማቃጠል የምትሠራ ሲሆን፤ ምንም አይነት ጭስ ባለመኖሩ ያለ ምንም ስጋት በመስራት ላይ ትገኛለች:: ዕውቀቷን ለሌሎች ማጋራት የማትሳሳው እማማ ሸክላ ትምህርት ቤቶችም ይሁኑ ማሰልጠኛ ተቋማት ይህን ዘዴ በመጠቀም መሥራት እና ማስተማር እንደሚቻላቸው ትመክራለች::
እማማ ሸክላ ልክ እንደ ጌም ዞን (የልጆች መጫወቻ) ተብለ እንደተሰየሙት ልጆች ጭቃን እያቦኩ፤ እንዝርት እየፈተሉ እና ሌሎች ክዋኔዎችን እየከወኑ ባህላዊ ጨዋታዎችን እንዲጫወቱ እያደረገች ትገኛለች:: ደግሞ በጣም ሩጫ ላይ ናት:: ለምን ቢባል? የሸክላ ማሰልጠኛ ተቋሙን ከመመሥረት ባሻገር የሸክላ ሥራ ተደራሽ ሆኖ ማየት እና ዕድገቱንም ማየት ትፈልጋለችና::
ነገን ቁጭ ብላ ከመጠበቅ ይልቅ ዛሬ ጉልበቷ ሳይደክም ባላት አቅም እና ችሎታ እርሷ መሠረቱን ጥላ ሌሎች እንዲረከቧት ለማድረግ በብርቱ እየጣረች ነው:: ነገር ግን በሽመናው ይሁን በሌሎች ሥራዎች የወጣቱ ክፍል ተሳትፎ እጅግ አናሳ ነው:: ሀገር ቤት ሆኖ ሸክላ ከመሥራት ይልቅ ወደ አረብ አገር ሄዶ ስደትን መምረጥ ይታያል:: በዚህ እና በሌሎች ምክንያት የራሳችንን እናዳናጣ በማለት እንዴት እንደሚሠራ በማሰልጠን አሁን ላለው ትውልድ በማስተማር እና በማሳየት ድርሻዋን እየተወጣች ነው::
አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ቀጨኔ አካባቢ ልዩ ጥበብ አለ የምትለው ወይዘሮ ብርክቲ፤ ሊወደስ እና ሊሞገስ የሚገባ ሰፈር ነው ትላለች:: የሸክላ ሥራ ሙያው አንድ ቦታ ላይ መቀመጥ (መገደብ) የለበትም:: አሁን ላይ የሸክላ ሥራ በስፋት የሚታየው ቀጨኔ ሠፈር ሲሆን፤ ሙያው እዛው አካባቢ ተወስኖ እንዳይቀር እና ሁለም ሠው እንዲረዳው፤ እንዲያውቀውና እንዲጠቀምበት ለማድረግ ያለምንም የእውቀት ስስት ችሎታዋን እንካችሁ እያለች ነው::
የሁለት ሴት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ ብርክቲ ልጆቿ የራሳቸውን ሕይወት የመሠረቱ ናቸው:: እርሷ የጀመረችውን ሥራ እንድትገፋበት የሚያግዟት ሲሆን፤ ዛሬ ላይ የሸክላ ሥራ ብቻ በመሥራት ዓላማዋን ዳር ለማድረስ ላይ ታች እያለች ትገኛለች:: በእርግጥ ለእስካሁን ጥረቷ የተለያዩ ሽልማቶች ተሰጥቷል:: በቀድሞ ስያሜው ከባህል እና ቱሪዝም፤ ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ ከውሃ እና ኢነርጂ ባለስልጣን የዋንጫ እንዲሁም የምስክር እና የማበራታቻ ወቀረቶች ተበክርቶላታል::
ወጣቱ ትውልድ ቁጭ ብሎ ‹‹በተማርኩበት ብቻ ካልሠራሁ›› ከሚል እና ጤነኛ ሆኖ ከመለመን ይልቅ ሸክላ ሥራ ውጤታማ እንደሚያደርገው በመተማመን ቢሠራበት ከራሱ አልፎ የሌሎችን ሕይወት መቀየር እንደሚቻለው ስትናገር ትደመጣለች:: ይህንን የተረዱ በአርክቴክት፣ ኢንጂነሪንግ እና በሌሎች ሙያዎች የተመረቁ ተማሪዎች እርሷ ጋር ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሲሆን፤ እነርሱም በሙያቸው እገዛ ያደርጉላታል::
ሁለም ሠው ፓይለት፣ ኢንጂነር፣ ሳይንቲስት…. መሆን አይቻላቸውምና እውቀት ያላቸው ሰዎች በሸክላ እና በሌሎች ትኩረት ባልተሰጣቸው የሙያ ዘርፎች ላይ በመሠማራት እውቀታቸውን በመጠቀም እና ተጨማሪ ምርምሮችን በማድረግ እገዛ ማድረግ እንደሚችሉ ታስረዳለች::
እንደ ጃፓን እና ቻይና ያሉ አገራት የሸክላ ሥራን በማዘመን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መትረፍ ችለዋል:: በእኛ አገር በርካታ እውቀት እና ግብአት ይኑር እንጂ ሠሪዎቹ ግን የታደሉ ጥበበኛ እጆች ብቻ ናቸው:: ሌላውም ወደ ጥበብ ቢጓዝ በብዙ እንደሚያተርፍ የእማማ ሸክላ ሕይወት ምስክር ነው::
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2016