ሴቶችን ከውበት ሳሎን ያዋለው የጥፍር ሥራ

‹‹የሴት ልጅ ውበቷ ጸጉሯ ነው›› እንደሚባለው ሁሉ አሁን አሁን ደግሞ ሴቶች ለእጆቻቸውና ለእግሮቻቸው ጥፍር አብዝተው ሲጨነቁና ሲጠበቡ ማስተዋል ተለምዷል፡፡ የእጅም ሆነ የእግር ጥፍሮችን በንጽህና መጠበቅ ወንዱንም የሚመለከት ጉዳይ ቢሆንም፣ ሴቶችን ግን የጥፍራቸው ጉዳይ በእጅጉ ያሳስባቸዋል። ከንጽህና አለፍ ብሎም የእጅና የእግሮችን የጥፍር ውበትን መጠበቅና ማስዋብ ለሴት ልጅ የውበት መገለጫ መሆን ከጀመረ ቆይቷል፡፡

ለዚህም ነው አብዛኞቹ ሴቶች ጊዜ ባመጣቸው የተለያዩ የመዋቢያ ቁሳቁሶች ጥፍራቸውን ሲያስውቡ የምንመለከተው፡፡ ሴቶች ጥፍራቸውን ለማስዋብ ከሚጠቀሟቸው ቁሳቁሶች መካከል ‹‹ጥፍር ቀለም›› ቀዳሚው ነው፡፡ ቀደም ሲል ጥፍራቸውን አሳድገው በሚፈልጉት ቅርጽ ሞርደው በማሾል ይዋቡበትም ነበር፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከተለያዩ ግብዓቶች እና ንጥረገሮች ውህድ የሚሠራው ሰው ሠራሽ (አርቴፊሺያል) ጥፍር ዋነኛው የሴቶች መዋቢያ ሆኖ መጥቷል። በመሆኑም ሴቶቹ ተፈጥሯዊ ጥፍራቸውን ማሳደግ ሳይጠበቅባቸው በሚፈልጉት የጥፍር ቅርጽ ዓይነትና ርዝመት ጥፍራቸውን ለተለያዩ ፕሮግራሞች ይሠራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅትም በየውበት ሳሎኑ ጥፍር የሚሠሩ እንስቶች ቁጥር በርክቷል፡፡ ይህን አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች እንዲሁም ሙያውን የሚያስተምሩ ማሰልጠኛዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡ አገልግሎቱ ጫን ያለ ዋጋ የሚጠይቅ መሆኑ ብዙዎች ወደ ሥራው እንዲያዘነብሉ እያደረጋቸውም ነው፡፡ በሌላ መልኩ ለሥራ ዕድል ፈጠራም አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡

ከዚህ ቀደም ጸጉራቸውን ብቻ ለመሠራት ወደ ውበት ሳሎን ያቀኑ የነበሩ አብዛኞቹ እንስቶች አሁን ላይ ጥፍራቸውን ለመሠራት ጭምር ወደ ውበት ሳሎን ያቀናሉ፡፡ የሴቶች የውበት ሳሎን ሰፊ ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙዎች አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉት አስቀድመው በሚይዙት ቀጠሮ መሠረት እንደሆነ የሙያ ባለቤቶች ይናገራሉ፡፡

ፍላጎት አብርሃም (ስሟ የተቀየረ) የጥፍር ሥራ ትምህርት ተምራ በሥራ ውስጥ የምትገኝ ወጣት ናት፡፡ ሙያውን ለመማር የሁለት ወር ተኩል ጊዜ ወስዶባታል። በጥፍር ሥራ ላይ ከባዱ ነገር አገልግሎቱን ፈልገው የሚመጡ ደንበኞችን ስሜት ጠብቆ ማስተናገድ እንደሆነም ተናግራለች፡፡ ትምህርቱ መሠረታዊ የሚባሉ የጥፍር ሥራዎችን ሲያካትት በቶሎ ለመልመድና ብቁ ለመሆን እንደሰው አቀባበል የሚወሰን መሆኑን አስረድታለች፡፡

በሥራው ላይ ለአምስት አመት ያህል የቆየችው ወጣት ፍላጎት፤ የጥፍር ሥራው ዓይነት እንደ ፕሮግራሙ ዓይነት ይለያያል ትላለች፡፡ ደንበኞች ወደ ውበት ሳሎኑ ሲመጡ መሠራት የሚፈልጉትን ዲዛይን ከተለያዩ ገጾች ላይ ተመልክተው እንደሚመጡ ጠቅሳ፣ እሷ ግን በፎቶ ተመልክተው የመጡትን ሥራ ከመሠራታቸው አስቀድሞ ሙያዊ ምክር ትሰጣቸዋለች፡፡ የጥፍር ዲዛይን እና የምንጠቀመው የጥፍር ቀለም እንደየ ጥፍራችን ቅርጽና ቆዳ እንዲሁም ቀለማችን ይለያያል ብላ ታስረዳቸዋለች፡፡

በመሆኑም ጠቆር ያለ የቆዳ ቀለም ላላቸው ደንበኞች ፍክት ያለ የጥፍር ቀለም፣ ነጣ ያለ የቆዳ ቀለም ላላቸው ደግሞ ደብዘዝ ያሉ የጥፍር ቀለሞችን በመጠቀም እነ ፍላጎት የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ለማሟላትና ለማስደሰት ይጥራሉ፡፡ እሷ እንዳለችው፤ በአሁኑ ሰዓት በብዙዎች ዘንድ የተለመደው የጥፍር ሥራ ዲዛይን ዓይነት ‹‹ፍሬንች›› ዲዛይን የተባለው ነው፤ ይህም ለሁሉም የቆዳ ቀለም ዓይነት የሚሆን እና ለፕሮግራምም ሆነ ለአዘቦት ቀን ቢደረግ ቀለል ያለና ልዩ ውበትን የሚያላብስ የብዙዎች ምርጫ ነው፡፡

ሌላኛዋ የጥፍር ሥራ ባለሙያ ናርዶስ ከበደ (ስሟ የተቀየረ) በሥራው ሁለት አመት ቆይታለች፡፡ ናርዶስ የጥፍር ሥራ ይስባት ነበርና ለአንድ ወር ከ15 ቀን የሚሰጠውን ሥልጠና ከወሰደች በኋላ ሥራውን ተቀላቅላለች፡፡ የጥፍር ሥራ ዓይነቶች የተለያዩ እንደሆኑ ስትገልጽ ፊትለፊቱ ላይ የአራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ‹‹ስኩዌር››፣ የእንቁላል ቅርጽ ያለው ደግሞ ‹‹ኦቫል›› እንደሚባሉ ጠቅሳ፤ የጥፍር ዲዛይኖቹ ቁመትም እንደ ደንበኛዋ ፍላጎት እንደሚወሰን ነው የተናገረችው፡፡

‹‹ጥፍሮቹ ሰው ሠራሽ እንደመሆናቸው ቆይታቸውም ውስን ነው›› የምትለው ናርዶስ፤ ለአጭርና ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችሉ የጥፍር ዓይነቶች እንዳሉም ገልጻለች። እሷ እንዳብራራቸው፤ ልጥፍ የሚባለው በሰዎች የጥፍር ልክ ተመሳስሎ የተሠራ ሲሆን፣ በራሱ ለጥፍር መለጠፊያ ተብሎ በተዘጋጀ ማጣበቂያ ጥፍራቸው ላይ ከተለጠፈ በኋላ በሚፈለገው ቅርጽ እና ቁመት ተሞርዶ ይሠራል። ሌላኛው ሰው ሠራሽ ጥፍር ጄል ሲሆን በእንስቷ ጥፍር ላይ ተሞልቶ ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ ማድረቂያ ማሽን ውስጥ ይደርቃል፡፡ በተለያዩ ኬሚካሎች እና ፓውደሮች ተቀላቅሎ የሚዘጋጀው ደግሞ አክሌሪክ ይባላል፡፡

አክሌሪክ የጥፍር ዓይነት ከባድ የኬሚካል ሽታ ስላለው ለነፍሰ-ጡር ሴት የማይመከር ሲሆን ባለሙያዎችም ሲሠሩ የራሳቸውን ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ይህም ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የጥፍር ዓይነት ነው፤ የጥፍሩ ዓይነት ከተመረጠ በኋላ የሚቀባው የጥፍር ቀለምም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው፡፡

የጥፍር ቀለሞቹ በውበት መጠበቂያ ሱቆች ይገኛሉ፤ ቀለሞቹን በቤታቸው መቀባት ይችላሉ፡፡ ሌላኛው ደግሞ ሺላክ ለውበት እና ዲዛይን ለማድረግ የሚውል ነው፡፡ ይህ የጥፍር ቀለም ዓይነት ለማስለቀቅ የራሱ ጥንቃቄ ማድረግ ይፈልጋል፤ ረጅም ጊዜ ሳይለቅ የሚቆይ በመሆኑ ሴቶች በራሳቸው ጥፍር ላይ ለመቀባትም ቢሆን ወደ ውበት ሳሎን ጎራ እንደሚሉ ናርዶስ ትናገራለች፤ ‹‹ጥፈራቸውን የተሠሩ እንስቶች ለማስለቀቅ ሲፈልጉም ጥንቃቄ ቢያደርጉና ወደ ውበት ሳሎኑ ቢያመሩ መልካም ነው›› ትላለች፡፡

ሌላኛዋ ባለሙያ ገሊላ አስራት ትባላለች፡፡ አንድ እንስት ጥፍሯን ለመሠራት ወደ ውበት ሳሎን ስትመጣ የሚወስደው ጊዜ፣ የምታልፈው ሂደት እንደምትሠራው የጥፍር ዓይነት የሚወሰን መሆኑን ጠቅሳ፤ ልጥፍ ከሆነ አጭር ጊዜን ይወስዳል ትላለች፡፡ ለዚህም በመጀመሪያ ተፈጥሯዊ ጥፍርን የማጽዳትና መቁረጥ እና የመሞረድ ሂደቶች አሉት፡፡ ሙሌት እና ጄል ደግሞ ለማድረቅ ጊዜ ከመውሰዱ ባሻገር የሚቀባው እንደ ዲዛይኑ ከአንድ ሰዓት በላይ ይወስዳል፡፡ ጥፍር ቀለምን በመጠቀም ብቻ ከሚሠራው ዲዛይን ውጪ የተለያዩ አብረቅራቂ ፈርጦች እንደየፍላጎታቸው የሚደረግ መሆኑን አስረድታለች፡፡

ለእያንዳንዱ አገልግሎት የሚኖረው ክፍያም እንደየ አካባቢው የሚለያይ ሲሆን፤ ሺላክ ጥፍር ቀለምን ለመቀባት ከ150 ብር ጀምሮ እስከ ሦስት መቶ ብር፣ ልጥፍ ከሺላክ ጥፍር ቀለም ጋር ዘጠኝ መቶ ብር፣ ሙሌት ደግሞ ከአንድ ሺህ እስከ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር፣ አክሌሪክ የጥፍር ሥራ ከሁሉም ከፍ ያለ እንደመሆኑ ከ1500 ብር በላይ መሆኑን ገልጻለች፡፡

በመጨረሻም መዋቢያ ቁሳቁሶቹ የራሳቸው የሆኑ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳላቸው የምትገልጸው ገሊላ ጥፍራችን አየር የሚፈልግ በመሆኑ ጥፍራቸውን አብዝተው የሚሠሩ ሴቶች በተደጋጋሚ ባይሠሩ እና ተፈጥሯዊ ጥፍራቸውን በማይጎዳ መልኩ የጊዜ ልዩነት እየጠበቁ ቢሠሩ የተሻለ እንደሆነ ሙያዊ አስተያየቷን በመስጠት ሃሳቧን ቋጭታለች፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You