የሳክስፎኑ ጌታ ጌታቸው መኩሪያ

ውልደቱ በ1928 ፋሺስት ኢጣልያ ሀገራችንን በወረረበት ወቅት፤ በይፋትና ጥሙጋ አውራጃ፣ ልዩ ስሙ ዝግባ በተባለ ሰፈር ነበር። ልጅነቱን ካሳመሩለት የሙዚቃ መሳሪያዎች ክራር እና ዋሽንት የሚወዳቸው ነበሩ። ከልጅነቱ ጀምሮ ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር አለው፤ በራዲዮ ሞገድ አብዝቶ እና በልዩ ተመስጦ እያዳመጠ አድጓል። ከዚያም የአንድ አመት ህጻን ሳለ ወደ አዲስ አበባ መጣ። እድሜው ለትምህርት ሲደርስ ከእኩዮቹ ጋር ወደ ትምህርት ቤት ቢላክም እሱ ግን ገና በጊዜ የነፍስ ጥሪውን ያወቀ ይመስላል።

ከትምህርቱ ይልቅ በማዘጋጃ ቤት እየተመላለሰ ሙዚቀኞችን በልዩ ሁኔታ ሲመለከት ይውላል። በየእለቱ ወደ ቴአትር ቤቱ ሲመላለስ የተመለከቱት የቴአትር ቤቱ ኃላፊዎችም የ13 አመቱ ታዳጊ ለሙዚቃ ያለውን ፍቅር በመረዳት ዋሽንትና ከበሮ መጫወት ይችል ነበር እና በ1940 ዓ∙ም በ10 ብር ወርሀዊ ደሞዝ ቀጥረውት የሙዚቃ ህይወቱን ‹‹ሀ›› ብሎ ጀመረ።

የኢትዮጵያ የሳክስፎኑ ንጉስ፣ ሳክስፎኑን አናጋሪው፣ ከአንድ ድምጻዊ ጋር ብቻውን ሙሉ ኦርኬስትራን የሚይዘው ከትውልድ ሀገሩ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን አገኘ። የሙዚቃ መሳሪያው ሳክስፎን ሲነሳ አብሮ ስሙ የሚነሳው አርቲስት ጌታቸው መኩሪያ በዛሬው የዝነኞች ገጻችን የምንዘክረው ይሆናል።

ገና በ13 አመቱ በ10 ብር ደሞዝ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋትነት፤ ከዚያም ታምቡር፤ እንዲሁም ክላርኔት የተሰኘ የሙዚቃ መሳሪያን በማጥናት የየመሳሪያዎቹ ተጫዋች ሆነ። ከዚያም ሳክስፎንን ተለማምዶ ሳክስ የሙዚቃ መሳርያን መጫወት ጀመረ። ለሙዚቃ ያለው ፍቅር ከልጅነቱ ጀምሮ ነበርና ምዕራብያውያኑ ሙሴ ነርሲስ ናልባንዲያን እና ፍራንሲስ ዙቤኬር የተግባር ስልጠና በመስጠት ጌታቸው ችሎታውን እንዲያዳብር አስተዋጽኦ አድርገዋል። በ1948 ዓ.ም የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ የሀገር ፍቅር ማህበር ሲመሰረት ጌታቸውም “ብቁ” ተብለው ከተመረጡ ሙዚቀኞች አንዱ መሆን ቻለ። ከዚያ በፊት በብሄራዊ ቴአትር ለ17 አመታት በሙያው ሲያገለግል ቆይቷል።

በሀገር ፍቅር፣ በፖሊስ ኦርኬስትራ፣ በብሄራዊ ቴአትር እና በማዘጋጃ ቤት ለአምስት አስርት አመታትን በሙዚቃ ስራው ሲቆይ የመምህርነት ስራንም ይሰራ ነበር።

በ1986 በስራ ላይ የሚያሳልፍበት ጊዜ አብቅቶ ማለትም በእድሜ ጣርያ አማካኝነት የጡረታ ጊዜው ደርሶ ስራውን አቆመ። ጌታቸው መኩርያ የሚጫወታት ሳክስፎን የራሷ ቋንቋ አላት ይባልም ነበር። በፖሊስ ኦርኬስትራ በነበረበት ወቅትም የሚሰማውን ቅሬታ በሳክስፎኑ ነበር የሚገልፀው ተብሎ ሲነገርለት ነው የነበረው።

ነገር ግን ጌታቸው እና ሙዚቃ በተለይም ሳክስፎን የሚለያዩ አይደሉምና ጡረታ ከወጣ በኋላ በሸራተን ሆቴል መስራት ጀመረ። በዚያ ሲሰራም በስራው የተሳቡ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ከሙዚቃ መሳሪያው (ሳክስፎን) ጋር የሚያደርገውን ንግግር ለማድመጥ ጌታቸው ወደሚገኝበት ቦታ መጉረፍ ጀመሩ። በሸራተን በሚሰራበት ወቅት የሚጫወትበት ሳክስፎን በማርጀቱ ሼህ መሀመድ አላሙዲን አዲስ ሳክስፎን ከውጭ አስመጥተው ሰጥተውት ነበር። ታዲያ ይህች ከጌታቸው እጅ የማትለየው ሳክስፎን በአንድ ወቅት ጌች ስራውን አቅርቦ ሲመለስ፣ ከተሳፈረበት ታክሲ ላይ ሲወርድ ሹፌሩ ሳክስፎኑን ይዞበት ጠፋ፤ በድጋሚም ሊያገኛት አልቻለም ነበር።

በሙዚቃ ስራው የሚወደደው ጌታቸው መኩሪያ እንደሱ ካሉ አንጋፋ ሙዚቀኞች (ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ፣ ከድምጻዊት ሂሩት በቀለ) ጋር በመሆን ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እጅ ወርቅና ሁለት ሺህ ብር ከአንዴም ሁለት ጊዜ ሽልማት ተበርክቶለታል።

ምንም እንኳን ሳክስፎን የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያ ባይሆንም፤ ጌታቸው ሳክስፎንን ሲይዘው ግን በትዝታ ስልት ልብን የሚሰውር፤ በባቲ እና በአምባሰል ትኩረትን የሚስብ ነበር።

የሀገራችን የጥንት የአባቶቻችን ታሪክ የሆነውን የድል አድራጊነት ገድል የሚገልጽ ሽለላ እና ሌሎች ዜማዎችን በሳክስፎኑ በማዜም ትዝታን ይቀሰቅሳል፤ ልዩ ወኔንም ያላብሳል። በሚጫወትበት ጊዜም በመድረኩ ላይ በመንቀሳቀስ ጭምር የተዋናይ ያክል ኢትዮጵያዊ አለባበስን ጭምር ተጎናጽፎ ስራውን በማቅረብ በታዳሚያን ዘንድ ልዩ ስሜትን ይፈጥራል።

ጌታቸው በሸራተን እየተጫወተ ባለበት ሰዓት ልዩ አጋጣሚ ተፈጠረለት። በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለውና አዳዲስ ድምጾችን ለታዳሚያን በማቅረብ የሚታወቀው የ‹‹ደች ባንድ ዘ ኤክስ›› የተመሰረተበትን 25ተኛ አመት የብር ኢዮቤልዩ ለማክበር በዝግጅት ላይ ነበር። የኢትዮጵያን ቱባ የሙዚቃ ስራዎች እየሰበሰበ ‹‹ኢትዮፒክስ›› በሚል ስያሜ ለአውሮፓውያን እና ለአሜሪካውያን የማስተዋወቅ ስራ የሚሰራው ፍራንሲስ ፋልሴቶ ከሰራቸው ስራዎች ውስጥ በአንጋፋው ድምጻዊ ሙሀሙድ አህመድ እና በሳክስፎኑ ጠቢብ ጌታቸው መኩርያ የተሰሩት የሙዚቃ ስራዎች በባንዱ መሪ ቴሪ እጅ ገብተው ነበር።

ከዚያም አዲስ የሙዚቃ ስልት እና ቋንቋን በመሞከር የሙዚቃ ቡድኑ አማርኛ ሙዚቃዎችን በማጥናት በአዲስ አበባ ትልቅ የሙዚቃ ድግስ አደረገ። በድግሱ ላይም በአዲስ ጣዕም የተቀናበረውን የሙዚቃ ስራቸውን ካቀረቡ በኋላ የሳክስፎኑን ጌታ የባንዳቸው አባል ማድረግን ተመኙ፤ ጥያቄውንም ለጌታቸው አቀረቡለት። ጌታቸውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የባንዱ አባል ሆኖ ቀጠለ።

የጌታቸው እና የባንዱ ጥምረት ከኢትዮጵያም አልፎ በሌሎች ሀገራትም ጭምር ሆነ። በተለያዩ ሀገራት በመዘዋወር ስራቸውን ሲያቀርቡ በጌታቸው ሳክስፎን እየታጀቡ የኢትዮጵያን ባህላዊ ጭፈራና እስክስታ ማስተዋወቅ ቀጠሉ። ጌታቸው እና የሙያ አጋሮቹ በቋንቋም በባህልም በሚጫወቱት የሙዚቃ ስልተ-ምት የተለያዩ ይሁኑ እንጂ፣ ለመግባባትና መድረክ ላይ የህዝብን ቀለብ የሚስብ ስራን ይዘው ለመውጣት ግን የመናበብ ችግር ፈጽሞ አልነበረባቸውም። ለዚህም የጌታቸው የሙያ አጋሮች እንደ ምክንያት የሚያነሱት አዲስ ነገርን ለመቀበል ዝግጁ፣ ፈጣን፤ ተግባቢነቱም ጭምር መሆኑን ያነሳሉ። ከ104 በላይ ሀገራትን ተዘዋውሮ የሙዚቃ ስራዎቹን ከባንዱ ጋር በመሆን ያቀረበው ጌታቸው በአለም ላይ በሳክስፎን የሙዚቃ መሳሪያ አጨዋወት ከሚታወቁ ባለሙያዎች ጋር እያነጻጸሩ “እነሱን ትመስላለህ” ቢሉትም፤ እሱ ግን እነሱ የሚሏቸውን ሙዚቀኞች አያውቃቸውም ነበር። በዋናነት በፈረንሳይ፣ ቤልጂም፣ ኔዘርላንድ፤ እንዲሁም በበርካታ የአውሮፓ ከተሞች መድረክ ላይ እርጅና ሳይገድበው ስራዎቹን አቅርቧል፤ ሀገሩንም አስተዋውቋል።

ታላቅነቱን የሙያ አጋሮቹ ተናግረው አይጠግቡም። በአንድ ወቅት ስለሙያ አጋራቸው የተጠየቁት አርቲስት መራዊ ስጦታው እንደተናገሩት ጌታቸው ሳክስፎን የሚዘፍንበት ብቻ ሳይሆን የሚሸልልበት፣ የሚፎክርበት፣ የሚፏጭበት ነው መሳሪያው ነው። ሳክስፎን ትንፋሽ የሚጠይቅ ቢሆንም እሱ ግን ብቻውን አንድ ኦርኬስትራን ሸፍኖ ከሶስት እና አራት ሰዓት በላይ ሊጫወት ይችላል።

እንደ አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) አስተያየት ጌታቸው መኩርያ ምንም እንኳን የሚጫወተው የሙዚቃ መሳሪያን ቢሆንም፤ ቃል የሚያወጣ እስከሚመስል ድረስ መሳርያውን ይጠበብበታል። የማይደክም ትንፋሽ፣ የሳክስፎኑ ንጉስ መጠርያዎቹ ናቸው።

ይህ የሙዚቃ ሰው የሳክስፎን ንጉስ ሲጫወት ሲታይ በሙያው ላሉ እና ሙዚቃውን ለሚያውቁ አጨዋወቱ የሚያስቀና፤ ሳክስፎን አናጋሪው የሚባልለት፤ እሱም በመድረክ ላይ ሳክስፎንን ሲጫወት አንዳች ድካም የማይታይበት ባለ ሙያ ነበር።

ጌታቸው በነበረበት የስኳር ህመም ምክንያት የጤና እክል ይገጥመው ጀመር። በእግሩ ላይ በተከሰተው ቁስል እንደልቡ ለመስራት በመቸገሩ የባንዱ እና የጌታቸው ግንኙነት በዚህ ሊገታ ግድ ሆነ። ለዘጠኝ ወር ያክልም ህክምናውን በመከታተል በቤት ውስጥ ቆየ። እድሜው እየገፋ የመጣው ጌታቸው ሳክስፎንን ጨርሶ አልተወውም። እሱም አልተወውም። በተለያዩ መድረኮች ላይ በመድረኩ ፊት ወንበር ላይ ቁጭ ብሎም ቢሆን መጫወቱን ቀጠለ። የተለያዩ ሙዚቀኞች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ስራዎቹን ያቀርባል።

ከዚያም ከአመታት በኋላ ጌታቸው አስቀድሞ ይጫወትበት የነበረው ኤክስ ባንድ 35ተኛ አመቱን ሲያከብር የባንዱን አባል ጌታቸውን መዘከር በመፈለጉ በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ መጣ። ጌታቸውንም የህክምና ባለሙያ ከሀገሩ በማስመጣት አስፈላጊውን ህክምና እንዲያገኝ አደረገ።

በወቅቱ ሰማንያ አመቱን የያዘው ጌታቸው ለባንዱ እና ለአድናቂዎቹ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ በብሄራዊ ቴአትር፣ በራስ ሆቴል፣ በጃዝ አምባ እና አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሲስ በመገኘት በድጋሚ በመጫወት ለአድናቂዎቹ እና ለባንዱ አባላት ደስታን ፈጥሯል። በጊዜውም ጌታቸው እንደሌላው ጊዜ በመድረኩ ላይ እየተንጎራደደ ስራዎቹን አያቅርብ እንጂ በወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ የነበረው አቀራረብም ከዚህ ቀደም ከነበረው ያልተለየና አስደናቂ እንደነበር ይናገራል። ባለትዳርና የዘጠኝ ልጆች አባት የነበረው ጌታቸው መኩሪያ በተለያዩ ሀገራት ተዘዋውሮ የሙዚቃ ስራውን አቅርቧል።

ጌታቸው በሙዚቃ መሳሪያ ብቻ የተቀነባበረ አልበም በመስራት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊም ነው። ከመድረክ ስራዎቹ ባሻገርም ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ፣ በሙዚቃ መሳሪያ ብቻ የተቀነባበሩ ከስድስት በላይ የአልበም ስራዎችን ለአድማጭ አቅርቧል።

“የኢትዮጵያ ንጉስ”፣ “ሞኣ አንበሳ” ለህዝብ ካደረሳቸው ስራዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው። ስድስት ካሴት አልበሞችን፣ ሶስት የሸክላ ስራ፣ አንድ ሲዲ ማሳተምም ችሏል። ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ለ66 አመት ከሙዚቃ ጋር የኖረው አርቲስት ጌታቸው መኩሪያ ከ100 በላይ ሀገራትን ተዟዙሮ ስራውን ሲያቀርብ ያካበተውን ሀብት በገጠመው የልብ ህመም ሳቢያ ለህክምና ማዋል ጀመረ። በህመም ላይ ሳለም ‹‹ትልልቅ ስራዎችን የሰሩ የሀገር ባለውለታዎች በደከሙ ጊዜ የሚረሱ፤ ሲያርፉ ግን የቀብር ስነ-ስርዓታቸው ደማቅ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ያሳዝናል›› በማለት በአንድ ወቅት መናገሩ ተነግሯል። እሱም ህክምናውን በሚያደርግበት ወቅት ባለቤቱም በገጠማቸው የልብ ህመም ምክንያት ህክምና ሲያደርጉ ቆይተው አረፉ። ጌታቸውም ባደረበት ህመም ምክንያት ህክምናውን ሲያደርግ ቆይቶ ሊሻለው ባለመቻሉ በተወለደ በ81 አመቱ፣ በየካቲት ወር ማብቂያ 2009 ዓ∙ም ላይ አረፈ።

በሀገራችን ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያ ሲነሳ በተለይም ሳክስፎን የሙዚቃ መሳሪያ ሲነሳ ጌታቸው መኩርያን አለማንሳት እስከማይቻል ድረስ የማይለወጥ፣ በጊዜ ብዛት የማይቀየር ስምን ተክሎ ያለፈ፤ እድሜውን ለሚወደው ሙዚቃ የሰጠ ታላቅ ባለሙያ ነው፤ የሳክስፎኑ ንጉስ ጌታቸው መኩሪያ ናቸው።

ስም ከመቃብር በላይ!!!

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን  የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You