ሕይወትን በዜማ

የልጅነት አቀበቶች…

የተወለዱት አዲስ አበባ፣ መሀል ሰንጋተራ

ነው፡፡ እናታቸውን እንጂ ወላጅ አባታቸውን በአካል አያውቋቸውም፡፡ አባት በሞት የተለዩት ገና ጨቅላ ሳሉ ነበር፡፡ እናት ከባላቸው ሞት በኋላ ልጃቸውን ለማሳደግ ጎንበስ ቀና ማለት ያዙ፡፡ የእናትነት ድርሻቸውን ሊወጡ ሌት ተቀን ባተሉ፡፡ ትንሹ ይልማ ግን ለወላጆች ፍቅር አልታደሉም፡፡ ጥቂት የልጅነት ጊዜያትን እንዳለፉ እናታቸውን ሞት ነጠቀባቸው ፡፡

ከዚህ በኋላ የይልማ ዕጣ ፈንታ በሌሎች እጅ ሆነ፡፡ ለቁም ነገር ያልደረሱትን የሙት ልጅ ብዙዎች ሊንከባከቧቸው ሞከሩ፡፡ አጋጣሚው ከበርካቶች ቤት ያደርስ፣ ያመላልሳቸው ያዘ፡፡ ይልማ በዕድሜያቸው ከፍ ማለት ሲጀምሩ ራሳቸውን ሊችሉ ሞከሩ፡፡ ይህ ሀሳብ በጉልበታቸው አሳድሮ ከሰዎች ቤት ሥራ

አስጀመራቸው፡፡ ለሁሉም እየተላኩ፣ እየታዘዙ ቀናትን ገፉ፡፡

አሁን ‹‹እከሌ›› የሚሉት ዘመድ ከጎናቸው አይጠራም፡፡ ያላቸው ምርጫ በየሰዉ ቤት ተቀጥሮ የዕለት ጉርስን ማግኘት ነው፡፡ ትንሹ ይልማ ለዚህ ትግል አልሰነፉም፡፡ ‹‹አቤት፣ ወዴት›› ብሎ ማደርን አወቁበት፡፡

ከቀናት በአንዱ ትንሹ ይልማ ከአንዲት ወይዘሮ ዓይን ገባ፡፡ ወይዘሮዋ ልጁን አሻግረው እያዩ ብዙ ማሰብ ጀመሩ፡፡ እሳቸው በዚህ ዕድሜ ለመኖር ስለሚታገለው ታዳጊ ከልብ አዝነዋል፡፡ ይህ ልጅ ጠዋት ማታ ይሮጣል፣ ይታዘዛል፡፡ እንዲያም ሆኖ ኑሮ በወጉ አልተመቸውም፡፡

ይህ ሐቅ የወይዘሮዋን ልብ አሸንፎ ለመርታት ጊዜ አልፈጀም፡፡ ደጋግመው ስለእሱ እያሰቡ አማራጮችን ፈለጉ፡፡ ይልማን ከነበሩበት አስወጥተው ከአንድ ታዋቂና መልካም ሰው ቤት አስገቧቸው፡፡ ሰውዬው በዘመኑ ብዙ ርስትና ቤተሰብ ነበራቸው፡፡ ከእሳቸው እንደደረሱ ነገሮች ለይልማ መልካም ሆኑ፡፡ የቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ፊደል መቁጠር፣ ቀለም መለየት ቻሉ፡፡

ዳዊት ደግመው እንደጨረሱ በወቅቱ ‹‹ስብስቴ ነጋሲ››ይባል ከነበረው ትምህርት ቤት ገብተው የቀለም ትምህርት ጀመሩ፡፡ ከፍ እስኪሉ በአሳዳጊያቸው ቤት የቆዩት ልጅ ውሎ አድሮ ዕድሜ ይፈትናቸው ያዘ፡፡

ወቅቱ የንጉሡ ዘመን ነበርና ለውጥን የሚሹ፣ ከእሳቸው ከፍ ያሉ ወጣቶች ጥያቄ ያነሱ፣ አመጽ ይቀሰቅሱ ነበር፡፡ መኪና በመስበር፣ ድንጋይ በመወርወር ለሚታገሉት ወጣቶች ይልማ አጋርና ታዛዥ ሆኑ፡፡ ድንጋይ በመወርወር አብረው በመጮህ አጋር፣ ረዳት ሆኑ፡፡ ረብሻው ሲሰፋም፣ ችግሩ ሲብስ ከየትምህርት ቤቱ የሚለቀሙ ተማሪዎች ቁጥር ጨመረ፡፡ ይህኔ ስለ ይልማ የአሳዳጊያቸው ልብ በስጋት ተሞላ፡፡

ቀጭን ትዕዛዝ …

አንድ ቀን ይልማ ሳያስቡት ከአሳዳጊያቸው ቀጭን ትዕዛዝ ደረሳቸው፡፡ ሁኔታቸውን ያልወደዱት ትልቅ ሰው በአስቸኳይ አዲስ አበባን ለቀው ወደ አርሲ እንዲሄዱ ወሰኑ፡፡ ይልማ ትዕዛዙን አልተቃወሙም፡፡ ሀሳባቸውን በእሺታ ተቀበሉ፡፡ በልጃቸው አድራሽነት አርሲ የገቡት ታዳጊ ሕይወትን በአዲስ መልክ ሊጀምሩ ተዘጋጁ ፡፡

ይልማ አርሲ፣ ጢቾ እግራቸው በረገጠ ግዜ ሕይወት እንደከተማው አልሆነላቸውም፡፡ በኑሮ ጊዜያትን ቢፈጁም የገጠሩን ውሎና አዳር በቀላሉ አለመዱም፡፡ ከብት መጠበቁ፣ በኩራዝ መጨናበሱ፣ በጭቃና በአፈር መራመዱ ከበዳቸው፡፡

ጥቂትም ቢሆን ፊደል መቁጠራቸውን ሲያስቡት ደግሞ እልህና ቁጭት ገባቸው፡፡ የቀድሞው አስተዳደግ በዓይናቸው ውል እያለ ተቸገሩ፡፡ ይልማ ያለ ምቾት ቀሪ ጊዜን መውሰድ አልፈለጉም፡፡ አካባቢውን ጥለው ሊሄዱ ከራሳቸው ጋር መከሩ፡፡

አንድ ቀን ይልማ በድንገት ሰፈር ቀየውን ትተው ራቁ፡፡ በየደረሱበት በየዛፉ ስር እያደሩም ካሰቡት

ደረሱ፡፡ ከተማ ደርሰው ድሬዳዋ በተሻገሩ ግዜ ስለኑሯቸው መታገል ነበረባቸው፡፡ ሕይወታቸው ግን ከትናንቱ ፈቅ አላለም፡፡ መልሰው ከአንድ ታዋቂ ገበሬ ዘንድ በሠራተኝነት ተቀጠሩ ፡፡

ተጓዝ ያለው እግር …

ይልማ አሁንም ኑሮ አልደላቸውም፡፡ ርቆ መሄድን እያሰቡ ውሰጣቸው ተነሳሳ ፡፡ አንድ ቀን ዳግም ጓዛቸውን ሸክፈው ለመንገድ ተዘጋጁ፡፡ ከጊዜያት በኋላ አዲስ አበባ ሲገቡ ልባቸው ብዙ እያቀደ ነበር፡፡ አሁንም ‹‹እከሌ›› የሚሉት የቅርብ ዘመድ ጎናቸው የለም፡፡ ከቀድሞ አሳዳጊያቸው ቤት ደፍረው አልሄዱም፡፡ በረንዳ እያደሩ ቀናትን ገፉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ከትናንቱ በተሻለ ስለራሳቸው ብዙ ወጠኑ፡፡

አሁን የንጉሡ ዙፋን በወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ተተክቷል፡፡ ለውጥ፣ አብዮት፣ መሬት ላራሹ፣ ይሏቸው እውነቶች በየቦታው ይሰማሉ፡፡ ይልማ ስለራሳቸው ደጋግመው እያሰቡ ነው፡፡ አ እምሯቸው ከብዙ እያ ደረሰ  ይመልሳቸዋል፡፡ በየመንገዱ የሠራዊቱ የሙዚቃ ማርሽ ደምቆ ይሰማል፡፡ ይህ ድምጸት ለይልማ ጆሮ ልዩ ትርጉም አለው፡፡ ቆም ብለው ባደመጡት ቁጥር ውስጣቸው ይማረካል፣ ከልብ ደስ ይላቸዋል፡፡

አሁን በአንድ ጓደኛቸው ሰበብ ብስክሌት መንዳትን ለምደዋል። እሱን እያከራዩ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል እየገባቸው ነው፡፡ አሁንም ስለትምህርት ማሰባቸውን አልተዉም፡፡ ጥቂት ቆይተው ካዛንቺስ ‹‹ልቤ ፋና›› ትምህርት ቤት ገብተው ያቋረጡትን ትምህርት ከስድስተኛ ክፍል ቀጠሉ፡፡ ውሎ አድሮ የራሳቸው ብስክሌት

ኖራቸው፡፡ እሱን እያከራዩ አናጺነትን ጀመሩ፡፡

ይልማ በአንድ ወቅት ሥራው፣ ትምህርቱና የብስክሌት ማከራየቱ ተጋጭቶባቸው እረፍት አልባ ሆነው

ነበር፡፡ ከትምህርት መልስ ከዕንቅልፍ እየታገሉ በብስክሌት ሲጓዙ ዕንቅልፍ አድክሟቸው የከፋ የመኪና አደጋ

ደርሶባቸዋል፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ያለ አንዳች ጉዳት በሕይወት ቢተርፉም ዛሬም ድረስ በትዝታ ያወጉታል፡፡

ሰውዬው በአናጺነቱ አልሰነፉም፡፡ ሙያውን አዳብረው ‹‹ኤካፍኮ›› ከተባለ ድርጅት

ተቀጠሩ፡፡ በዚህ ቦታ ከብዙዎች ተገናኝተው ስለማንበብ፣ ስለመወያያት ጥቅም ተረዱ፡፡ ይህ ተሞክሯቸው በአንድ

አላቆያቸውም፡፡ የተሻለ ከሚሉት ስፍራ ገብተው ሥራውን ቀየሩ፡፡ ብሔራዊ መሐንዲስ፣ በርታ ኮንስትራክሽን፣ ቫርኔሮ ከተባሉ መሥሪያ ቤቶች ተዘዋውረው በኮንስትራክሽኑ የአናፂነት እጃቸውን አስመሰከሩ፡፡

ራስን ፍለጋ…

አሁን ይልማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመጨረሰ እየታገሉ ነው፡፡ በዚህ መሐል ውል የሚላቸው የሙዚቃ ፍቅር ከእሳቸው ጋር ውሎ ያድራል፡፡ በልጅነታቸው የሰሙት የሠራዊቱ ሙዚቃ፣ በዚህ ተነሳስተው ውትድርናን የተመኙበት ጊዜ፣ በጥምቀት በዓል የተጫወቱት አርሞኒካ ሁሉ ትዝታቸው ነው፡፡

የአርሞኒካው ልምድና ፍቅር ይልማን ወደ ሙዚቃው ይመራቸው ይዟል፡፡ ካሉበት የአናፂነት ሙያ ጎን ለጎን ክራር እያነሱ መደርደር ልምዳቸው ሆኗል፡፡ የእሳቸው ክራር ከተለመደው ስድስት ክር በሁለት ጨምሮ ስምንት ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ይህን ያደረጉት ራሳቸው በፈጠሩት ዘዴና አዲስ መላ ነበር፡፡

ይልማና ክራራቸው እያደር በእጅጉ

ተዋደዱ፡፡ ማንጎራጎር በፈለጉ ግዜ ክራሯ እንደልባቸው

ትሆናለች፡፡ ከበሮ፣ መሰንቆና ዋሽንቱን ተክታ ያሻቸው

ታደርሳቸዋለች፡፡ ክራር ለይልማ ጎዶሎን የምትሞላ፣ ሕይወትን የምታያሳይ፣ መስታወት ነች፡፡ በፈለጓት ጊዜ ከእሷ እየተያዩ ያወጓታል፡፡

ይልማ በዘመነ ደርግ በአኢወማ ተሳትፎ የሙዚቃ ልምድ አዳብረዋል። የታዋቂ ዘፋኞችን ሙዚቃ በመጫወት፣ ዜማና ግጥም ይደርሱ ነበር፡፡ ይህ መንገድ ቆየት ብለው ለገቡበት የሙዚቃ ሕይወት አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ ዛሬም ድረስ የካዛንቺሱን ቀበሌ 23 መድረክና አካባቢውን ከልብ ያመሰግናሉ፡፡

ትዳር – በአንድ ሳምንት …

ይልማ ሕይወታቸውን በወጉ መምራት ሲይዙ ቤት አግኝተው ኑሮን ጀመሩ፡፡ የቀበሌው ቤት ክፍያ አልከብዳቸውም፡፡ ቤት የሚሰረስሩ፣ በር የሚሰብሩ ሌቦች ግን ስጋት ሆኑባቸው፡፡ ለዚህ መፍትሔው ምግብ እያበሰለች ቤት የምትጠብቅ ሠራተኛ መፈለግ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ታዲያ አንዲት ሴት ቤታቸውን እየጠበቀች ምግብ ለማብሰል ተስማማች፡፡ ይህች ሴት የተገኘችው በቅርብ ባልንጀራቸው ፍለጋ ነበር፡፡

በደሞዝ ተቀጥራ ጥቂት ቀናትን እንዳለፈች ውል ይሉት ጉዳይ ተረስቶ ስምምነቱ ታጠፈ፣ ሁለቱ በአንድ አድረው አንሶላ ተጋፈፉ፡፡ ፍቅር ጸና፣ መዋደድ መጣ፡፡ ሥራ በጀመረች ልክ በሳምንቱ በቤታቸው ወዳጅ ዘመድ ተጠርቶ፣ ግብዣ ሆነ፡፡ ውሉ ታስሮም ጋብቻቸው ድል ባለ ሠርግ ተፈጸመ፡፡

ይልማ ሳያስቡት የገቡበት ትዳር ጎጇቸውን

አሞቀው፡፡ የመኖር ወግ ደርሷቸው ‹‹ቤቴ፣ ባለቤቴ›› ማለት ያዙ፡፡ ሚስት አስቀድሞ አንድ ልጅ ነበራትና በይልማ ይሁንታ ከቤት እንዲመጣ ሆነ፡፡ እንደ ልጃቸው ተንከባክበው

አሳደጉት፡፡ ልጁ ስማቸውን ወርሶ በእሳቸው ተጠራ፡፡ እንዲህ በሆነ ጥቂት ጊዜያት በኋላ ለእሳቸው የመጀመሪያውን ወንድ ልጅ ታቀፉ፡፡ ቤታቸውን ደስታና ፍስሐ ሞላው፡፡

ይልማ የአናፂነት ሙያቸውን ቀጠሉ፡፡ አሁን አብሯቸው የኖረው የሙዚቃ ፍቅር ከክራራቸው ተዛምዶ ዜመኛ አድርጓቸዋል፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ባለ ስምንት ክሯን ክራር አንስተው የውስጣቸውን ያወጣሉ፡፡ ሁሌም በርካታ ዓይኖችና ጆሮዎች ያተኩሩባቸዋል፡፡ ክራራቸውን በያዙ ጊዜ በአምስት የተለያዩ የአገር ውስጥ ቋንቋዎች በጎ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ይጥራሉ፡፡ የመልዕክታቸው አብዛኛው ዓላማ በትውልዱ ላይ ያተኮረ ነው ፡፡

ይህ ትውልድ ባሕሉን እንዲጠብቅ፣ ነባር ወጉን እንዳይለቅ፣ ጨዋነቱን እንዲያከብር ብለው ባሰቡ ግዜ ክራራቸውን ይጠቀማሉ፡፡ የሙዚቃን ፍቅር፣ የሙያውን ክብር በዜማቸው ያሰማሉ፡፡

አንዳንዴ ከክራራቸው ጋር ያላቸው ቁርኝት የቤተሰብን ጊዜ ይሻማል፡፡ ይህ አይነቱ አጋጣሚም ከሚስታቸው እያጋጨ ያነታርካቸዋል፡፡ ይህኔ ይልማ ‹‹ፀባይ፣ ጥርስና ጸጉር የለኝም›› እያሉ በራሳቸው ይቀልዳሉ፡፡ ሁኔታቸውን በማሳቅ አሳልፈውም ክፉ ነገሮችን ያመልጣሉ፡፡

‹‹ጉልቤው ይልማ››

አንዳንዴ ደግሞ ይልማ ጉዳያቸውን በጉልበት ለመፍታት ይሞክራሉ፡፡ ይህ ኃይለኝነታቸው ታዲያ በሌሎች ዘንድ ‹‹ጉልቤ›› የሚል ስያሜ አሰጥቷቸዋል፡፡ ብዙ ግዜ እንዲህ አይነቱ ባሕሪያቸው የሚገለጸው ሰዎች ሲበደሉና ሲጠቁ ባዩ ግዜ ነው፡፡ ይልማ መቼም ቢሆን ኅዘንና ዕንባን ማየት አይሹም፡፡ መፍትሔ በመሰላቸው ግዜ ከግልግል ድብድብ ምርጫቸው ይሆናል፡፡

ይልማና የሙዚቃ ፍቅር በክራር ብቻ

አልተገደበም፡፡ ፍላጎታቸውን ለማሳየት ከመጀመሪያዎቹ እስከ ቅርብ ጊዜያቱ የሙዚቃ አይዶል ውድድሮችን የመሳተፍ ዕድል አግኝተዋል፡፡ እንዳሰቡት ሆኖ አሸናፊነት ከእሳቸው ባይሆንም ችሎታቸውን አሳይተዋል፡፡

ይልማ ዓመታትን ከክራር ጋር ሲወዳጁ የአናፂነት ሙያቸውን አልተዉም፡፡ ዛሬም በዕድሜያቸው ማምሻ የተገኘውን እየሠሩ ያድራሉ። በዚህ ሙያቸው ብዙ አይተዋል፣ ችግርን አልፈው ከዕንቅፋቶች

ተጋፍጠዋል፡፡ ከአስር ዓመታት በፊት በሥራ ላይ ሳሉ የደረሰባቸው የኤሌክትሪክ አደጋ መላ ሰውነታቸውን ጨምሮ ጭንቅላታቸው ላይ ጉዳት አስከትሏል፡፡ ይህ ሕመም ዛሬ ቁስሉ ባለመሻሩ ከሐኪም ቤት ደጃፍ እያመላለሳቸው

ነው፡፡

ክራር እንደ እንጀራ …

ዛሬ ይልማ ዕድሜያቸው ገፍቷል፡፡ ለመሥራት ፍላጎት ባያጡም እንደቀድሞው እንደ ትናንቱ ሮጥ ብለው፣ በአናፂነት ሙያቸው ሥራ አይገኙም፡፡ ክራራቸው ግን አሁንም ፍቅራቸው ናት፡፡ ባሻቸው ግዜ አንስተው የውስጣቸውን ያዜሙባታል፡፡ ከባለ ስምንት ክሯ ክራር ጋር ጎዳና መሐል በተገኙ ግዜ ተመልካቻቸው ብዙ ነው፡፡

ይልማ ተመልካች በርከት ብሎ በሚገኝበት አራት ኪሎ፣ ጎላጎል፣ ካዛንቺስ፣ መናኸሪያ ሆቴል አካባቢ የመገኛ ቦታቸው ነው፡፡ እሳቸው እነዚህን ቦታዎች ‹‹ስቱዲዮ›› ሲሉ ይጠሯቸዋል፡፡ ክራራቸውን አንስተው ባዜሙ፣ ባንጎራጎሩ ጊዜ ቆም የሚሉ መንገደኞች እያደነቁ ይሸልሟቸዋል፡፡ በርካቶቹም በሥራቸው ተደስተው ያበረታቷቸዋል፡፡

ይህ አይነቱ አጋጣሚ በአዛውንቱ ይልማ ውስጥ ታላቅ ኃላፊነትን አድርቷል፡፡ እሳቸው ሙዚቃቸው ይጣፍጥ፣ አይጣፍጥ፣ ለውበቱ አይጨነቁም፡፡ ካላቸው አጉድለው፣ ከለመዱት ሸራርፈው መታየትን ግን አይሹም፡፡ የጎዳናው አንጎራጎሪ በተገኙበት ስፍራ ሁሉ ተመልካቾችን ለማስደሰት ይጥራሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ድምፀ መልካሟ ክራራቸው ባለውለታቸው ናት፡፡

ይልማ የክራራቸውን ክሮች ከስድስት ወደ ስምንት ባሳደጉ ጊዜ ዕዝራ አባተና ሙላቱ አስታጥቄን የመሳሰሉ ታዋቂ የመዚቃ ሰዎችን አማክረዋል፡፡ እነሱ የቁጥሩ መጨመር በድምፀቱ ላይ የሚሳየው የከፋ ለውጥ አለመኖሩን በበጎነት አይተው አረጋግጠውላቸዋል።

ዛሬ ይልማ በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች አረፍ እያሉ ከክራራቸው ጋር ማዜምን ቀጥለዋል፡፡ ክራራቸው፣ ቋሚ መተዳደሪያቸው ሆናለች፡፡ በአድናቆት የሚሰጣቸውን ሽልማት ይቀበሉባታል፡፡ ሁሌም በአንደበታቸው ዜማ በጎ ምክር እየዘሩ ለትውልዱ ያደርሳሉ፡፡

አሁንም ያልደከሙ ጣቶቻቸው፣ ከክራራቸው ተዋደው ብዙዎችን እየተጣሩ፣ እየማረኩ

ነው፡፡ ሕይወትን፣ ኑሮን፣ ፍቅርን የሚሰብከው የጎዳና ላይ ሙዚቃ ፈተናዎች ቢኖሩትም ይልማ ጠንክረው በመጋፈጥ ማሸነፍ እንደሚቻል ያምናሉ፡፡

በእርግጥ እንዲህ አይነቱ ልምድ በሌሎች አገራት ክብርና ዕውቅና እንዳለው ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ይህ አይነቱ እውነት በሀገራቸው ዕውን ሆኖ ፈጣን ለውጥ እንዲያመጣ አይጠብቁም፡፡ ይሁን እንጂ የውጭውን ዓለም ማድነቅ ብቻ ሳይሆን የራስን አክብሮ በመሥራት ማሸነፍ እንደሚቻል ግን ፈጽሞ አይጠራጠሩም፡፡

የጎዳናው አንጎራጎሪ መልዕክት …

ይልማ እንደ ማሊ ያሉ ሀገራት ማሲንቆን አዘምነው በማራቀቅ ዓለም የሚያደንቀውን ድምፀት መፍጠራቸውን ያደንቃሉ፡፡ በእኛም ሀገር ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በማራቀቅ ጆሮ ገብ ሙዚቃን መፍጠር ይቻላል የሚል ዕምነት አላቸው፡፡

ይህን ሙከራ አብራቸው በምትዞረው ክራራቸው ተግብረው ለመላው ዓለም የሀገራቸውን የሙዚቃ ቀለምና አቅም ማሳየት ሕልማቸው ነው፡፡ የጎዳናው አንጎራጓሪ አንጋፋው ይልማ ዘለቀ፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You