• መንግሥት እስከ 30 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ማሻሻያዎችን አድርጓል
• የፕሮጀክቶች መጓተት መንግሥትን ለ43 ቢሊዮን ብር ወጪ ዳርጎታል
• የዋጋ ግሽበቱን ወደ አንድ አሃዝ ማውረድ አልተቻለም
አዲስ አበባ፡- የገንዘብ ሚኒስቴር የአስር ወራት አፈጻጸሙን በትናንትናው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ ሪፖርቱን ያቀረቡት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ባለፉት አስር ወራት የኢኮኖሚ ሚዛኑን በመጠበቅ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም የመንግስትን ወጪ በገቢው እንዲሸፍንና የዕዳ ጫናን ለማቃለል የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
የአገር ውስጥ መደበኛ ገቢ አፈጻጸምን በተመለከተ በ2011 በጀት ዓመት ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው የፌዴራል መንግስት መደበኛ ገቢ 235 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ውስጥ በአስር ወራት መሰብሰብ የተቻለው 160 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ አፈጻጸሙ የዕቅዱ 68 በመቶ በመሆኑ አፈጻጸሙን ለማሻሻል በግብረ ኃይሉ አመራር ሰጭነት ባለፉት አስር ወራት ውስጥ በርካታ የታክስ ህግ ማሻሻያ ጥናቶች መከናወኑን አስታውቀዋል፡፡
በጥናቶቹ ውጤት ላይ በመመስረት ስምንት መመሪያዎችና ሦስት ረቂቅ ህጎች ተዘጋጅተዋል። ከዚህም ባሻገር በሥራ ላይ ያለው የታክስ ቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት ያስገኘውን ጥቅምና ጉዳት ለመለየት የሚያስችል ጥናት ተካሂዶ አሰራሩን ወጥ ለማድረግ የሚያግዝ የህግ ረቂቅ የተዘጋጀ ሲሆን በማሻሻያዎቹ አማካኝነት በቀጣይ ከሃያ እስከ ሰላሳ ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ነግረዋል፡፡
የተረጋጋ የዋጋ ዕድገት እንዲኖር ባለፉት አስር ወራት ውስጥ መንግስት ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደረግ መቆየቱንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የመንግስት ወጪ በገቢው እንዲሸፈን፣ የበጀት ጉድለቱም በዕቅድ ከተያዘው በላይ እንዳይንር የውጭ ብድር ጫናን የሚያረግቡ ተግባራትን በማከናወንና እንዲሁም የወጪ ጫና የሚፈጥሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዳይኖሩና የተጀመሩትም የሚጠናቀቁበትን መንገድ የመንግስት ወጪ በዋጋ ንረት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ጥረት ተደርጓል፡፡
ይሁን እንጂ የዋጋ ንረቱን በአንድ አሃዝ እንዲገደብ ለማድረግ አለመቻሉን ነው ሚኒስትሩ ያስታወቁት፡፡ በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሰረት በአሁኑ ሰዓት አገራዊ አጠቃላይ የፍጆታ ዕቃዎች የዋጋ ዕድገት 12 ነጥብ 6 በመቶ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አህመድ፤ በዝቅተኛ የሁለት አሃዝ እንዲረጋጋ የተሰሩ ሥራዎች ግን ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአብዛኛው በብድርና በእርዳታ የሚካሄዱ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ወቅታቸውን ጠብቀው በተያዘላቸው ጊዜ የማይጠናቀቁ በመሆናቸው መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ እየዳረጉ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩልም የክትትልና ግምገማ ችግር መኖሩን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በመሆኑም በዘርፉ ያለውን ክፍተት ለማሻሻል ባለፉት አስር ወራት የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም በበጀት ዓመቱ የፕሮጀክቶችን ፕሮፋይል የማዘጋጀትና ችግር ያለባቸውን ፕሮጀክቶች የመለየት ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የ2010 የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም መነሻ በማድረግ የካፒታል ፕሮጀክቶች ፕሮፋይል ተገምግሞ የማጠቃለያ ሪፖርት የተዘጋጀ ሲሆን በ102 የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ከአንድ ሺ በላይ የሆኑ ፕሮጀክቶች ፕሮፋይላቸው ተገምግሟል፡፡ በተረደገው ግምገማም ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸውና ከመጠን በላይ በመጓተታቸው መንግስት ከ 43 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ እንደሚያስወጣ አረጋግጠዋል፡፡
ይህም የሆነበት ምክንያት ፕሮጀክቶቹ በአመዛኙ የአዋጭነት ጥናት ሳይደረግባቸው ወደ ሥራ በመገባቱና አንዳንዶቹም ትክክለኛ ፕሮጀክት አዘገጃጀት ሥርአት ባለመከተላቸው በታቀደላቸው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው መሆኑን ለመረዳት መቻሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2011
ይበል ካሳ