ቡታጅራ፡- ሥራ አጥነት በወጣቱ ዘንድ እየተስተዋለ ላለው ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ችግር ዋነኛው መንስኤ መሆኑን የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተደረገ አንድ ጥናት አመላከተ፡፡
የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ከሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሰሞኑን በቡታጅራ ከተማ ባዘጋጀው መድረክ የሥራ አጥነት ችግር ለወጣቱ የሥነ ምግባር ብልሽት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ መሆኑን በጥናት ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
ቢሮው ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በክልሉ በተመረጡ ሰባት ከተሞች ባደረገው ጥናት የሥራ አጥነት መስፋፋትና ከዚህ ጋር ተያይዞ የወጣቱ በአልባሌ ቦታዎች መዋል በወጣቶች ዘንድ ለሚስተዋለው የሥነ ምግባር ችግር ዋነኛው መንስኤ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል፡፡
የጥናቱ አቅራቢ የደቡብ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የወጣቶች ስብዕና ልማት ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ቡላ እንደተናገሩት፤ የጉዳዩን ባለቤት ራሳቸውን ወጣቶቹንና በተለያዩ ዘርፎች ከወጣቶች ጋር ሁነኛ ግንኙነት ያላቸውን ዋና ዋና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በክልሉ ሰባት ከተሞች ውስጥ በወጣቶች ላይ ጥናት ተደርጓል፡፡
ጥናቱ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቱ ድረስ በተለያዩ ደረጃዎች በትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችም በጥናቱ የተካተቱ ቢሆንም ሥራ አጥነት የሥነ ምግባር ችግር እየፈጠረ የሚገኘው ግን ከትምህርት ውጭ ባሉ የከተማ ወጣቶች ዘንድ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ ከተካሄደባቸው ከትምህርት ተቋማት ውጭ ያሉ የከተማ ወጣቶች መካከል 31 በመቶው የአልኮል መጠጥ የመጠቀም፣ 29 በመቶው ጫት የመቃም፣ 12 በመቶ ሲጋራ የማጤስና አራት በመቶ የሚሆኑት በጣም አሳሳቢ የሆነውን ሃሽሽ የማጤስ ልማድ እንዳለባቸው በራሳቸው አንደበት መናገራቸውን የጥናት አቅራቢው ተናግረዋል። ለዚህም እንደ ዋነኛ ምክንያት ያነሱት ሥራ አጥነትን ነው፡፡
90 በመቶ የሚሆኑት የከተማ ወጣቶች ሥራ አጥነት ለተለያዩ ጎጂ ልማዶች እያጋለጣቸው መሆኑንና የሥነ ምግባር ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከሥራ አጥነት በተጨማሪ በቂ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት አለመኖር 79 በመቶ፣ የጓደኛ ግፊት፣ የመገናኛና የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ 75 በመቶ እና አደንዛዥ ዕፆችን የሚነግዱ ንግድ ቤቶች መበራከታቸው 74 በመቶ ለወጣቶች የሥነ ምግባር ችግር የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ መሆናቸውን የጥናቱ ውጤት አመላክቷል፡፡
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ከፍታው በበኩላቸው፤ “በክልላችንም ሆነ በአገራችን ወጣቱ በተለያዩ አደንዛዥ ዕጾችና ጎጂ ልማዳዊ ሱሶች ምክንያት በወጣቱ ዘንድ በርካታ የሥነ ምግባር ችግሮች እየተስተዋለ ነው” ብለዋል፡፡
የሥነ ምግባር ችግሮች መንስኤዎችን በመከላከልና የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣት ስብዕና በመልካም በመገንባት ረገድ ሁሉም የድርሻውን መወጣት የሚገባው መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የክልሉ መንግስትም በሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ አማካኝነት በርካታ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ጎጂ ልማዶችንና አደንዛዥ ዕጾችን ለመከላከልና የወጣቱን ስብዕና ለመገንባት የሚያስችል የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ወቅት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉም ወጣቱን ከመጤ ባህሎችና ከጎጂ ልማዶች ለመጠበቅና ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በግንዛቤ ፈጠራና በስብዕና ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የወጣቱ ጉዳይ የነገዋን ኢትዮጵያ የመገንባትና ያለመገንባት ጉዳይ በመሆኑ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው አለመሆኑንና ለዚህም በክልልና በፌዴራል የሚገኙ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በቅንጅት የሚሰሩበት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን አመላክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2011
ይበል ካሳ